>

“ተራማጁ” እና “አድኀሪው” ኢሕአዴግ (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

“ተራማጁ” እና “አድኀሪው” ኢሕአዴግ
በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
እያንዳንዱ እርምጃ፣ ተመጣጣኝ እና ተቃራኒ ድኅረ-ምላሽ አለው። ኢትዮጵያውያን የለውጥ ዕድሎቻቸው ለምን እንደማይፀኑ ሲጠየቁ፥ የሚያገኙት ተደጋጋሚ መልስ “አድኀሪያን” አደናቀፉት የሚል ነው። አባባሉ ያሰልች እንጂ ከእውነት ሙሉ ለሙሉ የራቀ አይደለም። ኢሕአዴግም እለወጣለሁ ሲል፣ አትለወጥም የሚሉ የራሱ ኀይሎች መልሰው እየጎተቱት ነው። ይህ ውጤት ለኢትዮጵያ ሁለት ፓርቲ ስርዓት መወለድ መንስዔ ይሆን ይሆን?
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “የለውጥ ፈር ቀዳጆች” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሐፍ አላቸው። ይህ መጽሐፍ በጄምስ ደ ሎሬንዚ የተጻፈው “የትውፊት ጠበቆች” የተሰኘው መጽሐፍ ካልታከለበት ብቻውን ትርጉም አይሰጥም። ባሕሩ የለውጥ ፈር ቀዳጆች የሚሏቸው ዘመናዊ አስኳላ ቀመስ የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ምሁራን የሚያቀርቡትን የመፍትሔ ሐሳብ፣ ትውፊታችን እንዳይናጋ በሚል ባለፈው አሠራር አዲስ ነገር የሚጠብቁ ተቀናቃኞች ነበሯቸው። ይህ የታሪክ እውነታ ዳግም ፊታችን ተደቅኗል።
አሁን የዐፄያዊውም ይሁን የደርግ ስርዓት ናፋቂዎች በኢትየጵያ ፖለቲካ የጎላ ሥፍራ የላቸውም። በ2010 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ውስጥ የሕዝብ ጥያቄ የወለደው የሥልጣን ሽኩቻ ተጉዞ ተጉዞ፣ ለነባሩ ኢሕአዴግ መክሰም፣ ለአዲሱ ኢሕአዴግ መሰንጠቅ መሥመሩን ጠርጓል። አሁን ኢሕአዴግ ከስሞ ውሕድ ፓርቲ ሆኖ እንዲመጣ የሚፈልገው ቡድን በአንድ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተመራ ነው፤ ከተቃዋሚ ወገን ደጋፊዎችም አሉት። በሌላ በኩል ደግሞ «ፌዴራላዊ ስርዓቱን እና ሕገ መንግሥቱን ማስጠበቅ እንፈልጋለን» የሚለው ቡድን በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እየተመራ ነው፤ ይህም ከተቃዋሚዎች የዓላማ ደጋፊዎች ያሉት ቡድን ነው። የሁለቱን ወቅታዊ ግንኙነት በመመልከት አዲስ ነገር ፈላጊዎቹን “ተራማጅ” እና በነባሩ መንገድ መቀጠል የሚፈልጉትን “አድኀሪ” ብዬ ሠይሜያቸዋለሁ።
“ተራማጁ” ኢሕአዴግ፦ ‘ፌዴራላውያን’
ነባሩ ኢሕአዴግ እንደሚታወቀው ከአራት ክልሎች የተውጣጡ እና የዘውግ ማንነታቸውን የሚያስቀድሙ ዜጎች የመሠረቱት ጥምር ፓርቲ ነው። እያንዳንዱ አባል ፓርቲ በግንባሩ ውስጥ እኩል ድምፅ ያለው ሲሆን፥ ከፓርቲው ውጪ ያሉ ክልሎች ወሳኝ የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን የሚያገኙበት ዕድል የማይሰጥ ግንባር እና ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን ይህንን ክፍፍል አክስሞ ውሕድ ፓርቲ በመመሥረት የሁሉም ክልል ነዋሪዎች አባል ሊሆኑበት እና ወደ ሥልጣን ሊወጣጡበት የሚችሉበትን ፓርቲ ለመመሥረት ዝግጅቱን በይፋ ጀምሯል። “የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ” የሚባል ሥም ይኖረዋልም እየተባለ ነው።
የዚህ ፓርቲ መሥራቾች ‘ፌዴራላዊያን’ ናቸው። ነገር ግን የፌዴራል ስርዓቱ ቢያንስ ክልሎቹ ከዘውጌኝነት መውጣት (de-ethnicise መደረግ) አለባቸው። አልያም ደግሞ የፌዴራል መዋቅሩ መለወጥ አለበት የሚሉ ሰዎች ያሉበት ቡድን ነው። ሆኖም በተለይ የሚለዩበት መርሓቸው ከክልል መንግሥታት አንፃር በጣም ጠንካራ የፌዴራል መንግሥት ያስፈልጋል የሚል ትርክት ያላቸው ፖለቲከኞች የሚሰባሰቡበት መሆኑ ነው። ይህንን ስብስብ “ተራማጁ” ብዬ ልጠራው የወሰንኩበት ምክንያት በነባር ችግሮች ላይ ተመሥርቶ አዲስ መፍትሔ ይዞ ለመምጣት ማሰቡን ነው።
“አድኀሪው” ኢሕአዴግ፦ ‘ኮንፌዴራላውያን’
“ተራማጁ” ብዬ የጠራሁት ውኀድ ፓርቲ መመሥረት ያሰጋቸው ቡድኖች ካሁኑ ቢጤዎቻቸውን ማሰባሰብ ጀምረዋል። ከነዚህም ውስጥ ቀዳሚው ሕወሓት ነው። ሕወሓት መጋቢት ወር 2011 ወይን የሕወሓት ርዕዮተ ዓለም መጽሔት ላይ ባተመው “በኢትዮጵያ አገር ዐቀፍ የተዋሐደ ፓርቲ ጥያቄ ለምን?” በሚል ባቀረበው 43 ገጽ መጣጥፍ ላይ “ውሕደትን በደፈናው ባንቃወምም…” ካለ በኋላ የአሁኑን ኢሕአዴግ “ለውሕደት ቀርቶ አሁን ላለበት የግንባርነት ደረጃም” የማይመጥን ነው ይለዋል። ይልቁንም የማዋሐድ ዕቅዱን “የኢሕአዴግ ዓላማዎችን የማፍረስ” እና “ወደ ፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት” የመሸጋገር ሕልም ብሎ ካጣጣለው በኋላ “ኢህአዴግ ሲቀበር የራሳችንን የተሟላ አማራጭ ይዘን ከውሕደቱ ራሳችንን አግልለን ነው የምንቀጥለው። በዚህ ወቅት ቶሎ ግንባር ፈጥረን አማራጭ ፓርቲ ይዘን ልንቆይ ይገባናል” ይላል። አልፎ ተርፎም “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥታዊ ግንባር” ወይም “የኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራል ግንባር” የሚል ሥም ከወዲሁ ለዚህ ፓርቲ ይጠቁማል።
በዚሁ መሠረት በመቐለ ከተማ የዛሬ ወር ገደማ ባካሔደው እና በርካታ ፖለቲከኞችን በጋበዘበት የውይይት መድረክ መዝጊያ ላይ “ፌዴራላዊ ስርዓቱን እና ሕገ መንግሥቱን ለማዳን” ከፌዴራላዊ ኀይሎች ጋር ለመሥራት በመሥማማት ተበትኗል። በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ጃዋር መሐመድም ይህንን ሐሳብ ተሥማምተውበት በአንድ ንግግራቸው ሲያስተጋቡት ታይተዋል። ከኢሕአዴግ የውስጥ ሰዎች በተገኘ መረጃ መሠረትም ኢሕአዴግ ከስሞ ውሕድ ሲሆን ሕገ መንግሥቱን እና ፌዴራላዊ መዋቅሩን መጠበቅ የሚፈልጉ ከየክልሉ የተውጣጡ ቡድኖች ልክ እንደነባሩ ኢሕአዴግ ያለ ሌላ አዲስ ጥምር ፓርቲ ይፈጥራሉ። ይህ አካሔድ “አድኀሪ” የሚያሰኘው ከላይ በጠቀስነው መሠረት በአሮጌው መንገድ አዲስ ሥራ መሥራት የሚፈልግ በመሆኑ ነው።
የዚህ ጥምር ፓርቲ መሥራቾች ዕጩዎች ‘ኮንፌዴራላዊያን’ ናቸው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የክልል መንግሥታቱ ከፌዴራል መንግሥቱ የበለጠ መጠናከር አለባቸው የሚል መርሕ አላቸው፤ የክልል መንግሥታቱንም እንደ የዘውጌ አገረ መንግሥት (ethnic-states) የሚያይዋቸው በመሆኑ በሕዝብ ቁጥር አናሳ ለሆኑ ቡድኖች ምቹ አይደሉም። ባሕሪያቸው ‘ኮንፌዴራላውያን’ ዓይነት ቢሆንም ቅሉ ራሳቸውን ‘ፌዴራላውያን’ ብለው ይጠራሉ። ከላይ እኔ ‘ፌዴራላውያን’ ብዬ የጠራኋቸውን በሁሉም ክልሎች ሁሉም ኢትዮጵያውያን በነጻነት እና በእኩልነት መኖር ይገባቸዋል የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ቡድኖችንም እነዚህኞቹ ‘አሃዳውያን’ በማለት ያጣጥሏቸዋል።
የሁለት ፓርቲ ስርዓት መወለድ?
ከኢሕአዴግ ሙሉ ለሙሉ መክሰም በኋላ ሁለት ተቃራኒ ቡድኖች መውጣታቸው ሙሉ ለሙሉ ጎጂ አይደለም። እንዲያውም “በአድኀሪያኑ” እና “ተራማጆቹ” በመካከል የሚደረገው እሰጥ አገባ እና ፉክክር ዴሞክራሲያዊ ማመቻመች እና ሁለቱም የፖለቲካ ፍላጎቶች ሚዛን ጠብቀው የሚያድሩበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲወለድ ሊያደርግ ይችላል። ወሳኙ ቁም ነገር ሁለቱ ቡድኖች ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት ‘ሰላማዊ መንገድ በመከተል፣ ብዙ ተከታይ እና አጋር በማፍራት ያደርጉታል ወይ?’ የሚለው ነው። ይህ መሆን ከቻለ ምናልባትም ትልቅ አቅም ያላቸው እና ታች ድረስ የዘለቀ መዋቅር ያላቸው ቡድኖች በመሆናቸው፥ “ተራማጆቹ” እና “አድኀሪያኑ” ኢትዮጵያን ከአውራ (በተግባር አሃዳዊ) ከሆነ የአንድ ፓርቲ ገነን ስርዓት እንደ ብዙዎቹ ትልልቅ (አሜሪካ እና ሕንድ) ዴሞክራሲዎች የሁለት ፓርቲ ስርዓት ሊፈጥሩ ይችላል።
Filed in: Amharic