>

ባለሥልጣኖች ለምን ወደ ፕሮቴስታንትነት ፈለሱ? (መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው)

ባለሥልጣኖች ለምን ወደ ፕሮቴስታንትነት ፈለሱ?
መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው
 “ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት መለስ ዜናዊ ሃይማኖትን በተመለከተ አንድ ጽሑፍ ያዘጋጅና በጣም ታማኝ የሚባሉ ባለሥልጣኖች ብቻ ማታ ማታ ቤተ መንግሥት ተሰብስበው እንዲወያዩበት ያደርጋል።  “ኢትዮጵያን እኛ እንደ ፈለግናት ዓይነት ለማድረግ የግድ እምነት አልባ ትውልድ ማፍራት አለብን!!!” የሚል ነበር። 
የምእመናን ፍልሰት ለምን እንዳጋጠመ የተለየዩ ምክንያቶችን መደርደር ቢቻልም የባለሥልጣኖቹ ትንሽ ለየት ይላል። የፖለቲካ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ወደ ፕሮቴስታንትነት መፍለስ ከጀመሩ እጅግ ሰነባብተዋል። ነጭ የፕሮቴስታንት ፓስተሮች በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ በነ አባ ዱላ ላይ እጃቸውን ጭነው ሲጸልዩ በገሀድ አይተናል። በኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጊዜ ከአንድ አፍሪካ ሀገር ሐሰተኛ ነቢይ አስመጥተው በቤተ መንግሥቱ ማጸለያቸውን ሰምተን እንደ ዋዛ አልፈናል። በዩኒቨርስቲዎቻችን ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በጾም ወራት ሥጋ ካልበላችሁ ተብለው ሲገደዱ ሰምተን አይተን ለአንድ ሳምንት ተንጫጭተን ዝም ብለናል። ለሃያ ስምንት ዓመታት በዓለ መስቀል እና በዓለ ጥምቀት እናከብርባቸው የነበሩ ቦታዎቻችን በጉልበት ሲነጠቁ ሰሚ የሌለው ጩኽት ጮኸናል። አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፥ ካህናት እና ምእመናን ሲታረዱ እያየን እርር ድብን ብለን ቀርተናል። ያለንበት ዘመን፦ ዘመነ ዮዲት ጉዲት፣ ዘመነ ግራኝ መሐመድ፣ ዘመነ ፋሽስት ኢጣልያ፣ ዘመነ ሱስንዮስ ሆኖብናል።
ይህ ሁሉ ለምን ሆነ? ጩኸታችንስ ለምን የቁራ ጩኽት ሆነ?
ደማችንስ ለምን ደመ ከልብ ሆነ? እዚህ የምኖርበት ሀገር ውሻ እንኳ ትልቅ ክብር አለው። ክብርት፥ ልዕልት፥ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በባለ ሥልጣኖች ዘንድ ለምን ክብር አጣች?
እስኪ የሰማሁትን አንድ ታሪክ ልንገራችሁ። ታሪኩን የነገረኝ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አድዋ ተወልዶ ያደገ፥ አምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ የተማረ ባልንጀራዬ ነው። ፍጹም ኢትዮጵያዊ፣ ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ነው። ከተማሪነት ጊዜ ጀምሮ የማኅበረ ቅዱሳንም አባል ነው። የሥጋ ዘመዶቹ ታላላቅ ባለሥልጣኖች ነበሩ።
ነፍሳቸውን ይማረውና ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር  መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ማኅበረ ቅዱሳንን ከእስልምና አክራሪዎች ጋር  በማነጻጸር በፓርላማ ላይ ይከሱታል። በዚህን ጊዜ እስከ ዛሬም ድረስ ባልንጀራዬ የሆነውን ገብረ መድኅንን፦
“ለምንድነው እነዚህ ዘመዶችህ ማኅበረ ቅዱሳንን እንዲህ ንክስ አርገው የያዙት? ማኅበሩ ፖለቲካ ውስጥ እንደማይገባ አንተ ራስህ ምስክር ነህ፤” ብዬ በቀልድ አዋዝቼ ጠየኩት። እር ሱም፦
“ይህንንማ በደንብ አሳምረው ያውቃሉ፥ የተማረውን ትውልድ በኦርቶዶክሳዊነት ያጸና፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከውስጥ እና ከውጭ ጠላት የጠበቀ ማኅበር እንደሆነ ማንም እንዲነግራቸው አይፈልጉም። ራሳቸው በደንብ አጥንተውታል። እኔም ገርሞኝ፦
“ታድያ ችግሩ ምንድነው?” ስል ዳግመኛ ጠየኩት።
ባልንጀራዬም እስከ ዛሬም ድረስ የሚገርመኝን ታሪክ እንደሚከተለው ተረከልኝ። “ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በፊት መለስ ዜናዊ ሃይማኖትን በተመለከተ አንድ ጽሑፍ ያዘጋጅና በጣም ታማኝ የሚባሉ ባለሥልጣኖች ብቻ ማታ ማታ ቤተ መንግሥት ተሰብስበው እንዲወያዩበት ያደርጋል። ለተወሰኑ ወራት እስከ እኵለ ሌሊት እየቆዩ ተጨቃጭቀውበታል። የጽሑፉ መንፈስ፦ “ኢትዮጵያን እኛ እንደ ፈለግናት ዓይነት ለማድረግ የግድ እምነት አልባ ትውልድ ማፍራት አለብን” የሚል ነበር። በማጠቃለያም የተስማሙበት አሳብ፦ “እምነቶችን ሁሉ ማጥፋት ቢያቅተን መቼም ቢሆን ከኦርቶዶክስ ፕሮቴስታንት ይሻለናል። ስለዚህ ትውልዱን በፕሮቴስታንትዝም ማደንዘዝ አለብን የሚል ነበር። ስለዚህ ኦርቶዶክስን ለማዳ ከም ማኅበረ ቅዱሳንን አስቀድሞ መምታት የሚለው የመጀመሪያ ስልታቸው ነው። ወደ ተግባር ሊገቡ ሲሉ የባድመ ጦርነት ፈነዳ። ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ ሕወሓት ለሁለት ተሰነጠቀ። እስኪረጋጉም ትንሽ ጊዜ ወሰደባቸው።” አለኝ።
እንግዲህ ለዚህ ነው፣ ኦርቶዶክስ እንዲጠፋ ፕሮቴታንቲዝም እንዲስፋፋ በገሃድ ሳይሆን በስውር የታወጀብን። ለዚህ ነው አብዛኛው ባለ ሥልጣን ወደ ፕሮቴስታንት የፈለሰው። ለዚህ ነው ተሀድሶ መናፍቃንን ፈትተው የለቀቁብን። ለዚህ ነው ሐሰተኞች ነቢያትን እንደ እንጉዳይ ያፈሉብን። ለዚህ ነው አብያተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉብን፥ ካህናትና ምእመናን እየታረዱብን ዝም በሉ የሚሉን። በአብዛኛው ክልል ባለ ሥል ጣን የሚሆነው ፕሮቴስታንት ነው። ኦርቶዶክሱ ሠርቶ የሚበላው የሚያመልከውም በሰቀቀን ነው። በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀለው ኦርቶዶክስ ነው። ሀብቷ እና ንብረቷም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በሰገሰጓቸው ካድሬዎች እንዲመዘበር አድርገዋል።
የተለያየ ቋንቋ የምትናገሩ ኦርቶዶክሳውያን እባካችሁን ከዘር ከረጢት ውስጥ ውጡና በቅድሚያ ቤተ ክርስቲያናችሁን አድኑ። ጌታ በወንጌል፦”አስቀድማችሁ መንግሥቱን እና ጽድቁን ፈልጉ፤” ያለውን አትርሱ። መንግሥቱን የተባለ ሃይማኖት ነው፥ ጽድቁን የተባለ ደግሞ ምግባር ነው። እግዚአብሔር ሀገራችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፥ አሜን።
Filed in: Amharic