>

ፀብ አጫሪ የተስፋፊነት የቁም ቅዥት በጊዜ ይቁም!! (ሙክታር ኡስማን)

ፀብ አጫሪ የተስፋፊነት የቁም ቅዥት በጊዜ ይቁም!!
ሙክታር ኡስማን
ይህ የአዲስ አበባ የኢሬቻ ሩጫ ሜዳልያ እጅግ ፀብ አጫሪ ነው። በሶማሌ ክልልና በኦሮሚያ ክልል መካከል ሁለት ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የድንበር ወሰን አለ። በሁሉም ቦታ ሊባል በሚያስችል መልኩ ያልረገበ የድንበር ይገባኛል ንትርክ አለ። ይህ ንትርክ በእንደ ሙስጠፌ አይነት የበሰለ መሪ እንዲረጋጋ ሆኖ ዛሬ ያለውን የሁለቱ ህዝቦች ሰላም ለመጠበቅ አስችሏል።
ነገርግን ይህ ሜዳሊያ የኦነግ ማፕን የያዘና መሬት ላይ ቢወርድ ከብዙ ህዝቦች ጋር የሚያጋጭ ፀብ ያለሽ በዳቦ አይነት ተንኳሽ ነው። ሶማሌዎች በአሁኑ የክልሎች አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያስተዳድሩት ቦታ መሆኑ እየታወቀ በድፍረትና በማናለብኝነት ለኦሮሚያ ተካልሎ ይገኛል። የድንበር ግጭቱን በመላ ተይዞ ሀገር በተረጋጋበት ወቅት እንዲህ መተንኮስ ፍፁም ከኦሮሚያ አመራር እና ከኢቨንቱ አዘጋጆች የማይጠበቅ ነው።
ይህ ሜዳልያ ከስርጭት ታግዶ ያሳተመው አካል ይቅርታ መጠየቅ አለበት። የኦሮሚያ ክልልም ከዚህ ፀብ አጫሪ ነገሮች በመቆጠብ በሁለቱ ክልሎች መካከል የነበረውን እና በይደር የቆየውን ስሱ ጉዳይ በመነካካት ለሌላ ግጭት ሁለቱን ህዝቦች መዳረግ የለበትም።
በኢህአዴግ ዘመን የተሰመረው የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል ድንበር እጅግ አወዛጋቢ ለአስራምናምን አመታት ካጨቃጨቀ በሃላ በሪፍረንደም (በነገራችን ላይ ሂደቱም ውጤቱን ብልሹ ነበር፣ ጥናት ሰርቼበታለሁ) የተወሰነ ነው። ከዚያም ሳይከለል አጨቃጫቆ በሁሉ (ከሞያሌ ደቡብ ጥግ እስከ አዋሽ ጫፍ ሚኤሶ) ቦታዎች ከጥግ አስከጥግ አሁንም አሉ። ይህ ባለበት ሁኔታ እንዲህ አይነት የኦነግ የትግል ዘመንን ካርታ አሁን ቤተመንግስት የገባ አካል ሲመዘው እንዲሁ እንደቀላሉ መታየት የለበትም። ለከፋ ደም መፋሰስና ለማያባራ ግጭት ይዳርጋል።
በሶማሌ በኩል ያለውን አነሳሁት እንጂ ወደ ሰሜንም፣ ወደ ምዕራብም የተስፋፊነት ምኞትን በይፋ የሚያንፀባርቅ ካርታ በመሆኑ በፍጥነት ሊታገድ ይገባል።
“ኦነግ እንዳሻው ካራታ እየሰራ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየተጠቀመበት ያለው ህወሀት እና ራሱ ኦነግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያለ ይሁኝታ በጫኑት ህገመንግስት እንኳ እውቅና የሌለው ግልፅ ወረራ የአማራው፣ የሱማሌ፣ የሃድያ፣  ከምባታ፣ ጉራጌ፣ ጋፋትና የጋሞ መሬቶችን ወደ ኦሮሚያ በማካለል በሃገር ላይ ሃገር የመመስረት ቀቢጸ ከንቱ ቅዥት በአራቱም አቅጣጫ በሚነሳ የተቀናጀ ኢትዮጵያዊ ትግል በጊዜ ሊመክን ይገባል፡
Filed in: Amharic