>

ያለ መስዋዕትነት የተገነባ ሀገር የለም! (አሰፋ ሃይሉ)

ያለ መስዋዕትነት የተገነባ ሀገር የለም!
አሰፋ ሃይሉ
ባለፈው “ብሔራዊ የአንድነት በዓል” (ወይ እንደዚያ የመሠለ ስያሜ የተሰጠው) የጳጉሜን ዝግጅት በቤተመንግሥት ተደግሶ ሀገርን ጉድ ያሰኘችውን ታዳጊይቱን ትንታግ ገጣሚ ሕሊና ደሣለኝን አሳይቶናል። ስሜቷና ቃላቷ ለጉድ ይንበለበሉ ነበር።
ሀሳቧ ከለጋ ዕድሜዋ በላይ እጅጉን የመጠቀ ነበር። ሀገር ምን ማለት እንደሆነ፣ ለሀገር የሚቆም ወኔያም ትውልድ ምን ዓይነት የፀና አቋም እንደሚላበስ በአስደናቂ ስንኞቿ አሳይታለች። በዛሬው ትውልድ ላይ የፅናት ተስፋ የፈነጠቀችውን ይህቺን ታዳጊ ወጣት ፈጣሪ አብዝቶ ይባርካት።
ሕሊና ካለቻቸው ለሁሉም ሕሊና ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንዲገባው የተሰነቁ ስንኞቿ ውስጥ ከአንድ ሥፍራ በፅሑፍ ያገኘሁት እንዲህ የሚሉትን አስደናቂ ስንኞቿን ነው፦
“ያ ከንቱ ፎካሪ፣ ባረጀ ቀረርቶ፣ ሺህ ጉራ ቢነዛም፣
ሚለዮን ዘር ቢሸጥ፣ አንድ አገር አይገዛም።
“የዘመን እውነት ነን፣
በደግነት ሰማይ በጥበብ የኖርን።
ትግስትም ልክ አለው፣
ስላቀረቀርን ፈርተን እንዳይመስለው።
ማተብ አስሮን እንጂ
ተጣልተን እንዳንቀር በክፍፍል ገደል፣
ካገር ፍቅር በልጦ ሞት ብርቃችን አይደል።
“ንገሩት ለዛ ሰው፣
ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ
ኃይል እንደተራራ ገዝፎ ቢከመርም፣
ክንዱን አፈርጥሞ
እልፍ የሰገደለት፣ ጀግና ቢሰደርም፣
ዓለም የሞተበት
የጠላት ማርከሻ ጦር ቢደረድርም፣
በአንድ ዓይናችን ሠላም
በኢትዮጵያችን ክብር አንደራደርም።”
        ( – ገጣሚ ሕሊና ደሣለኝ)
የሀሳቧና የቃላቷ ግርማ አስገድዶኝ እንጂ አሁን ላነሳ የፈለግሁት የሕሊናን ግጥም አልነበረም። በዋነኛነት ላነሳ የፈለግሁት የዚያኑ ዕለት በሕሊና ተዓምረኛ ግጥም ተውጦ ሰው ልብ ሳይለው ያለፈውን የአንድን የሀገር ሽማግሌ ተብሎ የቀረበ የዕድሜ ባለፀጋ ሰው ንግግር ነው።
የዕድሜ ባለፀጋውን ለማስታወስ እንዲረዳ ይህ ሰው ሕሊና ግጥሞቿን ባቀረበችበት መድረክ ላይ በዚያው ዕለት – “እናንተ በመካከላችሁ ፍቅር ካላሰፈናችሁ – ባንዲራውን አላስረክብም፣ እናንተ ካልታረቃችሁ – ባንዲራውን አላስረክብም፣ እናንተ በአንድላይ ካልቆማችሁ – ባንዲራውን አልሰጥም፣ ወዘተ…” የሚል ተግሳፅ የመሠለ አነጋገር ሲናገር የነበረው ጠና ያለ ሰው ነው።
ይህ ሀሳቡ እጅግ መልካም ነው። ተግሳፆቹም የዋህነት ጭምር የታከለባቸው ግልፅና ቀጥተኛ ንግግሮች ነበሩ። እሠየሁ የሚያሰኙ ናቸው እነኚህም። እኔ ከዚህ የዕድሜ ባለፀጋ ቀጥተኛ ንግግር መሐል ስሰማው ግርምም ድንግጥም ያስባለኝ የንግግሩ ክፍል እንዲህ የሚለው አነጋገሩ ነው፦
“ይሄንን ምክሬን እእጣችኋለሁ…
የእናንተ ደም ማፍሰስ ኤርትራን አልመለሰም፣
ደም በማፍሰስ የሚመጣ ነገር የለም፣
ደም ለማፍሰስ አትዘጋጁ!”
ጥቂት የቃላት አሰካክ ልዩነት ካልተገኘበት በቀር – በሕሊና ደሣለኝ ግጥም የተነሳ ንግግሩ ከሚዲያ አትኩሮት ተድበስብሶ የቀረው የዚያን ዕለቱ የጠ/ሚ አብይ ታዳሚ የዕድሜ ባለፀጋው ንግግር – ቃል በቃል ይህ የተጠቀሰውን የመሠለ ነበር። እና ገረመኝ በጣም የዕድሜ ባለፀጋው ድፍረት!!!
የሀገሪቱ መሪ ባለበት መድረክ፣ በሀገር ደረጃ በቴሌቪዥን ስርጭት በሚተላለፍ ዝግጅት ላይ ምን ማለት ነው ይሄ ንግግር መተላለፉ?? ለማንስ ነው ምክሩ የተላለፈው? ማንስ ነው ያን የዕድሜ ባለፀጋ ለዚያ መድረክና ለዚያ ዓይነቱ ምክር ያጨው??
ኤርትራ ዓለም ሁሉ ዕውቅናውን ከቸራት ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ በገንጣዮች አትገነጠልም ብሎ ደሙን ያፈሰሰውን፣ አጥንቱን የከሰከሰውን ያን አመሥጋኝ ያጣ ጀግና ትውልድ “ለምን ለሀገርህ ደምህን አፈሰስክ?” እያሉ እየወቀሰው መሆኑ ነው አሁን?
ሀገር ልገንጠል ብሎ ሲነሳ ቀድሶና ባርኮ እንካችሁ ብሎ የሰጠ የዓለም ዕብድ ሕዝብ አለ ለመሆኑ በታሪክ??? የአንድ ሀገር ሕዝብ እስኪሸነፍ ወይ እስኪያሸንፍ ድረስ ደሙን ከማፍሰስ ሌላስ ሀገር ሲቆረስበት ምን እንዲያደርግ ነበር ይሄ የዕድሜ ባለፀጋ የጠበቀው?
ያ ጀግና የኢትዮጵያ ወጣት እኮ የተዋጋው ሻዕቢያን ብቻ አይደለም። ወያኔን ብቻ አይደለም። ከገንጣዮቹ ጋር የተሰለፉ የአረብ ሀገሮችን ጭምር ነው። ከገንጣዮቹ ጋር የተሰለፈችውን ልዕለ ኃያሏን አሜሪካንና ምዕራባውያን ሸሪኮቿን ሁሉ ነው የተዋጋው።
(በነገራችን ላይ ካፒታሊስቷ አሜሪካ ሶሻሊስት ነን የሚሉትን ህወኀትንና ሕዝባዊ ግንባርን “መንግሥቱ ኃይለማርያሟን ኢትዮጵያ” ተዋግተው እንዲጥሉ በግልፅ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርፃ ያደረገችውን ቀጥተኛ ድጋፍና ተሳትፎ ለተጠራጠረ ማንኛውም ሰው፦ በ2000/01 እ.ኤ.አ በኢትዮጰያ ጥናት ተቋም ዓመታዊ የምርምር መፅሔት ላይ፦ “The Foreign Policy of the USA toward TPLF/EPLF during 1975-1991” በሚል ርዕስ በስቴት ዲፓርትመንት ኦፊሻል የፖሊሲ ሰነዶችና ሌሎች ማስረጃዎች ጭምር ተደግፎ የቀረበውን ጥልቅና ግልፅ የምርምር ፅሑፍ – ከአ.አ.ዩኒቨርሲቲ አይ ኢ ኤስ ላይብረሪ ሄዶ ማየትና እውነቱን መረዳት ይችላል።)
እና ያን ከሞቀ ቤቱ ማቄን ጨርቄን ሳይል ወጥቶ ኤርትራን ከእናት ሀገሯ ስትገነጠል ዝም ብዬ አላይም ብሎ ለሚወዳት እናት ሀገሩና ለሚወዳት ኤርትራ ደሙን ያፈሰሰውን ትውልድ ነው እኚህ የዕድሜ ባለፀጋ ሊሳለቁበት የሞከሩት? ነደደኝ በጣም። ቆጨኝ። ማፈሪያ ሽማግሌ!!!!!
ደግሞስ አሁን ዳግመኛ “ደም ለማፍሰስ አትዘጋጁ” የሚለውንስ ማስጠንቀቂያ ወይ ምክር ለምን በዚያ ጠ/ሚው በተገኘበት፣ ለመላው ኢትዮጵያ በሚተላለፍ የዝግጅት መድረክ ላይ ማስተላለፍ ለምን አስፈለገ?? አሁንም ልገንጠል ብሎ የሚነሳ የኢትዮጵያ ክፍል አለ ማለቱ ነው የዕድሜ ባለፀጋው???
ማንንስ ነው.. ደማችሁን ለማፍሰስ አትዘጋጁ – ምንም የምትቀይሩት ነገር የለም – ኤርትራ ላይ ደማችሁን አፍስሳችሁ መገንጠሏ ቀረ? እና አሁንም ደማችሁን በከንቱ አትድከሙ። መገንጠል ያለበት ይገንጠል። ሀገርን ለመቁረስ የፈለገ ይቁረስ። ደማችሁን ለሀገር ለድንበር ብላችሁ ለማፍሰስ አትዘጋጁ… እያሉን ነው? እየተባልን ነው? ምን ዓይነት የሚያስጠላ ንግርት ነው? ምን ዓይነት ምክር ነው? ምን ዓይነት የሚቀፍፍ ሥላቅ ነው??
ከሰውየውም ንግግር በኋላ የሰውየውን ሀሳብ፣ በዚያ መድረክ የተነገረበትን አግባብ፣ በቃ ዝም ብዬ ባምሰለሰልኩት ቁጥር ይህን እኔን የተሰማኝን ነገር ለሌሎችም ማካፈል አለብኝ የሚል ሀሳቤ እያደላብኝ መጣ። እናም ሲከነክነኝ የቆየውን ነገር እነሆ አካፈልኩት።
(በነገራችን ላይ፦ የዚያን ደፋር የዕድሜ ባለፀጋ ንግግር ከዩትዩብ ላይ መልሼ ለማየት ያደረግኩት ሙከራ አልሳካ አለኝ። የሕሊና ግጥም ምንባብ አለ። የእርሱ ንግግር ግን ተቆርጦ ወጥቷል። ምናልባት በሌላ ፍለጋ ይገኛል የሚል ፅኑ እምነት አለኝና ያገኘ ተመልክቶ የራሱን ግንዛቤ ይያዝ እላለሁ።)
እንደ ስንብት ማለት የምፈልገው ነገር – በዓለም ላይ ያለ የትኛውም ሀገር – የሆነ የሀገሩ ነዋሪ – ወይም ቡድን – ወይም ሕዝብ ተነስቶ – ከሀገሪቱ ተገንጥዬ የራሴን ሀገር ቆርሼ እወስዳለሁ ቢል – እደግመዋለሁ የትኛውም በዓለም ላይ ያለ ሀገር – ያንን ገንጣይ ሳይዋጋው፣ ደሙን ሳይፋሰስ፣ ለማስቀረት ታጥቆ ሳይነሳ – ሁን ሰላም ብሎ መርቆ የሸኘም፣ የሚሸኝም ሀገር የለም።
አሜሪካኖች የደቡባዊ ግዛቶቻቸው ነዋሪዎች እንገነጠላለን ሲሉ ተዋግተው፣ ደማቸውን አፍስሰው በታላቅ መሥዋዕትነት ተሳክቶላቸው ሀገራቸውን ከመገነጣጠል አድነዋል። እንግሊዞች ከሰሜን አየርላንድ ጋር ለዘመናት ተናንቀው ነው በመጨረሻ በብረትም በዲፕሎማሲም አንድነታቸውን ለማስጠበቅ የተሳካላቸው። ሩሲያኖች ከቺቺኒያ ተገንጣዮች ጋር የሞት ሽረት መሥዋዕትነት ከፍለው ነው ሀገራቸውን ከመገነጣጠል ያዳኑት።
የስፔኖቹ ካታሎኒያኖች እንገነጠላለን ብለው በጦር መሣሪያም፣ በሪፈረንደምም የስፔኖችን አንድነት ሲገዳደሩ የአውሮፓ ኅብረት ጭምር ነው ያወገዛቸው ገንጣዮቹን፣ ስፔኖች በደምም በሠላምም ታላቅ መሥዋዕትነት ከፍለዋል የሀገራቸውን አንድነት ለመጠበቅ። ሱዳኖች ለዓመታት በበረሃ ደማቸውን ሲያፈሱ ኖረዋል ሀገራቸውን ከመገነጣጠል ለማዳን፤ ጠላታቸው በዝቶ ባያቅታቸውና ሀገራቸውን ቆርሰው በግድ ባይሰጡ ኖሮ። የትም ዓለም ላይ ይኬድ። ዛሬ አሜሪካና ቻይና በታይዋን ጉዳይ ሲዛዛቱ የምንመለከታቸው የታይዋን ሕዝብ የራሱን የብቻ መንግሥት እየፈለገም የግዛት አንድነቱን ለማስከበር የሚፈልገው የቻይና መንግሥት ግን መስዋዕትነት እንከፍላለን ብሎ በመቆሙ ነው።
ዛሬ እስራኤል የምንላት ሀገር በተወላጆቿ ደምና አጥንት የተገነባች ነች። ዙሪያዋ ያሉት ሀገራትና ሕዝቦችም እሰየሁ እንኪ ብለው ግዛታቸውን ለእስራኤል ሰጥተዋት አልነበረም፣ ብዙ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለው – ተሸንፈውም፣ አሸንፈውም ነው። ሕንድና ፓኪስታን ካሽሚር በተባለች ቁራሽ ግዛት አንዱ ለሌላው አሳልፌ አልሰጥም ብለው ወደር የሌለው መስዋዕትነት ከፍለዋል። ዛሬ ኒኩሊየር ወድረው ሊጫረሱ እየተዛዛቱ ነው። አንደኛው ሳይሸነፍ ግን ለሌላኛው ባርኮ አይሰጥም። ካሽሚሮቹ ቢሹ እንኳን። ለምን? ሀገር ነዋ።
በትክክል። ሀገር ቆንጥረህ የምትወስደው የቡና ቁርስ አይደለማ። ሀገር በደም፣ በላብ፣ በአጥንት መሥዋዕትነት የተገነባ ነዋ። ሀገር በቀላሉ አልተፈጠረም። በቀላሉም አይቦጫጨቅም። ለዚያም ብዙ ተከታታይ ትውልዶች መስዋዕትነት ከፍለዋል። ሀገር ያለ መሥዋዕትነት አይገነባም። ክብርና ፍቅር ነው የሚገባቸው። እነዚያ ኢትዮጵያዊነት የጠየቀውን ዋጋ የከፈሉ፣ ኃላፊነታቸውን ተወጥተው ያለፉ ክቡር ትውልዶች ናቸው። ያን ታላቅ መሥዋዕትነት ለከፈሉ ትውልዶች – የዕድሜ ባለፀጋው እንደተሳለቀው – ተሳልቆ አይገባቸውም።
ደግሞም እነርሱ ያለፉት ብቻ አይደሉም። የዛሬውም ዘመን ኢትዮጵያዊ ነኝ ያልክ ትውልድ ሁሉ – በመጨረሻው ክፉ ዕለት ኢትዮጵያዊነት የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ካልሆንክ – ኢትዮጵያዊ ዜግነትህን ካሁኑ መለወጥ አለብህ። አሊያም አሠላለፍህን ለይተህ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር መሠለፍ አለብህ።
አንዳንድ ዛሬ ላይ እዚህም እዚያም በተለያዩ አካላት አንደበቶች ሲነገሩ የምንሰማቸው ነገሮች ሁሉ የሚያስገነዝቡን አንድ ትልቅ ቁምነገር አለ። ያም – እንደቀደመው ትውልድ ሁሉ – የዛሬውም በየትኛውም ሥፍራ የሚገኝ ሀገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ሁሉ – በዚያ በማይቀረው ታላቅ የቁርጥ ቀን ላይ – እናት ሀገሩ ጥሪዋን በምታሰማበት በዚያ የቁርጥ ዕለት – ታላቅን መሥዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆኖ መጠባበቅ እንዳለበት።
“ትልቅ ሰው ወይም ትንሽ ሰው ሆኖ መፈጠሩ አይደለም ትልቁ ቁምነገር። ትልቅም ትንሽም የተባለው ሁሉም ሰው ኃላፊ ነው። ትልቁ ቁምነገር ለሀገር ታላቅን ቁምነገር አኑሮ ማለፍ መቻል ነው።” (- ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠነገሥት ዘ ኢትዮጵያ)።
“ንገሩት ለዛ ሰው፣
ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ
ኃይል እንደተራራ ገዝፎ ቢከመርም፣
ክንዱን አፈርጥሞ
እልፍ የሰገደለት፣ ጀግና ቢሰደርም፣
ዓለም የሞተበት
የጠላት ማርከሻ ጦር ቢደረድርም፣
በአንድ ዓይናችን ሠላም
በኢትዮጵያችን ክብር አንደራደርም።”
        ( – ገጣሚ ሕሊና ደሣለኝ)
ፈጣሪ ሠላምን ያብዛልን።
ፈጣሪ ልቦናውን አይንሳን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና የቁርጥ ቀን ልጆቿን አብዝቶ ይባርክ።
__________________
ምስል (ከምስጋና ጋር)፦
“A poster to Prof. Haile Gerima’s film: ‘The Children of Adwa: After 40 Years'”
Filed in: Amharic