>

ነፃ ያልወጣችው ሠንደቅ ዓላማ  (መስፍን ማሞ ተሰማ - ሲድኒ አውስትራሊያ )


ነፃ
ያልወጣችው ሠንደቅ ዓላማ 

 

መስፍን ማሞ ተሰማ

  

አዎ፤ አውሮፓዊው ቅኝ ገዢ ጣሊያን አድዋ ላይ ድል ሆኗል 1888 /ም። በኢትዮጵያና ኢትዮጵያን በሚወክለው ቀስተ ደመናዊ ሠንደቅ ዓላማዋ ላይ ግን ከትውልድ የዘለለ ቂም ቋጥሮ የደማ ልቡን በመዳፉ ደግፎ በተቆረጠው ቋንጃው እያነከሰ አንድ እግሩን ኤርትራ ላይ ልብና ሌላ እግሩን ጣሊያንአውሮፓ ላይ አድርጎና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፍራንቺስኮ ክሪስፒን ከሥልጣን አባርሮ ድፍን ጣሊያን ሀዘን ተቀመጠ። አርባ ዓመት ሲታመምና ሲያገግም ኖረ። ጣሊያን በኢትዮጵያና በሠንደቋ ላይ ለአርባ ዓመት ያረገዘው ቂም ዱቼንና ፋሽስት ፓርቲን ወለደ። ለጣሊያን ትንሳዔ ኢትዮጵያ መሥዋዕት መሆን አለባት ሲል እነሆ ዱቼ በሮም አደባባይ ተጣራ። ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በመሥዋዕትነት ለተዋረደችው ጣሊያን ትንሳኤ አቀረበ። አውሮፓ አጨበጨበ፤ ቪቫ ዱቼ ሲል ደገፈ።

 

ጥቁር ለባሽ የፋሽስት ጦር ከጣሊያን ጫፍ እስከ ጫፍ ተነቃንቆ ኢትዮጵያን እንበቀላለን ሲል ቃል ገባ። በቫቲካንም ቄስ ተባረከ። ዱቼም ለፋሽስቱ ጦር እንዲህ አለ፤ሂዱና ኢትዮጵያን አንበርክኩ፤ የአባቶቻችንንም ውርደት ተበቀሉ፤ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀስተ ደመናዊ ሠንደቅ ዓላማዋን አውርዳችሁ እርገጡ፤ አቃጥሉም፤ ዳግም በዚያች ምድር እንዳይውለበለብም አድርጉ፤ ህገወጥ መለያቸው ነውና በሠይፍና በጥይት አግዱ፤ ሠንደቅ ዓላማውን ይዞ ሲያውለበልብም ሆነ ሲምል ለምታገኙት ሁሉ አንዳች ምህረት እንዳይኖራችሁ፤ መፍጀት እስከ ቻላችሁ ኢትዮጵያንና ሠንደቅ ዓላማዋን የሚለውን ሁሉ ፍጁት ምድሪቷንም አንድዱ፤ የምፅዐት ቀን በኢትዮጵያ ላይ አውርዱ፤ የጣሊያንን ባንዲራ በኢትዮጵያ ሠማይ ላይ አውለብልቡድል ለፋሽስቶች፤ ሞት ለኢትዮጵያሲል ወራሪና ቅኝ ገዢውን የፋሽስት ጦር ወደ ኢትዮጵያ አዘመተ1928 /ም። (ፎቶ፤ የቫቲካኑ ካሕን የፋሺሽቱን ጦር ሲባርኩ)

 

እነሆም የምፅዐት ዘመን በሀበሻ ምድር ሆነ። አዎ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በፋሽስቶች ተረገጠ፤ ተቃጠለ፤ ታገደ። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በፋሽስቶች በይፋ ከኢትዮጵያ ሠማይ ላይ ተጋዘ። ተሰደደ። ህገ ወጥ ሠንደቅ ዓላማ ተብሎም ታወጀ። አረንጓዴ፤ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያን መለያ (መንግሥታዊ ያይደለ) ህዝባዊ ሠንደቅ ዓላማ የያዘ ሁሉ በፋሽስት ጥቁር ለባሽ ኮማንዶና ጦር ሠራዊት በጥይት ተነደለ፤ በእግረ ሙቅ ተከረቸመ፤ በቆመጥ ህሊናውን እስኪስት ተወገረ፤ በሶማሊያ በኤርትራ እና በጣሊያን ደሴቶች እስር ቤቶች እየተወሰደ ታጎረ። በሀገሩ ምድርም ወህኒ ተወረወረ፤ ከሀገርም ተሰደደ። እነሆም ለአምስት ዓመት ኢትዮጵያ በጣሊያን ፋሽስቶች ሥር ወደቀች። እነሆም እልፍ ኢትዮጵያውያንም ስለ ሀገራቸውና ስለ ሠንደቅ ዓላማቸው ወራሪ ፋሽስቶችንና ምንደኛ ባንዶችን እየጣሉ ወደቁ።

 

በአምስቱ ዓመት የወረራና የግፍ አገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ግን ለአንዲትም ደቂቃ ቢሆን ከኢትዮጵያ ምድር ከተራራውና ከጉድባው፤ ከዋሻውና ከገደላ ገደሉ ስር አሻቅባ ከመውለብለብ የሚያግዳት አንዳችም የፋሽስት ሃይል አልነበረም፤ የአርበኛው ሀይልና ጉልበት ሠንደቅ ዓላማውን ከፍ አድርጎ መያዝና ለነፃነቱ መዋደቅ ነበርና!! በአምስት ዓመት የኢትዮጵያ አርበኞች መሥዋዕትነት እነሆ ኢትዮጵያ ከዱቼ ፋሽስት መዳፍ ነፃ ወጣች፤ ታላቂቷም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓለማ ነፃነቷን ተቀዳጅታ በኢትዮጵያ ሠማይ በነፃነት ተውለበለበች። ይህ የሆነው ከአንድም ሁለቴ በቀደመው ዘመን ነበር። (እነሆም በተከታታይ ትውልድ ሁሉ ሠንደቅ ዓላማችንን እንደ አባትም እንደ እናትም ፆታ እያፈራረቅን ዛሬ ድረስ የምንጠራው ለዚህ ነው)

 

የኢትዮጵያና የሠንደቅ ዓላማዋ ፍዳ ከጣሊያን ወረራ ጋር አላበቃም። ሶማሊያ የታላቋን ሶማሊያ ቅዠት እውን ለማድረግ ካንዴም ሁለቴ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ አቃጥላና ረግጣ፤ ኢትዮጵያንም ልታንበረክክ ተንጠራርታ ነበር። ኢትዮጵያንና ሠንደቅ ዓላማዋን የደፈረ በኢትዮጵያውያን አናብስት ክንድ መድቀቁ የታሪክ ሀቅ ነውና የታላቋ ሶማሊያም ቅዥት ያው ቅዠት ሆኖ ቀርቷል።

 

ዘረኝነት የተጠናወታቸው ዕብሪተኞች ግን ድሮም ሆነ ዘንድሮ ከታሪክ አልተማሩም ነገም አይማሩም፤ አይታረሙም። አብነት ቢባል የደደቢቱን ህወሃት የሚቀድም አይኖርም። እርግጥ ነው ያጎረሰን እጅ ነካሹን ሻዕቢያን አንረሳም። በኢትዮጵያና በሠንደቅ ዓላማዋ ላይ የዋለውን ግፍ ለታሪክ ትተነዋል። እንደ ሻዕቢያና ህወሃት ሁሉ ኦነግም የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ አዋርዷል፤ ዘልፏል፤ በተረታ ተረት ትርክት በኢትዮጵያና በተጋመደው የህዝቦች አንድነቷ ላይ ተዘባብቷል። ኢትዮጵያ ላይ በኦቦ ለማ መገርሳ አስገምግሞ የተነሳው ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!” አዝማች ኮከብ መርህ እነሆ ዛሬ ላይኢትዮጵያዊነት የለምእናኢትዮጵያዊ ስለመሆናችን መደራደርለሚሉት ኦነጋውያን ሁሉ ትዝብት ሆነ እንጂ ትርፉ!

 

ፎቶ፤ በአዲስ አበባ የጣሊያን ባንዲራ ወርዶ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ በእንግሊዝ ወታደሮች ሲሰቀል)

 

ዱቼ በራሱ ህዝብ ተዋርዶ ህይወቱን ከማጣቱ በፊት ያኔ ጥቁር ለባሾችን ኢትዮጵያ ላይ ሲያዘምት ለትግራይ ምንደኞች /ባንዶች/ የላከላቸው መልዕክት ነበር፤ አማራና ኦሮሞ ጠላቶቻችሁን ልናጠፋና እናንተን ልናሳድግ በእነሱም አናት ላይ እናንተን ልናበለፅግ የመጣን በመሆኑ ከእኛ ጋር ቆማችሁ ዓላማችንን አራምዱ። አማራና ኦሮሞን ተባብረንእሳትና ጭድእናርጋቸውየሚል። ያኔ የዱቼ ዓላማና ግብ በአብናቶቻችን አርበኞች ደምና አጥንት በአጭር ተቀጨ። ቅኝ አገዛዙም ተሰባበረ። ዱቼም ሞተ ተቀበረ። ፋሺዝም በሀገረ ጣሊያን ተንኮታኮተ። ነገር ግን እነሆ ከትግራይ ምንደኞች የተወለዱት የህወሃት መሥራቾች ደደቢት በረሃ ገብተው ዱቼን ከሙታን መንደር አንስተው ከመንፈሱ ጋር ተጋቡ። እነሆም ዱቼ በደደቢት በረሃ በህወሃት አድሮ ህወሃትን ሆነ። ህወሃትም የዱቼን መንፈስ ወረሰ። ፋሽዝምም በህወሃት ተተካ። ህወሃትም ፋሽሰትን ሆነ። የዱቼ መልዕክትና ዓላማ /አማራና ኦሮሞን በማባላት የትግራይን የበላይነት ማስፈን/ 1967 / ጀምሮ እስከዚህ ዘመን የህወሃት ማኒፌስቶ ሆነ። የህወሃት መለያ!!

 

ዱቼ በአካል ቢሞትም ዓላማው በህወሃት አልሞተም። እነሆ ዱቼም በመለስ ተቀየረ፤ መለስም ዱቼን ሆነ። ጥቁር ለባሹ የዱቼ ወራሪ በህወሃት አጋዚ ወራሪ ተተካ። ከደደቢት እስከ አራት ኪሎ ህወሃት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያን ሠንደቅ ዓላማ እንዳዋረደ፤ እንደረገጠ፤ እራፊ ጨርቅ እያለ ቁሳቁስ  እየቋጠረ አንደተዘባበተበት በግፍና በንፁሃን ደም እየዋኘ እንደ ዱቼ አዲስ አበባን በበቀለኛውና ቂመኛው ወራሪው ጦር ተቆጣጠረ። እነሆም ኢትዮጵያና ሠንደቅ ዓላማዋ በሀገር በቀሉ ወራሪና ቅኝ ገዢ ህወሃት መዳፍ ሥር በኢህአዴግ መንግሥትነት ከግንቦት 20/1983 / ጀምሮ እስካለንበት ዘመን እየተሰቃዩ ይገኛሉ። 

 

እነሆም ኢትዮጵያን ባስተዳደሩት መሪዎች በየትኛውም ዘመነ መንግሥት ውስጥ ተደርጎና ተሰምቶ የማያውቀውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ (የመንግሥት ዓርማ ያይደለ) የኢትዮጵያን ህዝብ ሠንደቅ ዓላማ ፋሽስት ወራሪ ህወሃት አዋጅ አውጥቶ በወንጀለኛ ሠንደቅ ዓላማነት ፈርጆ በኢትዮጵያ ሠማይ ላይ እንዳይውለበለብ አገደ። ከወራሪው ዱቼ ዘመን ቀጥሎ ሠንደቅ ዓላማችን በወንጀለኝነት ከኢትዮጵያ ሠማይ ላይ ሲታገድ ሁለተኛው በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ መሆኑ ነው። ንፁሁን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማ መያዝ በህወሃት አጋዚ ጦር በጥይት ያስነድላል። በወህኒ ቤቶች ለግፍና ለቶርቸር ይዳርጋል። በሽብርተኝነት ያስከስሳል። ከሀገር ያሰድዳል።

 

በኢትዮጵያ ምድር ግን እንዲህ የነበረው በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ዘመን ብቻ ነበር። ህወሃት ሀገር በቀል ወራሪና ቅኝ ገዢ ከመሆኑ በቀር ተፈጥሮውም ሆነ እርኩሰቱ፤ ለኢትዮጵያና ለሠንደቅ ዓላማዋ ያለውም ጥላቻ ከአምስቱ ዓመት የዱቼ ቅኝ አገዛዝ ቢብስ እንጂ የሚያንስ አይደለም።

 

የተስፋይቱን ምድር ኢትዮጵያን የሚጠብቃት አንድ አምላክ በየዘመኑ ከጥፋት የሚታደጋትን ትውልድና መሪ ባልታሰበ ወቅት ባልታሰበ ዘመን እያስነሳ ተዓምር ሲታይ ቆይቷል። 2010 / በወርሃ መጋቢት የሆነው ይኸው ነው። በኦህዴዱ ለማ መገርሳ እና በብአዴኑ ገዱ አንዳርጋቸው ቲሞች የታገዘው በኢህአዴግ ማህፀን ያደገውና የህወሃትን እርኩሰት የተጠየፈው ዶ/ር አብይ አህመድ /ጠቅላይ ሚኒስትር/ ሆኖ ተሾመ! እኛም ኢትዮጵያን አስቀድሞ ኢትዮጵያን ከፍ ላደረገ እንደ ኢትዮጵያዊም እንደ ሰውም ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ የነገ ተስፋና ሠላም ፍቅርና ብልፅግና አንድነትና ህብረት ለቆመ መሪ ሁሉ ድጋፋችንና ዝግጁነታችን እንደ አባቶቻችን ነውና አብይንና ቡድኑን የደገፍነውና ተስፋም የሰነቅነው በሙሉ ጉልበትና ፍላጎትም ከጎኑ የቆምነው እነሆ የኢትዮጵያን ስም ጠርቶ ከፍ ስላደረጋት ነው! ኢትዮጵያውያን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በድፍን ኢትዮጵያ ስናወግዘው ከኖርነው ኢህአዴግ ጎን የቆምነው ኢትዮጵያን የሚታደጉ፤ ኢትዮጵያውያንንም የሚያዳምጡ መሪዎች አገኘን ብለን ነው። 

 

ከደቡብ አፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ ከእስያ ጥግ እስከ አውሮፓ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ (ኮኮብ አልባ) የአባቶቹን ነፃ ሠንደቅ ዓላማ እያውለበለበ <አብይ የኛ፤ አብይ የኛ> እያለ በሲቃ የዘመረው በህወሃት/ኢህአዴግ ስትሳደድና ስትሰደድ የኖረችውም ሠንደቅ ዓላማ ነፃ የምትወጣ መስሎት ነው። በመስቀል አደባባይ ሰማየ ሰማያትን የጋረደው ኮኮብ አልባው ሠንደቅ ዓላማ እየተውለበለበ የአዲስ አበባ ወጣት፤ ጎልማሳና አዛውንት ሰኔ 16 ለአብይና ለቲሙ የድጋፍ ድምፁን ብቻ ሳይሆን የቀቢፀ ተስፈኞችን የግድያ ሙከራ ለሰከንድ ሳያመነታ በደሙ ጭምር አብይን የታደገው የሠንደቅ ዓላማውና የኢትዮጵያ ትንሳኤ ምልክት አብይ ተነክቶብኛል ብሎ በማመኑ ነው። ይህ ሀገራዊና ዓለም ዐቀፋዊ የኢትዮጵያውያን ፍፁማዊ ድጋፍና አብያዊ ዕምነት ከመጋቢት 2010 ዓ/ም ጀምሮ ቢያንስ ለሰባት ወራት ሳይሸራረፍና <ከመደመር ባቡር> ወራጅ ሳይበዛ ዘልቋል። 

 

ይሁንና ይህ ለአብይና ለቲሙ <ከድፍን> ኢትዮጵያውያን ያለ አንዳች ስስት የተሰጠ ዕምነትና ተስፋ በሚያስደነግጥ ፍጥነት ዕምነቱና ተስፋው በአብያዊው መንግሥት <ኢፍትሃዊ> ድርጊቶች ሲሸረሸር፤ ተስፋውም ሲሸሽ መታየቱ እጅግ ቅስምን የሚሰብር ክስተት እየሆነ ይገኛል። ሁለት ሺህ አሥራ ሁለት ገና ከመጥባቱ በመስከረም ወር በአዲስ ዓመት መባቻ ኮከብ አልባዋ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ እንደ ህወሃት/ኢህአዴግ ዘመነ አገዛዝ ሁሉ በኦዴፓ/ኢህአዲግ መሪ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መንግሥታዊ መዋቅር በኦፊሴል በህገወጥ ሠንደቅ ዓላማነት ተወንጅላ ለስደትና ለግዞት መዳረጓ ህወሃት መራሹን ዘመን በአዲስ የመተካት ያህል እንዲሰማን አድርጎናል። ቢያንስ ይህችን የአባቶቻችንን የነፃነት ሠንደቅ በአብያዊው ዘመን በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ያለፍርሃት፤ ያለመ,ታሰርና ያለመከሰስ ስጋት ኢትዮጵያውያን በነፃነት የማውለብለብ መብት ሊኖራቸው ይገባ ነበር። እነሆ ይህ በዶ/ር አብይ መንግሥት ሊሆን ግን አልተፈቀደም!! 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሆይ!! የኢትዮጵያንና የህዝቧን ሠንደቅ ዓላማ በሽብርተኛ ምልክትነት የወነጀለውንና ከኢትዮጵያ ሠማይ ላይ ያገደውን የህወሃት/ኢህአዴግ ህገ ወጥ አዋጅ በአንተ ዘመን ተደግሞ በአደባባይም በህግ አስከባሪዎችህ እጅ ኮኮብ አልባዋ ሠንደቅ ዓላማ ስትዋረድና ስትንገላታ እንደማየት የሚያምና የሚያስቆጣ ሁነት ከቶስ ምን አለ? አብይ ሆይ! በመንግሥትህ በኮኮብ አልባዋ ሠንደቅ ዓላማ ላይ የታወጀውን ዘመቻ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በህጋዊ አዋጅ አንሳልን!!! ይህንን የምንጠይቅህ በበዓለ ሲመትህ መጋቢት 24/2010 / ላይ በክብርና በታላቅ የጀግንነት አክብሮት ደጋግመህ ባነሳሃቸው በአድዋ በመተማ በማይጨው በካራማራና በባድመ ይህቺን ዛሬ የተወነጀለችውን ንፁህ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያን መገለጫ ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው በተሰዉት እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን አጥንትና ደም ነው።

 

(ፎቶ፤ በባድመ ሠማይ ላይ የተውለበለበው ሠንደቅ ዓላማ)

አብይ አህመድ ሆይ! ሌላውን የመሥዋዕትነት አውድማ ሁሉ አቆይተን አንተ ወታደር በነበርክበት ወቅት በህወሃት/ኢህአዴግ አማካይነት በተካሄደው አሰቃቂው የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት በባድመ ሠማይ ላይ የተውለበለበው ሠንደቅ ዓላማ ኮኮብ አልባው ንፁሁ /የመንግሥት ዓርማ ያይደለ/ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ ዓላማ አልነበረምን? እንደምን ቢሆን ነው ሌላው ሁሉ የመሥዋዕትነት ታሪክቢረሳ/ ቢካድእንኳን በዚያ ጦርነት የተሰዋው 70(?) የሚገመት ኢትዮጵያዊ ባድመ ላይ ያውለበለበው የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ወንጀለኛና ሽብርተኛ የሚሆነው?! ይህ በቃላት ልንገልፀው የማንችል እጅግ መሪር ሀገራዊ ማነቆ በድጋሚ የተፈፀመው ዛሬ አንተ በምትመራውና ያኔ ህወሃት በሚያሽከረክረው ኢህአዴግ ነው። 

 

ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነትና የነፃነት ተምሳሌነት ሲተረክና ሲነገር በዚህ ታሪክ ውስጥ ሁሉ /ዛሬ በሽብር ምልክትነት በደደቢቱ ህወሃት የተወነጀለውና ዛሬ ደግሞ አንተ በምትመራው መንግሥት የተደገመው/ ኮኮብ አልባው የኢትዮጵያ ህዝብ ሠንደቅ ዓላማ አለ። 

 

ነፃነቷን በህወሃት/ኢህአዴግ የተገፈፈችውና በአንተ መንግሥት <ወንጀለኝነቷ> የፀደቀው ኮኮብ አልባ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ /የመንግሥት ዓርማ ያይደለች/ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ነፃ ሳትወጣ ስለ ኢትዮጵያውያን ጀግንነትና የጥቁር ህዝቦች ነፃነት ሠንደቅ ተምሳሌነት በአደባባይ መዘከር ምን ማለት እንደሆነ በቃላት ማስቀመጥ አንፈልግም፤ አንተ የተከበርከው /ሚኒስትር አብይ አህመድ የታሪክ ሰው ነህና። ሠንደቅ ዓላማችን በሽብርተኝነት ተወንጅላና ከሀገር ሠማይ ላይ ታግዳና እግር ስር ተጥላ የሠላም ዓየር የሚተነፍስ ኢትዮጵያዊ አይኖርምና አብይ አህመድ ሆይ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ምላሽህን እንጠብቃለን!! ሠንደቅ ዓላማችን ነፃ ትውጣ!!! አዎ! የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ነፃ ትውጣ!!!

 

ኢትዮጵያ በቅን መሪዎቿና በእግዚአብሄር እርዳታ ትንሳኤዋ ዕውን ይሆናል!

መስከረም 2012 ዓ/ም ( ሴፕቴምበር 2019)

ሲድኒ አውስትራሊያ 

ዋቢ

1 ለዚህ ፅሁፍ አቅርቦት በሚስማማ መልክ /ከህወሃት ዓላማና ግብ/ አኳያ የተፍታታው ዱቼ ለትግራይ የላከው መልዕክት የተገኘው ‘የሀበሻ ጀብዱ’ በአዶልፍ ፓርለሳክ ተፅፎ በተጫኔ ጆብሬ መኮንን ከተተረጎመው መፅሀፍ ነው።

*በባድመ ሠማይ ላይ ስለተውለበለበችው ኮኮብ አልባ ንፁህ /የመንግሥት ዓርማ ያይደለች/ የኢትዮጵያ ህዝብ የኢትዮጵያ
ሠንደቅ ዓላማ ቀጣዩን ቪዲዮ ይመልከቱ፤ https://www.youtube.com/watch?v=pDv0uaKuOiA

አድራሻ፤ mmtessema@gmail.com

Filed in: Amharic