>

የጎሰኝነት መርከባችሁ ከበረዶው ግግር (Iceberg) ጋር ተጋጭቷል!!! (ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ) 

የጎሰኝነት መርከባችሁ ከበረዶው ግግር (Iceberg) ጋር ተጋጭቷል!!!
ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ 
ላለፉት ሁለት አሠርታት በመንግሥትነት የሰለጠነው፣ ላለፉት አርባ ዓመታት በፖለቲካ ማዕከልነት ሲያብጥና ሲኮፈስ የኖረው “በብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች”፣ ቋንቋ፣ ጎሰኝነት ላይ የሚያጠነጥነው ዘረኛ እና ከፋፋይ መርከብ (ideology) የፈራው አልቀረም የማታ ማታ ከቁልል የበረዶ ግግር (Iceberg) ጋር ተጋጭቷል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መስጠሙ አይቀርም።
ጎሰኛው መርከብ የተጋጨው የበረዶ ግግር፣ ከላይ ሲታይ ያለ የማይመስል፣ ከውስጥ ግን በጠንካራና ታላቅ መሠረት ላይ የቆመው የበረዶ ግግር ሌላ ምንም ሳይሆን ኦርቶዶክሳዊነት ነው። ይሰማችኋል? መርከባችሁ ተጋጭቷል፣ ተሰንጥቋል፣ ውኃ ማስገባት ጀምሯል። ካሰባችሁት አያደርሳችሁም። መርከቡ መስጠሙ አይቀሬ ነው። ከማትችሉት ጋር ነው የተጋጫችሁት።
ውድ ኦርቶዶክሳውያን እና በጎ ሕሊና ያላችሁ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ!!!
የሀገራችንን ችግር በደንብ እናውቀዋለን። በቋንቋና በሰፈር የከፋፈለን ጎሰኝነት ነው ፋታ የማይሰጠን ወሳኝ ችግር። እንደፈለገ ብናስታምመው፣ ብናንቆለጳጵሰው፣ እሹሩሩ ብንለውም የልቡ አይደርስም። ደስ የሚለውና የልቡ የሚደርሰው ጭራሽ ከሥር መሠረታችን ነቅሎ ሲጥለን ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ መፍትሔው አምላክን አምኖና በአምላክ ታምኖ ፊትለፊት መግጠም ብቻ ነው።
ጎሰኝነት ያጠፋናል። በቋንቋ መለያየትና መከፋፈል ያጠፋናል። ሃይማኖታችን ከቋንቋ እና ከፖለቲካ ልዩነት በላይ ነው። ስለዚህ ዋነኛውን ችግር በፍፁም ሃይማኖተኝነት እንጋፈጠው። ሃይማኖታችን፣ ሥርዓታችን፣ ቅርሳችን እና ህልውናችን ከምድረ ገጽ እንዳይጠፋ በጽንዓት እንቁም። በፍፁም ኦርቶዶክሳዊነት እና ከጥላቻ በራቀ ክርስቲያናዊ ማንነት የገጠመንን ፈተና እንሻገረዋለን።
+++
*በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም” (የማቴዎስ ወንጌል 16፥18)
 ከጽሑፉ ውስጥ እርስዎ በግልዎ ሊያደርጉት የሚገባዎ ነገር ያለ ከመሰልዎ ከማድረግ ወደኋላ አይበሉ። ያነበቡትን በሚጠቅም መልክ ሥራ ላይ ማዋል ሃይማኖታዊም ሀገራዊም ግዴታ ነው። እግዚአብሔር ይርዳን!!!
Filed in: Amharic