>

ዘመናይት ኢትዮጵያ በአጫጭር ሰዎች የተሞላችው አለምክንያት አይምሰልህ!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ዘመናይት ኢትዮጵያ በአጫጭር ሰዎች የተሞላችው አለምክንያት አይምሰልህ!!!
በእውቀቱ ስዩም
 
ፈረንጆች  አለመጠን ረጅምና ግዙፍ የሆነን ሰው Giant  ብለው ይጠሩታል  :: “ጋይንት”  ብሎ እሚያነበው ስለማይጠፋ” ጃይንት ” መሆኑን  አስታውሼ ልለፍ :: በአማርኛ   መንዲስ የሚል አቻ አለው:: በታሪካንችን ዝነኛው መንዲስ ከታች ፎቶው ላይ ያለው ይመስለኛል::  ይህ ሰማይ- ጠቀስ ሰውየ፤ መጀመርያ  የቤኒሻንጉሉ ጌታ የሼህ ሆጀሌ ባርያ ነበር:: ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ይህንን  “ግራውንድ ፕላስ ቱ “ ጎረምሳ፤   ለራሳቸው ስለፈለጉት፤  ከሼኪው  ተረክበው ፤ወደ አዲሳባ አስመጡትና የውትድርና ትምርት ቤት   አስገቡት :: ሰውየው  ብሩህና ቀልጣፋ ስለነበር ባጭር ጊዜ የመቶ አለቃ ሹመት  አገኘ::   ባንድ የታወቀ ስዊዛዊ የሙዚቃ መምህር ( ፎቶው ላይ ይታያል) አማካኝነት በሙዚቃ ተካነ፤
ይህ መንዲስ  ቁመቱ ሁለት ሜትር ካስር ሳንቲ ሜትር ነው ::  ጌም ኦፍ ትሮንስ በተባለው  ፊልም ላይ  ጃይንት ሆኖ የሚተውነው ያለም የአለም ረጅሙ  ሰው neil fingleton በጥቂት ሳንትሜትር ቢበልጠው ነው::
አገራችን በሞሶሎኒ ወታደሮች ስትወረር ይሄ ሰውየ ባርበኝነት ተሰማርቶ፤በጀግንነት ተዋግቶ ተማርኮ በስቅላት ተገድሉዋል፤   የጥልያን ወታደሮች ይሄንን ሰውየ ሲገድሉ ሁለት ወንጀል  የሰሩ ይመስለኛል፤  አንደኛው ወንጀል  እናት አገሩን ከመከላከል ውጭ ሌላ በደል የሌለው  አርበኛ መግደላቸው ሲሆን ፤ ሁለተኛው፤  በተፈጥሮ ውስጥ ከስንት አንድ የሚገኝ ድንቅ ፍጡር ማስወገዳቸው ነው::  በነገራችን ላይ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ”  ህይወቴ  እና የኢትዮጵያ ርምጃ” በተባለው መፅሀፋቸው ውስጥ፤  ይህን መንዲስ   በሁለት አንቀጾች ሲዘክሩት ስሙን አልመዘገቡልንም ::
ባገራችን “ረጅም ሰው ለጦር ፤አጭር ሰው ለምክር “ የሚል አባባል አለ፤ ይህን አባባል ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የፈጠሩት አጭር ሊቃውንት ይመስሉኛል፤ እነ አጭሬ ፤ጦር  ሲመጣ ረጅሞችን ለመከራ   ያጋፍጡና ምክራቸውን ተሸክመው  ላጥ ይላሉ፤ረጃጅሞች ዘር ሳይተኩ ያልፋሉ፤ዘመናይት ኢትዮጵያ በአጫጭር ሰዎች የተሞላችው አለምክንያት አይደለም ለማለት ነው፤
Filed in: Amharic