>
5:14 pm - Friday April 20, 2114

ድብቁ ማህበር ‹‹Illuminati›› (‹ኢሉሚናቲ›) እና ሚስጥራዊ ምልክቶቹ!!! (አሰፋ ህይሉ)

ድብቁ ማህበር ‹‹Illuminati›› (‹ኢሉሚናቲ›) እና ሚስጥራዊ ምልክቶቹ!!!
አሰፋ ህይሉ
እጅግ ከፍተኛ በሆነ ምስጢር ከተቋቋመ ድፍን 240 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ መሥራቹ ዓለም ፍፅምና የነገሰባት የአምላክ ስጦታ ናት ብሎ የሚያምን የሣይንስ ፕሮፌሰር ነው፡፡ በዓለማችን ከኖሩ ባለዕፁብ ድንቅ ጭንቅላት የሳይንሱ ዓለም ሊቃውንት አንዱ ነው፡፡ አዳም ቬሾፕት /Adam Weishaupt (1748–1830)/ ነው ስሙ፡፡ እርሱ ልክ በ May 1, 1776 የመሠረተው ድብቅ ማህበር ‹‹Illuminati›› (‹ኢሉሚናቲ›) ይሰኛል፡፡ ዓለም ላይ ካሉ ድብቅ ማህበራት ውስጥ በኃያልነቱ፣ በምስጢራዊነቱ የሚስተካከለው የለም ይባልለታል፡፡ ህልውናው ከስሟል ቢባልም እስካሁን እንዳለ በማስረጃ የሚተነትኑልህ ብዙ ናቸው፡፡ በዓለም ላይ የሚፈጠሩ ነገሮች በሙሉ በዘፈቀደ የተፈጠሩ እንዳልሆኑና… የዚህ የኢሉሚናቲ (እና ፍሪሜስንና የመሳሰሉት የድብቅ ማህበራቱ) በረቀቁ ምስጢሮች ታቅደው የሚተገበሩ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ዓላማቸው ወጥ የሆነችንና የሰብዓዊነት እና የዕውቀት ብርሃን የተገለጠላቸው ሰዎች አስተሳሰብ የነገሰባትን ያልተከፋፈለች አንድ-ዓለም መፍጠር ነው ይባላል፡፡
አሜሪካ በ July 4, 1776 ከእንግሊዞች ነፃ የወጣችው ህቡዑ የኢሉሚናቲ ማህበር በ May 1, 1776 ከተመሠረተ ሁለት ወር እንደሞላው ነው፡፡ ከአሜሪካ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ጆርጅ ዋሺንግተን ጀምሮ ብዙ ታላላቅ መሪዎች የዚህ የኢሉሚናቲ ህቡዕ አባላት ናቸው ይባላል፡፡ የ1789ኙ የፈረንሣይ የጭቁኖች አብዮት፣ የጆን ኤፍ ኬኔዲ እና የተዋናይት ማርሊን ሞንሮ ሞት፣ ወይም የቢዮንሴ መግነን፣ ወይ የአውሮፕላኖች መሰወር፣ ወይ በዓለም ላይ በአሁን ጊዜ ያሉ ትላልቅ ሃገራትና ተቋማት ድርጊቶች ሁሉ የኢሉሚናቲዎች ምስጢራዊ ዕቅዶችና ተግባራት ናቸው ይባልላቸዋል፡፡ አንዳንዶች የሠይጣን ሉሲፈር ደቀመዛሙርት ናቸውም ይሏቸዋል፡፡ እነሱ ግን ምልክታቸውን በብሮች፣ በምርቶች፣ በተፈጥሮአዊ ዐውዶች፣ በታወቁ ዓለማቀፍ ምልክቶች፣ በተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች፣ በብር ኖቶች፣ በጥበብ ስራዎች ውስጥ ሁሉ በምስጢር እያኖሩ እርስበርስ በምልክት መልዕክቶቻቸውን እየተለዋወጡ ዓለማችንን ከጀርባ ሆነው ወዳለሙት ታላቁ ግባቸው እየወሰዱን ነው የሚሉ ነገር-ፈልፋዮች በተለይ አሁን አሁን ተበራክተዋል፡፡
በነገራችን ላይ በብዙዎች የሚታወቀው የኢሉሚናቲዎች ምልክት፡- በውስጡ ዓይን ያለበት የሶስት ማዕዘን ቅርፅ ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ በታች የቀረቡት በዓለማችን በተለያዩ ጥቅሞች ላይ የዋሉት ምልክቶች ሁሉ (ለካንስ ሳናውቃቸው) የኢሉሚናቲዎች ድብቅ ምልክቶች እንደሆኑ በብዙዎች ይታመንባቸዋል፡፡ እነዚህን ምልክቶች ከጥንታዊ ዘመን እስካሁን በነገሮች ሁሉ ውስጥ ታገኛቸዋለህ፡፡ እናም ኢሉሚናቲዎች የሚመርጧቸው ማተሞቻቸው እና ኮዶቻቸው ናቸው ይባላል፡፡ ለምሳሌ ብዙዎች የሆሊውድ ተዋናዮች የሚያሳየአቸው የተለያዩ ምልክቶች እንደኢሉሚናቲ ምልክቶች ሲወሰዱ… የዩኤስ አሜሪካ ዶላር ላይ ከፒራሚድ ባለሶስት ማዕዘን ቅስት ጋር አብሮ የተቀመጠው ምልክትና ሌሎች ድብቅ ምልክቶች ሁሉ የኢሉሚናቲዎች ምልክቶች ናቸው ይባላል፡፡ በነገራችን ላይ እጅግ የገረመኝ ነገር.. የኢሉሚናቲዎችን የታወቀ የኮከብ ምልክት በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መሐሉ ላይ ጉብ ብሎ ሳየው.. በቃ ‹‹ጉድ! ጉድ! ጉድ!›› ነው ያልኩት፡፡ በእርግጥ እስከዛሬ ከምንም ነገር ጋር አገናኝቼው አላውቅም… አሁን ግን እነዚህ ኢሉሚናቲዎች የሚሏቸው የዓለማችን ታላቅ ህቡዓን ምልክታቸውን ምናልባት እኛ ባንዲራ ላይ እንዲሰፍር አድርገውን ይሆን እንዴ? የሚል ሃሳብ መጣብኝ፡፡ ከዛ ልክ እንደአሜሪካኑ ዶላር.. እስቲ የራሳችንን ብርና ሳንቲሞች ልያቸው ብዬ ባይ.. አሁንም ‹‹ጉድ! ጉድ!›› ያስባሉኝን መዓት የኢሉሚናቲዎች ምልክት እኛ ብሮች ላይ እንደጉድ ተገጥግጠው ያየሁ መሰለኝ እንግዲህ!!
እንግዲህ ወሬ አላበዛም፡፡ የኢሉሚናቲዎቹ ምልክቶቹም እኚሁና፡፡ የእኛን ገንዘቦችም ሁሉም የሚያውቃቸው ናቸው፡፡ አጋጣሚውና ምስስሎሾቹ ግን ግርርር..ም አይልም?? ‹‹የታየህ ቅዠት ነው!›› የሚል ቢኖር ግን እንደገና በመነፅር ደጋግሜ ለማየት ቃል እገባለሁ!! በተረፈ ግን ‹‹ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል!›› እንዲሉ አበው… እኔም ሃሳቤን ለተመልካች ክፍት አድርጌ ብሰናበትስ፡፡ መልካም መደበሪያ፡፡ መልካም ምልከታ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡ ለሁላችን፡፡
Filed in: Amharic