>

የህሊና እስረኛ፤ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ (ገብርዬ) ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (3ኛ) ፖሊስ ጣቢያ የላከው ደብዳቤ

አዲሱ አመት ጭቆና ተወግዶ ዲሞክራሲ የሚነግስበት ሕዝባችንም ባለአገርና ባለመንግስት የሚሆንበት ይሁንልን!!
ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ (ገብርዬ)
አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (3ኛ) ፖሊስ ጣቢያ የህሊና እስረኛ፤
★★★
ለመላው ወገኖቼ እንኳን ለ2012 ዓ.ም አዲስ ዓመት አደረሳችሁ፤ አደረሰን እላለሁ፡፡ የሸኜነው 2011 ዓ.ም እንደ አገርና ሕዝብ በርካታ ክስተቶችን ያስተናገድንበት ነው፡፡ 2011 ዓ.ም በተስፋ ተጀምሮ በመጥፎ የተዘጋ ዓመት ነው፡፡
 የአማራ ሕዝብ የዘመናት ብሶት አምጦ የወለደው አብን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥነ ምህዳር ያደረገው አንፀባራቂ ተጋድሎና ከኢትዮጵያ ውጭ የኖሩ ልዩ ልዩ የፖለቲካ አደረጃጀቶች ወደ አገር ቤት መመለሳቸው በመልካምነት 2011 ዓ.ም ሲታወስበት፤ ውቅያኖስ ተሰጥቷቸው በኩባያ ውኃ የሚነፈርቁ ዋጭ ሰልቃጭ የፖለቲካ ኃይሎች የፈፀሙት አውዳሚ ሥራ (የአዲስ አበባ የመሬት ወረራ፣ የቡራዩ ጭፍጨፋ፣ በጌዲኦ ሕዝብ ላይ የተደረገ አስከፊ ጥቃት፣ የአማራ መፈናቀል፣ የለገጣፎና ሱሉሉታ ቤት ፈረሳ እንዲሁም በምንጃር፣ በአጣዬ፣ ኬሚሴና መተከል በአማራ ላይ የፈፀሟቸው ጥቃቶች ከብዙ በጥቂቶቹ) እንዲሁም ታላላቆቻችንን ያሳጣን የሰኔ 15ቱ ክስተት (ክስተቱን ተከትሎ በአማራ ላይ የተወሰደውን ዘር ተኮር ጥቃት ጨማሮ) ደግሞ አሮጌውን ዓመት በመጥፎነቱ እንዳንዘነጋው ያደርገናል፡፡ በእርግጥ ከ12 ወራት ባነሰ ጊዜ ሶስቴ የካቢኔ ሹም ሽር መደረጉን፣ የሰው ልጅ ከነነፍሱ ተዘቅዝቆ መሰቀሉንና ከነነፍሱም በእሳት እንዲነድ መደረጉን፤ “ወደ ዲሞክራሲ አሻግራችኋለሁ” ያሉን መሪም ሰላማዊ የመብት ታጋዮችን “እስክብሪቶ ጥለን ክላሽ እናነሳለን” ብለው በእውነተኛው የጨቋኝ (tyrant) ማንነታቸው የተገለጡበት ወቅተ መሆኑን በዚሁ በሸኜነው 2011 ዓ.ም የታዘብናቸው ናቸው፡፡
የኮሎኔሉ የፍቅርና የሰላም የተሸመደመደ ስበከት አልቆ በ“ጦርነት እንጀምራለን!!” መተካቱ “ለአገሬ ብሞት አይቆጨኝም” የሚሉት መፈክርም “በእኔ ላይ መጥፎ ከታሰበ በአንድ ቀን መቶ ሺህ ሰው ይታረዳል፤” የሚለው ዛቻቸው “ቅዳሴ ቢያልቅበት፤ ቀረርቶ ሞላበት” የሚለውን ተረት ያስታወሰን ነበር፡፡ በጥቅሉ በ2011 ዓ.ም ማን የፍትኅና የእኩልነት ኃይል፣ ማን ደግሞ የጭቆና ኃይል መሆኑን ያሳየንና ዴሞክራሲም አባወራዋን የለየችበት ዓመት ነበር፡፡ የጭቆና ውታፍ ነቃይ ሆነው አመቱን ያጠናቀቁ አፋሽ አጎንባሽ ኃይሎች ለአቅመ ምሳሌ የደረሰ አንዳች ነገር ባለማድረጋቸው ስለእነሱ የምለው የለኝም፡፡
አዲሱ 2012 ጭቆና ግብዓተ መሬቱ የሚፈፀምበት፤ ዲሞክራሲ፣ ፍትኅና እኩልነት የሚያደላድልበት ዓመት እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡ ለምን ቢባል ለጭቆና ከዚህ በላይ ጊዜ መስጠት አገር ሲፈርስ እንደመተባበር ይሆናል፡፡ ጭቆናን በሰላማዊ ምርጫ አስወግደን ዲሞክራሲን ማንገስ ለዘመናት አገርና መንግስት አልባ የነበረወን ሕዝባችንን ባለአገርና ባለመንግሥት የምናደርግበት ቁልፍ የ2012 ዓ.ም ግባችን መሆኑን፤ ከዚህ የበለጠ ቁልፍ ሥራም እንደማይኖረን መላው ወገናችንን ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ለመላው ኢትዮጵያውያን በተለይም ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት አለኝ፡፡
ትግላችን የፍትኅና እኩልነት፣ ዲሞክራሲን በማንገስ ዜጎች የአገር ባለቤት የሚያደርጋቸውን በመረጡት መንግስት የመተዳደር መብታቸውን ለማጎናፀፍ ነው፡፡ ፍትኅና እኩልነት ብሔር፣ ኃይማኖት ወዘተ የሚለዩ አይደሉም፡፡ ኃቁ ይህ ሆኖ ሳለ በተጨባጭ መረጃ እና እውቀት ስለፍትኅና እኩልነት የምንሞግታቸው የጭቆና ኃይሎች ትግላችንን በማጥላላት የኖሩበትን የጠልነት ትርክት እየዘመሩ መሆናቸውን፤ በዚህም ወጣቶችን በ”የወንዜ ጅብ ይብላኝ” ጎዳና ለመምራት ያላሰለሰ ዘመቻ እያደረጉ መሆናቸውን እናውቃለን፡፡ የዘመን ተጋሪያችሁ የሆንሁ ወንድማችሁ የምነግራችሁ ቢኖር የየትኛውም ሰፈር ጅብ እንዲበላን ጨርሶ መፍቀድ እንደሌለብን ነው፡፡ ፍትኅና እኩልነት ከዲሞክራሲ እንጅ በተምቤን ወይም በእስቴ ክብ፤ በጀልዱ አልያም በሸበዲኖ ጅብ ከመበላት አይገኙም፡፡ እኛ ወጣቶች ውግንናችን ለዲሞክራሲ እንጅ ለጭቆና ሊሆን አይገባም፡፡
መላው የአማራ ሕዝብ በተለይም ወጣቶች የምናደርገው ትግል የሞት ሽረት መሆኑን፤ ዝቅተኛውም ሆነ ከፍተኛው የፖለቲካ ጥያቄያችን የፍትኅና የእኩልነት መሆኑን ላፍታም ሳናዘነጋ ከጭቆና ጋር ለምናደርገው ሰላማዊ ትግል ወትሮ ዝግጁ እንድትሆኑ የአደራ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
በውጭ አገራት ለምትኖሩ ወገኖቼ፤ ባሳለፍነው ዓመት ከጭቆና ጋር ያደረግነውን ትንቅንቅ በድል እንድናገባድድ አበርክቷችሁ ትክ የለሽ ነበር፡፡ በ2012 ዓ.ም ጭቆናን አስወግደን ዲሞክራሲን ለምንገስ በምናደርገው የሞት ሽረት ትግልም የነበራችሁን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ በባለቤትነት ጭምር እንድታጠናክሩ አደራ እላለሁ፡፡
ለማህበረሰብ አንቂዎች፤ ትግላችን ትግላችሁ በድል ዋዜማ እንዲገኝና የጭቆናን መደላድል በመበጣጠስ ረገድ ሚናችሁ አይነተኛ ነበር፡፡ ጭቆናን እወግደን፣ ዲሞክራሲን ሞሽረን፤ ሕዝባችንን በ2013 እንቁጣጣሽ የምንለው ፍትኅና እኩልነትን ዓርማው ያደረገ መንግስት በመስጠት ነው፡፡ ይህን የምንጊዜም ምኞታችንን ዕውን ለማድረግ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ጠንቅቃችሁ ስለምታውቁ እጅጉን እመካባችኋለሁ፡፡ ምርጫና የሕዝብ ቆጠራን በስኬት ማደማደም የትኩረት ነጥባችን መሆኑን ግን ማስታወስ እወዳለሁ፡፡
በሰኔ 15ቱ ክስተት ላለፉ ወንድሞቻችን ቤተሰቦች፡- ይኄ እንቁጣጣሽ ያለውዶቻችሁ የምታሳልፉት የመጀመሪያው እንቁጣጣሽ ነው፡፡ የደረሰባችሁ ኃዘን ምን ያህል መሪር መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ ኃዘናችሁን የበለጠ ያከፋውም ከክስተቱ ጀርባ ያለውን ደባ ለመሸፋፈን ተረኞች እየሄዱበት ያለው የስሁት መንገድ መሆኑ ነው፡፡ የወንድሞቻችንና የውዶቻችሁ ሰማዕትነት ተድበስብሶ እንደማይቀር ግን አረጋግጥላችኋለሁ፤ በኃዘን ድንኳናችን የፖለቲካ ዝሙት የፈፀሙ ሁሉ ፍትኅ አደባባይ ቀርበው የጥፋት ደመወዛቸውን መውሰዳቸው አይቀሬ ነው፡፡
የሰኔ 15ቱን ክስተት ተከትሎ በግፍ ታግታችሁ ላላችሁ የአብን አባላትና አመራሮች፣ የአዴፓ አባላት፣ የባላደራ አመራሮች፣ የአስራት ጋዜጠኞች፣ የአተማ አመራሮች፣ አቃቢያን ሕግና ንፁኃን ወንድሞችና እህቶች፡- በግፍ እገታው እስካሁን ባሣለፍናቸው የግፍ ቀንና ሌሊቶች ሥለሰጣችሁኝ  ክብር፣ ፍቅርና ትምህርት አመሰግናለሁ፡፡ የግፍ እስራችን ለፍትኅና እኩልነት እየከፈልን ያለነው እጅግ ትንሹ ሰማዕትነት መሆኑን ግን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡
ለአብን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎ፤ እንቁጣጣሽ! ፍትኅና እኩልነትን ለማስፈን፣ ዴሞክራሲን ለማንገስ የምናደርገው የሞት ሽረት ትግል የጭቆና ኃይሎችን ከነጋሻ ጃግሬዎቻቸው ምን ያህል ጭንቀት እንደለቀቀባቸው በሚያደርጓቸው የእውር ድንብር እርምጃዎች በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ጨቋኝ የፈሪ ዱላውን በዴሞክራሲ ላይ ባነሳ ጊዜ ወደ ድል የመቃረባችን ምልክቱ ነውና ከወትሮው እጅግ በላቀ ትጋትና ብቃት ጭቆናን ለማስወገድ ማቀዳችንን ማጥበቅ ይኖርብናል፡፡ ፍትኅ የተጠማ፣ እኩልነትንም የተራበ ወገናችንን መከታ ከመሆን የላቀ ክብር፣ ለዴሞክራሲ ሰማዕት ከመሆን የገዘፈ ዋጋ የለምና ወደፊት እንገስግስ፡፡ ወደ ኃላ ማየት የሎጥሚስት እጣን መጋፈጥ  ብቻ ነው፡፡ ኅልውችን ወደፊት በመገስገስ በማሸነፍ ብቻና ብቻ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑና ደግሜ ማስታወስ እፍልጋለሁ፡፡ 2013 የፍትኅ እንቁጣጣሽ፤ የእኩልነት ብስራት ዘመን እንዲሁም የዴሞክራሲ አዲስ ምዕራፍ መክፍቻ ይሆን ዘንድ በ2012 እንደ ንቅናቄ በለየናቸው ምርጫ ን ማሸነፍና ሕዝባችንን በትክክል የማስቆጠር ስትራቴጂካዊ ዓላማዎች ላይ ያለረፍት እንድንተጋ እደራዬን እንቁጣጣሽ እላለሁ፡፡
በመጨርሻም ለእናቴ እማሆዩ የህዝባአለም ዘለቀ፡- እማየ እንደምን አለሽ? እነሆ ወደ አምላክሽ ከሄድሽ ጥቂት ወራት በኃላ የመጀመሪያውን እንቁጣጣሽ ላሳልፍ ነው፡፡ ሁሌም እንደምልሽ ሥለ አውነት፣ ፍትኅና እኩልነት እስከ መጨርሻው ስል ልታገል በጠባኋቸው ጡቶችሽ ቃል እገባልሻለሁ፡፡ ማስተዋልና ጥበብን እንድሰጠኝ፤ ወዳጀ መስለው ከሚያሣድዱኝ የቅርብ ሰዎች እንድጠብቀኝም ፈጣሪያችንን ለምኝልኝ፡፡ ናፍቄሻለሁ እማዬ……. እወድሻለሁ!!
የእናቴ ምትክ የሆንሽው ባለቤቴ እንኳን አደርሰሽ!! የኔ ልባም…. በርችልኝ!
ለጠበቆቻችን፡-ይሄ መልዕክት ከሁሉም የላቀው ነው፡፡ እናንተ ምሳሌ የሚሆን አዲስ ባህል በትግላችን ውስጥ ጨምራችኋልና፡፡ በሙያቹሁ ዋጋን ከፍላቹሁ ጥብቅና የቆማቹሁልን አብነቱ ሁሉም በሙያው ማድርግ የሚገባውን እንዲያበርክት አደራ ነው፡፡ እንቁጣጣሽ!! ውለታችሁ/ትግላቹሁ ታሪካዊ ነው!
 ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ (ገብርዬ)
አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን (3ኛ) ፖሊስ ጣቢያ የህሊና እስረኛ
ፍኖተ አብን
Filed in: Amharic