>
5:13 pm - Sunday April 20, 3349

የሽመልስ አብዲሳ ሙሉ ንግግር!!! (ትርጉም - ዶክተር  አብርሃም አለሙ)

የሽመልስ አብዲሳ ሙሉ ንግግር!!!
ዶክተር  አብርሃም አለሙ በአሜሪካ ሀገር ነዋሪ እና የቋንቋ ተመራማሪ ሲሆኑ አማርኛ እና ኦሮምኛን አቀላጥፈው ይናገራሉ። የሽመልስ አብዲሳ የትላንትናው የኢሬቻ ሙሉ ንግግርን እንዲህ ተርጉመዉታል።
 
“ይኸው ለዚህ በቃን
የተከበርከው የኦሮሞ ሕዝብ፣
የተከበራችሁ የገዳ አባቶች፣
የሲቄ እናቶች ፣
ቄሮ እና ቀሬ ፣ የህዝባችን ጋሻዎች፣
እንኳን ድል አደረግን ፣ እንኳንም እዚህ ደረስን ፣
የተከበራችሁ ሚኒስቴሮች ፣ አምባሳደሮች ፣ በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ እዚህ የተገኛችሁ አካላት ፣ ብሔር ብሄረሰቦች ፣ ከሁሉም በላይ የደቡብ ህዝቦች ክልል መንግስት ፣ የጋምቤላ መንግስት ፣ ቤንሻንጉል ፣ አፋር ፣ የሶማሌ መንግስት ፣ የአማራ ክልል መንግስት ፣ እዚህ የተገኛችሁ ብሔር ብሄረሰቦች ፣ ይህ በዓል በዓላችን ነው ብላችሁ እዚህ ስለተገኛችሁ ታላቅ ምስጋና ላቅርብላችሁ ፣ ክቡር ሁኑ ልላችሁ እፈልጋለሁ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ እዚህ ነበር የተሰበረው፤ እዚህ ነበር መዋረድ የጀመረው ፤ እዚህ ነበር ቅስሙ የተሰበረው፡፡ ቱፋ ሙናን ፣ የዚያን ዘመን ታጋዮች የነፍጠኛ ስርዓት እዚህ ነበር የሰበራቸው፡፡ ዛሬ የሰበረንን ሰብረን ፣ ከመሰረቱ ነቅለን ኦሮሞ በተዋረደበት ቦታ ተከብሮ ይገኛል፡፡
ኦሮሞ እንኳን ድል አደረክ፡፡ የ150 ዓመት ትግል ፣ ሃይለማርያም ገመዳ ፣ ዋቆ ጉቱ፣ ታደሰ ብሩ ፣ የኦሮሞ ታጋዮች በሙሉ የተሰበሩበት ፣ በእልህ የታገሉለት ፣ ሌት ተቀን የለፉለት ፣ ኦሮሞነት (ኦሮሙማ) ወደቦታው እንዲመለስ የደከሙት ፣ ዛሬ የኦሮሞ ታላላቆች በከፈሉት መስዋእትነት ፣ በተለይም ቄሮ እና ቀሬ ስናይፐር ፊት ቆመው ታግለው ኦሮሞን ዛሬ የድል ባለቤት አድርገዉት ይገኛሉ ፡፡ ይህ ድል የግለሰቦች አይደለም ፣ይህ ድል የተወሰኑ ቡድኖች አይደለም፤ ይህ ድል የኦሮሞ ሕዝብ ድል ነው ፡፡
ኦሮሞ እንኳን ድል አደረክ፡፡ ያለፉት ስርዓቶች የኦሮሞ ማንነት እና ምንነት እንዲሰበር ፣ የኦሮሞ ማንነት በነበረበት ቦታ ላይ ሌላ ነገር ገነቡ፡፡ የኦሮሞ ምልክት በነበረበት ሌላ ነገር አስቀመጡ ፣ ሌላ ስም አወጡለት፡፡ ሆኖም ሊቀብሩት አልቻሉም ፤ ሆኖም ሊቀብሩት አልቻሉም ፤ ሆኖም ሊያስቀሩት አልቻሉም፡፡ የኦሮሞ እዉነት ተነስቶ ተናገረ ፤ የኦሮሞ እዉነት ተነስቶ ቆመ፡፡ እንኳን ድል አደረግን!”
Filed in: Amharic