>
5:13 pm - Tuesday April 18, 4265

ሶደሬ–ዛሬና ትናንትና (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

ሶደሬ–ዛሬና ትናንትና

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም

ከሶደሬ ጋር የተዋወቅሁት የዛሬ አርባ አምስት ዓመት ግድም ነው፤ አብሮ አደጌ ጌታቸው መድኅኔ የየረርና ከረዩ አውራጃ ገዢ ነበር፤ እሱ ቤት እያደርሁ ሶደሬ እሄድ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ሶደሬ ባዶ ቦታ ነበር፤ የጠበል ሙቅ ውሀ መታጠቢያ ነበረ፤ ባለቤት አልነበረውም፤ የሕዝብ ነበር፤ በጭራሮ ታጥሮ ማንም ሰው ደሀ ሆነ ጌታ ያለምንም ክፍያ ገብቶ በአግዚአብሔር ጠበል እንደልቡ ይጠመቅ ነበር፤ የአውራጃ ገዢው ጌታቸው ሁኔታውን በቅርብ እየተከታተለ እንዲጠበቅ ያደርግ ነበረ፤ ሶደሬ ደሀና ጌታ የማይለይበት የእግዚአብሔርና የሕዝብ ሃይማኖታዊ ከመሬት የሚፈልቅ ፍል ውሀ ነበረ፡፡

ሁሉንም ነገር የመሸጥና የመለወጥ አባዜ ሲጀመር፣ እግዚአብሔርም፣ ሕዝብም ከሶደሬ ወጡ፤ መንግሥት የሚባል ድርጅት ተንሰራፍቶ ያዘው፤ ሥልጣንና ጉልበትን አደባልቆ በመጨበጥ ደሀውን ሕዝብን እግዚአብሔር ከሰጠው ፈውስ ለዩት፤ በመንግሥትና በሕዝብ ስም ሶደሬን ጉልበተኞች በሉት፤ ጋጡት ማለት ይሻላል፤ ቤተ ክርስቲያንም ጉልበት አጥታ ይሁን ሸሪክ በላተኛ ሆና ይሁን ባይታወቀም፣ የደሀው አጋር ስትሆን አትታይም፤ ዛሬ ደሀ ሶደሬ ለመግባት ከሰማንያ አስከመቶ ብር ይከፍላል፤ ውሀ በጠርሙስ ይዞ ከመጣ ስምንት ብር ይከፍላል፤ ርካሹ ክፍል 860.00 ብር ነው፡፡

አግዚአብሔር ያያል፤ አይቶም ይቆጣል፤ ተቆጥቶም አዋሽን ያስቆጣል፡፡
ሰውረነ ከመዓቱ!

Filed in: Amharic