>

የኦህዲድ/ኦነግ ሰሞነኛ አፓርታዳዊ ጉዞ (ምሕረት ዘገዬ)

የኦህዲድ/ኦነግ ሰሞነኛ አፓርታዳዊ ጉዞ

ምሕረት ዘገዬ

“እጎድጓዳ ሥፍራ ይበቅላል ደደሆ፤ የፈራነው ነገር መጣ ድሆ ድሆ” ይባል ነበር በዘፈን፡፡አሁን የምለውንም ነገር ዶ/ር አቢይ አህመድ አያውቅም በሉና እንደለመደብኝ ይግረመኝ፡፡

እ.አ.አ በ1990ዎቹ ከደቡብ አፍሪካ የተባረረው ነጮች በጥቁሮች ላይ ይፈጽሙት የነበረው የአፓርታይድ ሥርዓት ከነኮተቱ ወደ ሀገራችን ሰተት ብሎ በመግባት ቅርጹን እየለዋወጠ በመንግሥታዊ ተቋምነት የገዛ ቤተ መንግሥታችን ውስጥ ተገሽሮ ኅልውናችንን መፈታተን ከጀመረ እነሆ 30 ዓመታትን ሊደፍን ምንም አልቀረውም፡፡

የወያኔን አፓርታይድ በመከራና በስቃይ ተወጥተን አንድ ወር እንኳን እፎይ ሳንል በዚያን ጊዜዎቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዝደንት ከአሥመራ ተለምኖ የገባው ኦነግና እዚሁ ቤት ሲያሞቅለት የነበረው ልጁ ኦህዲድ አማካይነት ያን ዘረኛ ቅኝት በዕጥፍ ድርብ በማሻሻል በሀገራችን ቀርቶ በየትም ሀገር ተሰምቶ የማይታወቅ የጥቁር በጥቁር አፓርታይድ እውን እያደረጉ ነው፡፡
የምነግራችሁ ሰሞኑን በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘውን ኦህዲድ/ኦነጋዊ የመድሎ ሥራ ነው – “የከተማውን ወሬ” – የአደባባይ ምሥጢሩን – ነው ሹክ የምላችሁ፡፡ ያልሰማችሁ ካላችሁ፡፡

አዲስ አበባ በኦነግ እየተወረረች ነው፡፡ ለሁለት ተመሳሳይ ዲግሪ ላላቸው የኦሮሞና የሌላ ዜጋ የአበል ክፍያው የሰማይና የምድርን ያህል እንደሚለያይ ብትሰሙ ምን ትላላችሁ? ተመልከቱ – የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በሁለት የትምህርት ሥርዓቶች እንዲመሩ በወያኔ ቋንቋ መመርያ ወርዷል፡፡ ይህን መመርያ መቃወም ማለት በሽብርተኝነትና በነፍጠኝነት ያስከስሳል፡፡ በዚያ ላይ ባለሥልጣናቱ ከመቶ ዘጠናው በላይ (እርግጥ ነው ይሄ አባባል እንኳን መጠነና የዳሰሳ ጥናት ያስፈልገዋል) ኦህዲድ/ኦነጋውያን በመሆናቸው መመርያውን በማስፈጸም ረገድ እስካሁን ከጉርምርምታ ባለፈ ምንም አልገጠማቸውም፡፡
አንድ ትምህርት ቤት በኦሮምኛና በነባሩ የትምህርት ሥርዓት እንዲያስተምር ይገደዳል፡፡ ተማሪዎች በኦሮምኛው እንማር ካሉ መብታቸው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ለምሣሌ አንድ ትምህርት ቤት ካሉት ሃያ አምስት የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ከአንዱ ክፍል 80 ተማሪዎች 15ቱ በኦሮምኛ፣ ከሌላውና 90 ተማሪዎች ካሉት ክፍል ሃያው በኦሮምኛ… መማር እንፈልጋለን ቢሉ በድምሩ 50 ክፍሎች ሊኖሩ ነው – በሁለት የትምህርት ሥርዓት የሚማሩ ተማሪዎችን ለማስተናገድ፡፡ ዳይሬክተርና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች “ክፍሎች የሉንም፤መምህር የለንም…” በሚሉ ወይም በሌላ ተጨባጭ ምክንያቶች ስሞታ ቢያሰሙ ወዲያውኑ እርምጃ ይወሰድባቸዋል – በትንሹ ከሥራ ይባረራሉ፡፡

ስሙን መግለጽ በማልፈልገውና ከሞራል አንጻርም በማይቻለኝ አንድ ክፍለ ከተማ እንዲህ ሆነ፡፡ ቀደም ሲል ከነበሩት የ100 ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮች ውስጥ ሃያው ትግሬዎች፣ ሠላሣው አማሮች፣… ነበሩ፡፡ አሁን 95 በመቶ ኦሮሞዎች እንደሆኑ ውስጥ ዐዋቂዎች ይመሰክራሉ፡፡ (የትምህርት ቤቶቹን ቁጥር ሆን ብዬ አጋንኜዋለሁ) በዚያ ክፍለ ከተማና በሌላውም ጭምር አዲሱን የኦሮሞኛ የትምህርት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ከኦሮሞ አካባቢዎች በርካታ መምህራን መጥተው ተመድበዋል፡፡ እጅግ የሚሰቀጥጠውና የሚያስገርመው መድሎ – የቤት አበላቸው ለኦሮሞ መምህራን ብር 3000 ሲሆን ለሌሎች ብር 800 ነው፡፡ ለአንድ በኦሮምኛ የሚያስተምር የኤም ኤ ምሩቅ ወርኃዊ ጥቅል ደሞዝ ብር 26 ሽህ ሲከፈለው ለሌላው ብር 10800 ነው፡፡ የሒሣብና በጀት ክፍሎችም በዚህ ሸውራራ አፓርታዳዊ አሠራር እጅግ እንደተቸገሩ ይሰማል፡፡

በእሬቻው ረገድ ያለውን ብናይ ተዓምር ነው፡፡ የአብዛኛውን ሕዝብ ቀልብ የሚስበው የኢትዮጰያ ባንዲራ ከየሰው ብብትና ራስ ሳይቀር እየተነጠቀ ሲቃጠል የኦነግ ግን በየትም ሥፍራ በግልጽ እየተውለበለበ ነው፡፡ መከላከያውም፣ፌዴራል ፖሊሱም፣ ደምብ አስከባሪውም… ለዚህ አፓርታይድ ሥርዓት ያጎበደደና የነኦነግን ትዕዛዝ እያስፈጸመ ያለ ይመስላል፡፡ ግዴላችሁም ሰዎቹ አምርረዋል! “ኦሮሞነት ወይም ሞት!” ብለውም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ብዙዎቻችን “የምራቸውን አይደለም” ከሚል በግልጽ ያልተረዳንላቸው ሥነ ልቦናዊና እውናዊ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል – እነዚህ ዶንኪሾቶች፡፡ በዚያ ላይ የቁጥር ዕውቀታቸው ከዜሮ በታች ነው፡፡ “በአዲስ አበባ ከአሥር ሚሊዮን የሚበልጥ ኦሮሞ ከየሚኖርት መጥቶ እሬቻን ያከብራል” ሲሉ አሥር ሚሊዮን ስንት ሚሊዮን መሆኑን አያውቁም፡፡ አዲስ አበባ ከነዋሪዎቿ ቁጥር በላይ ይህን ሁሉ ምናባዊ ተስተናጋጅ በምን አቅሟ ነው ለአንድ ደቂቃም ቢሆን የምታስተናግደው? እርግጥ ነው – መመኘት ይቻላል፤ ቀላልም ነው፡፡ ግን ከእውነት ጋር መላተም መዘባበቻና ቡና ማጣጫ ያደርጋል፡፡ ውሸት ሲደጋገም ደግሞ ያስጠላል፡፡ ኤጭ!

ከመነሻው እኮ የጠብ ያለሽ በዳቦ ዓይነት ሆኖ – በድራቢውም “በገዛ ዳቦየ ልብ ልብን አጣሁት” ዓይነት የሁሉም የራሴ ነው እሳቤ ተመሥርተው እንዲህ ቅጥ አምባራቸው ጠፍቶ ክፉኛ ባለጉ እንጂ በአንዲት ዓለም አቀፍ ከተማ እንዲህ ያለ ባዕድ አምልኮት ተገቢ አልነበረም፡፡ እዩኝ እዩኝታውን ግን አጋጋሉት፤ ዙሩንም አከረሩት፡፡ አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት ገና በዋዜማው ትርምስምሷ ወጥቷል፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል እንዲህ ነው፡፡ ሌቱ የማይነጋ የመሰላት ሀቱ ሴት ቋቷን በአንድ አዳር ግምኛ እንዳደረገችው ሁሉ እነሁሉ አማረሽ የኬኛ ፖለቲካ ሰለባዎችም ሀገራችንን ውልአልባ ልቃቂት እያደረጓት ነው፡፡ ዕብደትን በግለሰብ እንጂ በመንጋ እንደዚህ በግላጭ አይቼ ስለማላውቅ እኔማ በጣም እየገረመኝ ነው፡፡ በብዙ ነገር ታወቅን፡፡

ለማንኛውም ኬኛዎች አዲስ አበባን ለመዋጥ ድፍረታቸው ቅጥ አጥቶ እሰከዚህ አንቀዥቅዧቸዋልና የኢትዮጵያ አምላክ ማብረጃውን ይስጣቸው ከማለት ውጪ በበኩሌ የምለው ሁሉ ጠፍቶብኛል፡፡

Filed in: Amharic