>

«የተከበራችሁ የዘመኔ እንትነኞች ሆይ . . . እንትን እና እንትና መባባሉን ብንተወውስ…. ?!?»  አሰፋ ሀይሉ

የእንትነኝነትን  ዘመን  ከላያችን እልፍ ያደርግ ልን ዘንድ!!!
 
«የተከበራችሁ የዘመኔ እንትነኞች ሆይ . . . እንትን እና እንትና መባባሉን ብንተወውስ…. ?!?» 
አሰፋ ሀይሉ
እኛ የእንትን ሕዝቦች ብዙ ነን፣ እኛ የእንትን ሕዝቦች እንትን ነን፣ እኛ እነ እንትና እንደ እንትን ነን፣ እናሳይሃለን፣ እኛ ባለ እንትን ሕዝቦች እንትና ሕዝብን እንትን እናደርገዋለን፣ እንትና ሕዝብ እንትናን ሕዝብ ያስከነዳዋል፣ እገሌ ሕዝብ የእገሌን ሕዝብ ይበላዋል፣ እገሌ ሕዝብ እገሌን ሕዝብ ያስፈራዋል፣ እገሌ ሕዝብ የእገሌን ሕዝብ ያፍረዋል፣ እገሌ ሕዝብ የእገሌ ሕዝብ ጠላት ነው፣ እንትን ሕዝብ በእንትን ሕዝብ ላይ እንትን አለው፣ እንትና ሕዝብ እንትናን ሕዝብ እንዲህ አደረገ፣ እነ እንትን ሕዝቦች እንትን ሕዝብን እንትን ሊያደርጉት ነው፣ እንትና ሕዝብ በእንትና ሕዝብ ላይ አኩርፎአል፣ እንትን ሕዝብ እንትን ነው፣ እንትና ሕዝብ እንትን ብቻ ነው፣ እንትንና እንትን፣ እንቶኔና እንትኔ፣ እንትን፣ እንትን ሕዝብ፣ አገሌ፣ አገሊት፣ እንትን ሕዝብ…. ወዘተ እና ሌሎች የትየለሌ «እንትኖችን» በምላሳችን፣ በብዕራችን፣ ከለመድን ውለን እድር ብለናል አይደል?? ምን ውሎ ማደር… – ዓመታትንስ ሳናስቆጥር – ዓይነተኛ የኑሮ ዘይቤያችንስ ሁሉ ሣናደርገው እንቀራለን?!!!
እነዚህ ዓይነቶቹ – ሕዝብን ያህል ብዙ እልፍ ሚሊየን ነገር – በአንድ ቅርጫት ውስጥ ጨምረው – የመሰላቸውን አጀንዳ ጭነው – እንትን ወይም እንቶኔ ሕዝብ ብለው በመፈረጅ – በጅምላ ፈረስ ሊጋልቡ የሚሹ – ደጋግመው የሚሰብኩ፣ የሚሞክሩም – ብዙዎች በተለይ በባላንጣ ፖለቲከኞች መንደር ተጎራብተው የሠፈሩ መንደረተኛ እንትነኛ አቀንቃኞች – በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ – በግላጭ የመውጣትና የመሰማት መብት ስላገኙ – የጓዳውን ባዋጅ እንዲሉ – ከነእንትን ዣንጥላቸው ባደባባይ መውጣት ጀምረዋል፡፡ ጀምረዋል ብቻ ሣይሆን ጎምርተዋል፡፡ አሽተዋልም፡፡ እነዚህ የዘመናችን እንትነኞች – ከጊዜ ወደጊዜ – በዓይናችን ሥር እያደጉ – በዓይናችን ሥር እየበዙ እንደሄዱ – ይኸው ዕለት በዕለት በሚሆነው ሁሉ – እያየን፣ እየሰማን፣ እየታዘብን ነው፡፡ ((ወይስ ‹‹ቀድሞ ያልታዩት እየታዩ በመምጣታቸው ይሆን እንዴ… የበዙ የመሠለን?!)
በእርግጠኝነት – የዘመናችን እንትነኞች – አንድም – እንትንና እንትን ብለው በቀደዱት መንገድ – ራሳቸውን ወደ እንትናዊ (ጎግማንጉጋዊ?!) መንገድ ማግባታቸው አንሦ – ይብሱን ደግሞ – ብዙዎችን የዋሃን ሁሉ ወደ ምክንያት-አልባ መንገዳቸው እና ወደ አሳዛኝ የፍልሚያ አርማጌዶናቸው ቀስ በቀስ… በስሜት ድፍድፍ ነዳጅ እያርከፈከፉ … እንትንና እንትን እንትን አስበዋለል እያሉ… አሁን ላይ እንትነኞቹ አሰቡትም አላሰቡትም… ግን አቀንቃኞቹ እነርሱም ራሳቸው ፈጽሞ ወደማይወጡት – ሁላችንም በቀላሉ ወደማንወጣው… ሕዝባዊ የጥፋት አረንቋ ውስጥ ሊጨምሩን እንደሚችሉ – የእንትነኞቹን አኳኋን ትክ ብሎ ላየው… ነገረ-ሥራቸውን ዝግ ብሎ ላሰበው…. የምናየው ነገር…. እጅግ ያስፈራል፣ ያሳስባል – ሰባት ጭንቅላቶች ከአሥር ቀንዶች ጋር እንዳሉት – እንደ ራዕየ ዮሐንስ አውሬ – ያስጨንቃል!!!
«11 ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤ እሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ሆኖም እንደ ዘንዶ+ መናገር ጀመረ።
12…. በመጀመሪያው አውሬ ፊት የመጀመሪያውን አውሬ ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ይጠቀማል። ምድርና የምድር ነዋሪዎች፣ ለሞት የሚዳርገው ቁስል የዳነለትን የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ ያደርጋል።
16 ሰዎች ሁሉ ማለትም ታናናሾችና ታላላቆች፣ ሀብታሞችና ድሆች እንዲሁም ነፃ ሰዎችና ባሪያዎች በቀኝ እጃቸው ወይም በግንባራቸው ላይ ምልክት እንዲደረግባቸው አስገደደ፤
 17  ይህም የሆነው ምልክቱ ይኸውም የአውሬው ስም ወይም የስሙ ቁጥር ካለው ሰው በስተቀር ማንም መግዛት ወይም መሸጥ እንዳይችል ነው። 18 ጥበብ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው፦ የማስተዋል ችሎታ ያለው ሰው የአውሬውን ቁጥር ያስላ፤ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፤ ቁጥሩም 666 ነው።»
የዮሐንስ ራእይ 13 ፡ 11-18
ግን ግን…. እነዚህ የምናወራላቸው…. የእኛው ዘመን እንትነኞች – እየሰበቁት ባሉት ‹‹የእንትን›› አንካሤ የተነሣ…  በያንዳንዱ ዜጋቸው፣ ወገናቸው፣ እና ሕዝባቸው ላይ ውሎ አድሮ ሊመጣ የሚችለውን ሀገራዊ መቅሰፍት… በትክክል አላጤኑትም፣ አልተረዱትም ይሆን…??. ምናልባት – በመልካምነት ካሰቡት – መገመት የሚቻለው ያንን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ – በገዛ ወገኑ ላይ – አሊያም ከገዛ ወገኑ ጋር – ወደምንፈራው ያህል እልቂት በፈቃደኝነት ሊመራው የሚችለው ሰብዓዊ አቅም የለውም – በሚል ቅን እሣቤ ማለት ነው፡፡
አሊያ ግን – እንትነኞቹ ያን የጥፋት ውጤታቸውን – አሁን ላይ ሆነው – በትክክል ተረድተውት – በትክክል ከነቀንዱና ራሶቹ እየታያቸው ከሆነ ግን – እንትንና እንትን እያሉ በሆነ ባልሆነው የሚያናቁሯቸውን ሕዝቦች… ሆን ብለው ወደጦርነት መክተት የሚፈልጉት ግን – ያለምንም መደባበቅ እነዚህ ሰብዓዊነት የሚሰማቸው ሰዎች ሳይሆኑ – ገሃድ የወጡ ሳዲስቶች ናቸው ብለን ለመውሰድ እንገደዳለን፡፡ ማለት የሚቻለውም ይሄንን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላ አማራጭ ያሳጡሃላ፡፡ ጥፋትን የሚወድ ሰው ካልሆነ እንግዲህ ሆነ ብሎ የጥፋትን መንሥዔዎች ሌት ተቀን ተግቶ የሚዘራ እንትነኛ – ታዲያ ሌላ – እሺ ምን ሊሆን ይችላል??
እና እናንተ የዘመኔ እንትነኞች ሆይ፡-….. እንትን ህዝብ፣ እገሌን ሕዝብ፣ እንትና ሕዝብ እንትናን ሕዝብ እያላችሁ – ለአንድ ሕዝብ በጥቅል የምትፈልጉትን ማንነት እያላበሳችሁ – አንዱ ሕዝብ… እንደ ሕዝብ… ከሌላው ህዝብ ጋር ጠላት እንደሆነ ልታሳምኑት ቀን ከሌት የምትቧትሩ የእንትነኝነት አጥማቂያን ሆይ – .. እናንት የጥፋት ዘመን አርማጌዶን መሢሆች ሆይ – እናንት የመጠፋፋት እሣት የምትቆሰቁሱ… የአኬልዳማ ምድር ሰባኪያን ሆይ – እባካችሁ ከጥፋት መንገዳችሁ – ስለፈጣሪ ብላችሁ – ተቆጠቡ፡፡ እናንት ራሳችሁን ወደጥፋት ቁልቁለት እየመራችሁ ያላችሁ የጥፋት ዘመን ነቢያት ሆይ – እባካችሁ – እባካችሁ – ከጥፋት ህልማችሁ ንቁ! 
እናም በመጨረሻ ይሄን ጫን ያለ ወገናዊ መልዕክቴን የምደመድመው – ይሄን አሁን በዚህች ደቂቃ – የዚህን ፖስት ቃላት እንደበገና እየደረደረ ያለውን ይህን ሐሳይ-ሰባኪውን ራሱን ጨምሮ – (Looool) – ሁላችንም – መልካም እንሁን እስቲ! መልካም ለመሆን እንሞክርና እንሣሣት እስቲ! እስቲ መልካምን ነገር ለወገናችን እናስብለት! እስቲ የመጠፋፋት ምኞታችንን (ያ ዓይነቱ ምኞት ካለን!) ከውስጣችን እናምክነው!! እስቲ ከአብራኩ ለፈጠረን ኢትዮጵያዊው ወገናችን ሻማ እንሁን! ልናቃጥለው ሣይሆን – ጨለማውን ልናበራለት!!! ወደተሻለ የብርሃን ዓለም ልናመላልሰው!! ልናበራለት!! እንቅፋት እንዳይገጥመው ልንንበለበልለት!! የጥፋትን ሣይሆን – የመልካም ብሥራትን ፋና – ልናበራለት፡፡ ያይ ዘንድ!! እንጠቅመው ዘንድ – ይጠቅመን ዘንድ – እንጠቃቀም ዘንድ – እናብራው እስቲ የክት ወገናዊ ሻማችንን ለሁላችን! አብረን ልንኖር እንለኩስ የፍቅር ጧፍ!! አበቃሁ፡፡
ዓመታችን የእንትን ዓመት ይሁንልን…!!  … … ማለትም…. የ…ሥኬት!! የ…ሠላም!! የ.. ብልፅግና!! የ… ፍቅር! ያንድነት!! የመሰማማት! የመረዳዳት! የመደጋገፍ! የጥበብ! የተስፋ፣… የብሩህ ንጋት፣ በኅብረታችን፣ በፍቅራችን፣ በትውልዳችን የማያልቅ ደስታ ያሸበረቀ፣ መልካም የብልፅግና…  ዓመት ይሁንልን!!!! ሠላም – ለሁላችን ኢትዮጵያውያን ሁሉ – እኛን ለሚሉ ወዳጆቻችን ሁሉ – በየቤታቸው ጣራ ሥር ስለእኛ ለሚተጉ ለሁሉም በጎ አሣቢዎቻችን ሁሉ ይሁን፡፡
ሠላም ~~~ ለሁላችን!! ሠላም – ላገራችን፡፡ ሠላም – ለኢትዮጵያችን፡፡ ሠላም  – ላፍሪካችን፡፡ ሠላም – ላለማችን፡፡ ሠላም – ለመላው ሕዋችን፡፡ ሠላም –  ለፍጥረተ ዓለሙ በሙሉ ይሁን፡፡ መልካም ጊዜ!! ቻው!!
Filed in: Amharic