>

ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ!!!

ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ!!!
 
“ የአማራ ብሎም የሀገራችን ህዝቦች የለውጥና የአንድነት ጉዞ በአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ከቶውንም አይደናቀፍም!”
 
በሀገር ግንባታ ውስጥ በርካታ አኩሪ ታሪኮች ያሉት የአማራ ህዝብ ከክልሉ ባለፈ የሀገራችን ህዝቦች ቋንቋቸው፣ ሃይማኖታቸው፣ ማንነታቸውን ጨምሮ ልዩ ልዩ ባህላዊ ዕሴቶቻቸው ተከብረው እንዲኖሩ በደምና አጥንቱ ጭምር በርካታ መስዋዕትነትን የከፈለ ታላቅ ህዝብ ነው፡፡
ባለፋት አመታትም ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ የሆኑ መብቶቹ ተከብረውለት በነፃነት እንዲኖር የክልሉ መንግስት እና ህዝብ መጠነ ሰፊ የሆነ ትግል እንዳደረጉ ይታወቃል፡፡
በተለይም ላለፋት 27 ዓመታት በደግ ህዝብ ጀርባ ተጠልለው እና የሀገራችንን ህዝብ እንደመዥገር ተጣብቀው ዋጋ ሲያስከፋሉ የቆዩ ግፈኞችን ከሌሎች የሀገራችን ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመተባበር፣ በተለይም በአማራ ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሠብ አባላት በመስዋዕትነት ጭምር የታገዘ ትግል በማድረግ የለውጥ አየር በኢትዮጵያ ምድር እንዲመጣ ግንባር ቀደም መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ የለውጥ ጅማሮ በሁከትና መለያየት ውስጥ ትርፍን በሚያሰሉ፣ በሴራ ፖለቲካ ተወልደው ባደጉ አካላት እና የህዝቡን የለውጥ ጉዞ ለመቀልበስ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተቀናጀ መልኩ በመዝመት፣ ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት በማጥፋት፣ ዜጎችን በማፈናቀልና መሠል ሴራዎችን በመጎንጎን በርካታ ጥቃቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል፡፡
በዚህም ከታታሪው እና ከአርቆ አስተዋዩ ህዝባችን ጋር በመሆን በሆደ ሠፊነት የገጠሙንን ችግሮች ሁሉ ተቋቁመን የአመራር ስምሪታችን ለማስተካከልና ህዝባችንን በአንድነት በማሠለፍ እንደ ክልል በልማት፣ በሰላምና በልዩ ልዩ ተግባራት በተለየ እምርታዊ ጉዞ ውስጥ ለመግባት ጥረት እያደረግን ባለንበት በዚህ ወቅት በእነኚህ የከሠሩ የፖለቲካ ቁማርተኞች የእጅ አዙር ትንኮሳ ተካሂዶብናል፡፡ በዚህም እነኚህ የጥፋት ሃይሎች ለዘመናት ተዋዶ፣ ተዋልዶና ተከባብሮ እንዲሁም በቋንቋና ባህል ተሣሥሮ በኖረው የአማራና የቅማንትን ህዝብ መካከል በመግባት እና የአንዱን ወገን የተቆርቋሪነት ጭንብል በማጥለቅ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ርብርብ አድርገዋል፡፡
ከዚህ ሴራ ጀርባም አርሶ አደሮቻችን እና ባለሃብቶቻችን ለፍተው ያለሙትን አዝመራ እንዳይሠበስቡ በማድረግ ክልሉን በኢኮኖሚ ለማዳከም እንዲሁም የታላቋ አገራችን ኢትዮጵያን አንድነት የማይፈልጉ የጥፋት ሃይሎች የአማራን ህዝብ ማዳከም የስትራቴጅያቸው አካል በማድረግ ከመሰሎቻቸው ጋር ሆነው የሽብር ድርጊቶችን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
የተከበራችሁ የአማራ ክልል ብሎም የሀገራችን ህዝቦች፣ 
በሠሞኑ በክልላችን የተፈጠረው የሽብር ተግባር ጀርባ ሲገለጥ የሚገኘው ሃቅ በሠላም ወዳዱ የአማራና የቅማንት ማህበረሠብ ላይ የተለየ ግጭት ኖሮ ሳይሆን ህዝባችንን እንደመዥገር ተጣብቀው ሲመጡት የኖሩና የሁከት ነጋዴ የሆኑ የጥፋት ሀይሎች በተቀናጀ መልኩ “ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራውን በልዩ ልዩ መልኩ ማዳከም” በሚል በሚከተሉት ያሮጌ ዘመን ቆሞ ቀሮች እቅድ መሆኑ በግልጽ ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡ ይህ እቅድ የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ፣ በፋይናንስና ሆን ተብለው ለጥፋት በተከፈቱ ሚዲያዎቻቸው አማካኝነት በተቀናጀ ዘመቻ ታስቦበት የተሠራና የአማራን ህዝብ አንድ እንዳይሆን ለማድረግ ንጹሀንን በመግደል፣ በአማራና በቅማንት ህዝቦች መካከል ተጀምሮ በመላው ህዝባችን ዘንድ የሚቀጣጠል እሣት በመለኮስ፣ የአማራ ህዝብና መንግስትን ሥም በማጠልሸት የከሸፈውን የሀሰት ትርክታቸውን ለመመለስ እና አማራ ውስጣዊ አንድነት እንዳይኖረው በአጠቃላይ የአማራ ክልል ህዝብ በአንድነት እንዳይቆም ጽንፈኛ ሚዲያዎችንና የተለያዩ የቁማርተኞች መሣሪያ የሆኑ በአማራ ስም የተከፈቱ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ጭምር እርስ በርስ እንድንባላ ጥረዋል፤ ሌት ተቀን እየባዘኑም ይገኛሉ፡፡
እነዚህ የሁከት ሃይሎች ይዘውት የተነሡት መጠነ ሠፊ የሆነ የጥፋት ውጥን ቢሆንም በጀግናው ህዝባችንና የክልላችን የፀጥታ መዋቅር የጋራ ርብርብ ረዥም መንገድ ሣይጓዝ እየከሸፈ ይገኛል፡፡
በቀጣይም እነዚህ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አማራን በሁሉንተናዊ መልኩ የማዳከም ኘሮጀክት ያላቸው ያሮጌው ዘመን ቁማርተኛ መዥገሮችን የክልላችን የፀጥታ መዋቅር አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ እየከፈለ ከህዝባችን ጋር ሆኖ በጠንካራ ክንዱ የሚመክታቸው ይሆናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የፌደራል መንግስት እነኚህ ወንጀለኞች፣ ካለፈው ስህተት የማይማሩና በዚህ ታሪክ ይቅር በማይለው የጥፋትና የሽብር ሥራ ላይ የተጠመዱ አካላትን እንዲሁም ጉዳዮን ወደ ሌላ በማላከክ የህዝባችንን ደህንነት ላይ ተጨባጭ ችግር በሆኑ ጽንፈኛ የሀገራችን ሚዲያዎች ላይ ህግና ሥርግትን ተከትሎ እርምጃ በመውሠድ ህግ እንዲያስከብር እንጠይቃለን፡፡
እነኚህ በዚህ ትንኮሳ ላይ እጃቸው ያለበት አካላት ሊያውቁት የሚገባ ቁም ነገር ቢኖር የአማራ ህዝብ የእነኚህን የጥፋት ሃይሎች ሴራ እያወቀ ለዘላቂ አብሮነት ሲባል ያሳየውን ትዕግስትና ሆደ ሠፊነት በንቀት አይን እንዳይመለከቱት እየመከርን ይህ ካልሆነ ግን የክልሉ ህዝብና መንግስት በተለየ ሁኔታ በአንድነት በመቆም ራሱን ለመከላከል የሚገደድ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለተሰው ንጹሀን ዜጎች እና የክልላችን የፀጥታ አካላት በክልላችን ህዝብና መንግስት ስም የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ በዚህ ክቡር መስዋትነታችሁም እንደ አያቶቻችሁና አባቶቻችሁ ሁሉ የአማራ ህዝብ አንድ በመሆን በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንደሚገባና ከፊቱ የሚቆም ተራራ ቢኖር እንኳን የመናድ አቅም እንዳለው ቅንጣት ታክል አንጠራጠርም፡፡
መላው የሀገራችን ህዝቦችም የእነኚህ የሽብር ሃይሎች ዋና ዓላማ አማራን ከማዳከም በዘለለ ግቡ ኢትዮጵያን የማፍረስ መሆኑን ተረድታችሁ ከጐናችን እንድትቆሙ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡ ለዘመናት በአንድነት ተዋህዳችሁ የኖራችሁ የአማራና የቅማንት ህዝቦችም በእናንተ ህይወት ለሚነግዱ የጥፋት ሃይሎች ሴራ ሳትጋለጡ በጋራ በመቆም በተለመደ አብሮነታችሁ ሴረኞችን በአንድነት በመቆም እንደምታሳፍሩ እንተማመናለን፡፡
በክልሉ ውስጥ የምትንቀሣቀሡ የፖለቲካ ፖርቲዎች እና የሲቪክ ማህበራትም ለህዝባችን ጥቅም ሲባል ከመንግስት ጎን በመቆም የጋራ ርብርብ እንድናደርግ እንዲሁም መላው የክልላችን ህዝቦችም አማራን ለማዳከም በልዩ ልዩ ሚዲያዎች የሚነዙ ወሬዎችንና የጽንፈኛ ሀይሎችን አጀንዳ ባለመቀበል ከመቸውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመቆም የጥፋት ሀይሎችን የቀቢፀ ተስፋ ድግስ በጋራ እንድናከሽፍ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
“ የአማራ ብሎም የሀገራችን ህዝቦች የለውጥና የአንድነት ጉዞ በአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ከቶውንም አይደናቀፍም!”
መስከረም 21/2ዐ12 ዓ.ም
ባህር ዳር
Filed in: Amharic