>

ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ችግሮች እና የልሂቃን ክፉ እሳቤዎች!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ችግሮች እና የልሂቃን ክፉ እሳቤዎች!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
* መቼ ይሆን ሸክማችን ቀለል ብሎን ዘመን የምንሻገረው?
በአያቶቹ ችግር የሚማቅቅ ትውልድ ካለ እሱ ከለውጥ የራቀ እና ከሳይንሳዊ እውቀት የተጣላ የስልጣኔ ድኩማን ነው። በሰለጠነው አለም በአያቶቹ አይደለም በአባት እና በእናቱ ወይም በታላላቆቹ ችግር የሚማቅቅ ሰው የለም!!!
እኛ ዘመንን፣ ችግሮቻችን ደግሞ እኛን እየተከተሉ የአብሮነት ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። ዘመን ሲታደስ የማይታደሱት ክፉ እሳቤዎቻችን አብረውን ከአንድ ዘመን ወደ ሌላ ዘመን እላያችን ላይ እየተንጠላጠሉ ተሻግረው እድሜያችንን እድሜያቸው አድርገው አብረውን ይኖራሉ። አንዳንዴም የእኛ እድሜም ሲያበቃም እነሱ የልጅ ልጆቻችንን ዘመን እና እድሜ ዘመናቸው አድርገው እንደ ውርስ ትውልድ እየተሻገሩ አብረውን ይዘልቃሉ።
እኛም የወላጆቻችንን ብቻ ሳይሆን የአያቶቻችንን ችግሮች እንኖራቸዋለን። ቅም ቅም አያቶቻችን በሬ ጠምደው በባዶ እግራቸው ያርሱ ነበር። ዛሬም የልጅ ልጆቻቸው በተመሳሳይ መልኩ በሬ ጠምደው እና በባዶ እግሮቻቸው ሆነው እሾህና ጋሬጣ እየወጋቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ያርሳሉ። ትላንት ሴት አያቶቻችን ቅጠል ለቅመው፣ በጭስ ታፍነው እንጀራ እየጋገሩ እና ሽሮ አንተክትከው ያበሉን ነበር። ዛሬም የልጅ ልጆቻቸው ያንኑ ህይወት ይኖሩታል። በሌሎች ህይወታችንም እንዲሁ ነን። ትላንትን ዛሬ አድርገን የምንኖር ጉዶች። ዛሬያችን ነገን እንዲያጨልም እንቅልፍ አጥተን የምናድር ልዩ ፍጡሮች።
የአያት፣ ቅድመ አያቶቻንን እድሜ እና ጉልበት እንክት አድርገው የበሉ ችግሮች ዛሬም የእኛን እድሜ እያገባደዱና በልጅ ልጆቻችን እድሜ እየቋመጡ አዲስ ዘመን አብረውን ተሻግረዋል። በአያቶቹ ችግር የሚማቅቅ ትውልድ ካለ እሱ ከለውጥ የራቀ እና ከሳይንሳዊ እውቀት የተጣላ የስልጣኔ ድኩማን ነው። በሰለጠነው አለም በአያቶቹ አይደለም በአባት እና በእናቱ ወይም በታላላቆቹ ችግር የሚማቅቅ ሰው የለም። በካቻምና ችግር ዛሬ የሚያለቅሰ ማህበረሰብ እንደኛ ገልቱ ካልሆነ በቀር የለም። ትላንት ችግር የነበሩ ነገሮች ሁሉ በአዳዲስ መፍትሔዎች ተውጠው እድሜያቸው ባጭሩ ይቀጫል። ዘመን የሚሻገሩ ችግሮች የሏቸውም። ትምህርታቸው፣ ጥናት እና ምርምራቸው፣ ፖለቲካቸው፣ ኢኮኖሚያቸው፣ ማህበራዊ ትስስራቸው እና ሌሎች መስተጋብሮቻቸው ሁሉ መፍትሔ ተኮር ናቸው።
በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ የምዕራብ አገራት የእድገት ጣራውን ስለነኩ እና ካሉበት በላይ ወደየትም ሊያድጉ ስለማይችሉ አብዛኛዎቹ የአዳዲስ ፈጠራዎቻቸው ግኝቶች ያተኮሩት ሕይወትን የበለጠ ቀላል እና ምቹ ማድረግ ላይ ነው። የሚጎረብጠውን ማቅናት፣ የሚሻክረውን ማለስለስ፣ የሚያዳልጠውን መገደቢያ ማበጀት፣ የሚከብደውን ለሸክም ማቅለል፣ የሚዘገየውን እንዲፈጥን ማድረግ፣ የሚጎመዝዘውን እንዲጣፍጥ ማድረግ፤ ባጭሩ ለሕዝባቸው የሚመቹ ነገሮችን ማበጀት ላይ ነው ጊዜያቸውን የሚያጠፉት። የዛሬ 20 ዓመት በፊት ወገባችን ላይ ሻጥ እናረጋቸው የነበሩ የሞባይል ቀፎዎች ዛሬ በምን መጠን እና ቅርጽ ላይ እንዳሉ ማየት በቂ ነው። ለችግሮቻቸው ሁሉ መፍትሔ የሚያፈልቁት በጥናት እና በምርምር ላይ ተመስርተው ነው። እንደኛ በደመ ነፍስ አይኖሩም። ስለሆነም አዳዲስ ችግሮች ይከሰታሉ እንጂ ካቻምና የኖሩበትን እና የተቸገሩበትን ችግር አዝለው ዘመን አይሻገሩም። እኛ ዘመን ስንሻገር አብሮ አደግ ችግሮቻንን በጀርባችን አዝለን እና ከፊታችን የሚጠብቁንን ችግሮች ለማቀፍ እጆቻችንን ወደፊት ዘርግተን ነው።
እኛ ሸክማችን ከተራራ የገዘፈ እና ትላንትን በዛሬ ውስጥ የምንኖር ዘመንተኞች ነን። ከዛም አልፈን የተወለዱትን እና ገና ያልተወለዱትን ልጆቻችንን እድሜ እንክት አድርገው የሚበሉ እና ነገን የሚያጨልሙ ችግሮችን እየፈለፈልን ከዘመን ዘመን የምንሻገር ጉዶች።
መቼ ይሆን ከቅድም አያቶቻችን ችግር የምንፋታው? መቼ ይሆን ከአያቶቻችን እና ከወላጆቻችን ችግር ተላቀን ሸክማችንን አራግፈን ዘመን የምንሻገረው? መቼ ይሆን የትላንት ችግሮቻችንን ለትላንት ትተን ከአዳዲስ መፍትሔ ጋር አብረን የምንዘምነው? መቼ ይሆን የልጆቻችንን ተስፋ ሊያጨልሙ እና እድሜያቸውን ሊያቀነጭሩ የሚችሉ የእኛ የሆኑ ችግሮችን በእኛ እድሜ እንዲነጥፉ መፍትሔ አፍላቂዎች የምንሆነው? መቼ ይሆን ለውይይት፣ ለእውቀት፣ ለምርምር፣ ለሥልጣኔ፣ ለግብረገብ፣ ለመርህ እና ለሞራላዊ ልዕልና የምንሸነፈው? መቼ ይሆን ሸክማችን ቀለል ብሎን ከዘመን ዘመን የምንሻገረው፤ ትውልድ የምናሻግረው?
እስቲ ማን ይሙት እንደኛ ሸክሙ የከበደ ማህበረሰብ አና አገር ከወዴት አለ? የዛሬ አርባ እና አምሳ አመት አንድ ትውልድ በማቀቀበት እና በተላለቀበት ችግር ዛሬም አገሪቷን የደም መሬት ለማድረግ የሚዛዛት ሕዝብ ከወደትስ አለ? የእኛን ሸክም የሚያከብደው ዛሬ ላይ በብዙ ችግሮ መተብተባችን ብቻኮ አይደለም። ችግሮቻችንን ልንፈታበት የሚያስችሉ መላዎች እና እቅዶቹ በጋራ ሆነን ከማፈላለግ ይልቅ ዛሬም አዳዲስ ችግሮች የምንፈበርክ መሆናችን ነው። ለ27 ዓመታት የተጣባን አግላይ እና ብሔር ተኮር ፖለቲካ ካደረሰብን የከፋ ጉዳት ሳናገግም ዛሬ ደግሞ በኃይማኖት እና ሌሎች የልዩነት አጥሮች ተከልለን ቅልቁል ተያይዘን ልንወርድ ማዶ እና ማዶ ሆነን አዲሱን ዘመኑን በዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ቁጣ እና የመጠፋፋት ቀረርቶ እያሰማን መቀበላች ነው።
ዛሬም ከነቁርሿችን፣ ከነቁስላችን፣ ከነክፋታችን፣ ከነመድሏችን፣ ከነመሰሪነታችን፣ ከነተንኳሽነታችን እንኳን ከዘመን ዘመን አደረሳችሁ እየተባባልን ከአሮጌ አመት ወደ አዲስ ጎዞ ጀምረናል። ዛሬ ላይ ሆኖ መጻዒው የአገራችን ሁኔታ የማያሳስበው፣ መስከረም ሲጠባ ምን ሊፈጠር ይችላል ብሎ በውስጡ ስጋት የሌለ፣ ይች አገር ወዴት ልታመራ ነው ብሎ ጭንቀት ያልገባው ልበ ደንዳና ሰው ካለ እሱ እድለኛ ነው። አንድም በጊዜ አብዷል፣ አለያም በራሱ የምናብ ደሴት ውስጥ የሚኖር ሰው ነው ወይም ጆሮውን ቢቆርጡት እንኳን የአገሩን ጉዳይ ጉዳዮ ብሎ የማይከታተል ሰው ነው።
ክፉ እሳቤዎቻችንን አዝለን፣ አሮጌ እና ከትውልድ ትውልድ ሲከባለሉ የመጡ ችግሮቻችንን ከአናታችን በላይ ቆልለን፣ አዳዲስ ችግሮችን ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ችግር ፈጣሪ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን አበራክተን የምንሻገረው ዘመን ምንኛ ከባድ ይሆን?
ሸክማችንን አቅልለን እና ክፉ እሳቤዎቻችንን ከላያችን አራግፈን በቅን መንፈስ ለመወያየት፣ ለችግሮቻችን በጋራ መፍትሔ ለመፈለግ፣ ከአጉል ፍትጊያ እና ጤናማ ካልሆነ የእኔ ልብለጥ ፉክክር ወጥተን፣ የእኔ እና የኬኛ ፖለቲካን አቁመን፣ ከብሔር ጥበት ተላቀን ሰፊዋን ኢትዮጵያን በእውቀት፣ በሥልጣኔ እና በብልጽግና አድምቀን የምንደምቅበት ዘመን ናፈቀኝ። ዘመኑን የከፍታ ዘመን ለማድረግ፤ ከወረዱት ጋር አብረን አንውረድ፤ ከጠበቡት ጋር አብረን አንጥበብ፤ ከደነቆሩት ጋር አብረን አንደንቁር፤ ከከፉት ጋር አብረን አንክፋ። እነዚህን ባህሪዎች እንታገላቸው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Filed in: Amharic