>

"በሽመልስ አብዲሳ ንግግር አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን የፓርላማ ወንበር የቡና ቤት ባለጌ ወንበር አይገኝም!!!" (ስዩም ተሾመ)

በሽመልስ አብዲሳ ንግግር አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን የፓርላማ ወንበር የቡና ቤት ባለጌ ወንበር አይገኝም!!!”
ስዩምተሾመ
የኦሮሚያ ም/ፕሬዝዳትን ሽመልስ_አብዲሳ “ነፍጠኞች የሰበሩን ቦታ ላይ ነፍጠኞችን ሰብረን ታሪክ ሰርተን የሀገሪቱን ትልቅ ከተማ ለመቆጣጠር ለደረስንበት ለተሻገርንበት ወቅት እንኳን አሰረሳችሁ!” በማለት በአጉል እብሪት ተናግሯል።
አቶ ሽመልስ ከተናገረው ይልቅ የተናገረበትን ምክንያት በጥሞና ማጤን ተገቢ ነው። በእርግጥ ይህ ንግግሩ የሚያስደስተው በአቅራቢያው የነበረውን ጃዋር መሃመድ እና ልክ እንደእሱ የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸውን ነው። ከዚያ በተረፈ ያለው የኦሮሞ ህዝብ ከስድብና ጥላቻ የሚያተርፈው ነገር እንደሌለ ጠንቅቆ ያወቃል። በህወሓት ዘመን የሰለቸውን ቂምና ጥላቻ በራሱ ልጆች መድገም አይፈልግም።
 በህወሓት መሪነት የተዘረጋውን ዘረኛ ስርዓት በተደረገው ትግል ኦሮማራ ጥምረት አማካኝነት አብሮት ሲታገል ለነበረው የአማራ ህዝብ ንቀትና ጥላቻ በማሳየት በራሱ ላይ ጠላትና ጥላቻ መሸመት አይሻም። በመሆኑም በአቶ ሽመልስ ላይ የሚሰነዘረው ትችትና ነቀፌታ ያለ አግባብ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተቃጣ ጥቃት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
 የቀድሞ መሪዎች ከራሳቸው ባለፈ የወጡበትን ህዝብና ማህብረሰብ አይወክሉም ካልን በተመሣሣይ አቶ ሽመልስ አብዲሳም ከራሱና አጨብጫቢዎቹ በዘለለ የኦሮሞን ህዝብ እንደማይወክል መገንዘብ ይኖርብናል። ነገር ግን አቶ ሽመልስ በዚህ ልክ ራሱን ከህወሓት ጋር ለማመሳሰል ምን አታገለው? በመጀመሪያ ደረጃ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የለማ_መገርሳን ጫማ መሙላት ተስኖት የሚውተረተር ምስኪን ነው።
ወደ ስልጣን በመጣ ሰሞን እዛም-እዚም እየሮጠ ሽለላና ቀረርቶ ካሰማ በኋላ ወደ ዋናው ስራ ሲገባ አቅም ሆነ ችሎታ ያነሰው ይመስለኛል። በዚህ ምክንያት አንዴ ወደ ዶ/ር አብይ ሌላ ግዜ ወደ ጃዋር በመቁለጭለጭ ለመውተርተር ጥረት ሲያደርግ ሰንብቷል። ይሁን እንጂ ከሰሞኑ እውን በሚሆነው የኢህአዴግ ውህደት ውስጥ የረባ የአመራር ሚና እንደሌለው ቀድሞ አውቋል። ከዚያ በኋላ ከጃዋር ጋር አብሮ መርመጥመጥ ጀምሯል። ዛሬም ይህን የተናገረው ከጎኑ ያለውን ጃዋር እና ከፊት ለፊቱ ያሉትን አጨብጫቢዎች እያሰበ ነው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ እና ብዙሃኑ የኦሮሞ ህዝብ ነው። በተለይ የፖለቲካ ድርጅቱ እንደ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያሉ አመራሮችን ይዞ ወደ ምርጫ የሚገባ ከሆነ “በቁጥጥር ስር አዋልናት” ባሏት አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን የፓርላማ_ወንበር ለቡና ቤት የሚሆን ባለጌ_ወንበር አታገኙም። ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ!!!
Filed in: Amharic