>

ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ እንስጥ (ከይኄይስ እውነቱ)

ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ እንስጥ
ሀገር – የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን

ከይኄይስ እውነቱ

የኢትዮጵያ ህልውና ከአንድነቷ፣ ነፃነቷ ከነሙሉ ክብሯ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ሕዝባችንም በማኅበራዊ ሕይወቱ ተሳስሮ ባንድ አገር ልጅነት ተሳስቦ እንዲኖር የኢትዮጵያ ቤተክህነትና ቤተመስጂድ ያደረጉት ለዘመናት የዘለቀ ኅብረት ካገራችን አልፎ ዓለም ሁሉ የሚደነቅበት አኩሪ እሤታችን ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆነ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን (ኢኦተቤክ) እና አገራችን ኢትዮጵያን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች አድርጎ ማየት ትክክልም ተገቢም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ አባባል ማስረጃና ድጋፍ ፍለጋና ትንተና ውስጥ መግባት የዛሬ አስተያየቴ ዓለማ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙ ተብሎለታልና፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዐላዊና ነፃ አገር እንዳትቀጥል፣ ሕዝቧም ሉዐላዊነቱ÷አንድነቱና ክብሩ ተጠብቆ እንዳይኖር ከሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች በስተቀር የኢኦተቤክንን እንደ ውቅያኖስ የጠለቀ እንደ ከዋክብት የበዛ አገራዊ ሚና የሚክድ የለም፡፡

የኢኦተቤክ ከፈተና የተለየችበት ጊዜ ባይኖርም ወያኔ (ኢሕአዴግ) የሚባል ነቀርሳ ባገራችን ከተተከለበት ጊዜ ጀምሮ መግለጫና ዕቅድ አዘጋጅቶ ላለፉት 28 ዓመታት በይፋ ለማፍረስ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በመዋቅሯ ውስጥ የራሱን ካድሬዎች፣ መናፍቃንና ዘራፊ ወንበዶችን አሥርጎ በማስገባት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ ገጠር ቤተክርስቲያንና ገዳማት ጭምር ሊቃውንትን አጥፍቷል፣ ካህናትንና ምእመናንን ገድሏል፣ አብያተክርስቲያናትን አቃጥሏል፣ አገራዊ ቅርሶችን ዘርፏል÷አቃጥሏል፣ ለባዕዳን አሳልፎ ሰጥቷል፣ ሙዳየ ምጽዋት ገልብጦ ምእመናን ሳይኖራቸው የሰጡትን ሀብት ጭምር ሙልጭ አድርጎ ዘርፏል፡፡

ቤተክርስቲያንን በማዳከም ኅብረተሰባችንን እንደ ድርና ማግ ያያዙ፣ ህልውናውና አንድነቱ ተጠብቆ ተሳስቦ እንደ አንድ ቤተሰብ እንዲኖረ ያደረጉ መልካም አገራዊ እሤቶች÷ በጎ ምግባራት በእጅጉ ጠፍተው ማኅበራዊ ድቀት እንዲሰፍን አድርጓል፡፡ አሁንም አዲሱ ወያኔና ቀፍቅፎ ያሳደጋቸው፣ የሚከባከባቸውና ከለላ የሚሰጣቸው ጋጠ ወጥ የመንደር ሽብርተኞች/ጉልበተኞች ወያኔ ትግሬ የጀመረውን የጥፋት ፕሮጀክት ከፍጻሜ ለማድረስ በማንአለብኝነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በሬ ካራጁ ጋር ኅብረት ፈጥረው፡፡ የዐቢይ አገዛዝም እነዚህን ዕኩያንና ዕቡያን በተግባርም በዝምታም እየደገፋቸው ይገኛል፡፡ ይህ ድጋፍና ዝምታም በዚህ መሠሪ ዓላማ ውስጥ እጁ የለበትም ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ ዐቢይ ፖለቲከኛ ነው፡፡ ያውም መሠረቱ የዘርና የመንደር የሆነ ፖለቲከኛ፡፡ ያገራችንን ፖለቲካ ደግሞ ቆሻሻ የሚለው ቃል ብቻ አይገልጸውም፡፡ ድንቁርና፣ ሴራ፣ መጠላለፍ፣ ሸፍጥ፣ ውሸት፣ የሥልጣን ሴሰኝነት ወዘተ. መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ ስለሆነም ዐቢይና አገዛዙ ስለ ቤተክርስቲያናችንና እምነታችን ጉዳይ አገዛዙን እንደሚመራ መንግሥት ዐቅም አለኝ ካለ ለካህናት፣ ምእመናንና ቅርሶቿ ጥበቃ ከማድረግ በቀር በየትኛውም መልኩ ጣልቃ እንዲገባብን አንፈልግም፡፡ ለፖለቲካው ዓላማ ማራመጅ እስካልጠቀመው ድረስ የኢኦተቤክንን ይፈልጋታል ብዬም አላምንም፡፡ ስለ ኢኦተቤክ የተናገረው በድርጊት ሲመዘን ዕብለት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የዘር ፖለቲካ የዕብደትና የድንቁርና ፖለቲካ መሆኑ በመንደር መርመጥመጡ፣ በቋንቋ፣ በአጥንት ጕልጥምት ቆጠራ ሳያበቃ፣ የአምልኮ ጉዳይ የሆነው እምነት ላይም ለመግባት ‹ደፋር› ነው፡፡ በመጨረሻም ቤተሰብ አፍርሶ የግለሰብን ሰውነት ያጠፋል፡፡

አሁን የመጨረሻ መጽናኛና መጠጊያችን ላይ ነው የመጣው፡፡ የትእግሥት ማብቂያው ጋር፡፡ ጠያቂ የሌለባቸውና የራሳቸውን መዋቅር ፈጥረው አገራዊ ፖለቲካ ውስጥ የሚጨማለቁትን፣ ከዚያም አልፈው አገርን በሽብር እየናጡ የሚገኙትን ጀዋርና ማኅበሩን ሌሎችንም ተረኞች ነን ባዮች መንደርተኞችን መረን ለቅቆ ሰላማዊ ዜጎችን ማዋከብ የዐቢይ አገዛዝ መገለጫ ከሆነ ከራርሟል፡፡

ይኽች የአገር ዋልታና ማገር የሆነች ተቋም ስትደፈር በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞን ማሰማትና በደም የተጨማለቀ እጃችሁን ከላይዋ ላይ አንሱ ማለት የምእመናን መብታቸው ብቻ ሳይሆን የውዴታ ግዴታቸው ጭምር ነው፡፡ ነባሩም ሆነ አዲሱ ወያኔ በሕግ የበላይነት የማይተዳደሩና መተዳደርም የማይፈልጉ አገዛዞች በመሆናቸው በኢትዮጵያ የሥልጣን መንበር ላይ በጉልበት ከተቀመጡበት ጊዜ ጀምሮ አገርና ሕዝብን ሳይሆን ‹ባለጌ ሥርዓታቸውን› ለማስጠበቅ በዘር ያዋቀሯቸውን የ‹ሕግ አስከባሪ አካላት› ሰላማዊ ሰልፍን ለማፈን እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡ ዐቢይም ሆነ የአገዛዙ መዋቅር በጉልበት ሕግ ካልሆነ በቀር የማናቸውም ሰላማዊ ሰልፍ ከልካይና ፈቃጅ አይደሉም፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ዐቢይ በኢኦተቤክ ጉዳይ አስታራቂ ሸምጋይ ሊሆን አይችልም፡፡ አስቀድሞም አልነበረም፡፡ የፖለቲካ ዕውቅና ለማግኘት ካልሆነ በቀር፡፡ አሁን አጥር ዘለለ፡፡ የግድግዳው ላይ ጽሑፍ በአገዛዙ ላይ ሊታይ የተቃረበ ይመስላል፡፡ በደሎች ተከማችተው የመንግሥትነት ምልክት ከጠፋ ውሎ አድሯል፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ ሰላማዊ ሰልፉ በታቀደው መሠረት እንዲከናወን ቤተክህነቱም ሆነ የሰልፉ አስተባባሪዎች እንዲሁም ምእመናን የማንም ፈቃድ አያስፈልገንም፡፡ ትእይንቱ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ከማሳወቅና ጥበቃ እንዲደረግ ከማድረግ በስተቀር፡፡ ይህንን ለማጨናገፍ ከዐቢይ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የአገዛዙ ባለሥልጣናትና ባለጊዜዎች በ‹ድርድር› ሽፋን ብዙ ዛቻዎችና ማስፈራሪያዎች እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የመጨረሻ አለኝታችንን የሚነጥቅ ኃይል ሲመጣ የሚኖረን አንዱ አማራጭ ቢያንስ ሕይወታችንን መለወጥ ነው፡፡ አለፍ ሲል ደግሞ አፅራረ ቤተክርስቲያንን አቅማችን በፈቀደው ኹሉ መታገል ነው፡፡ ፆምና ጸሎት ትልቁ የጦር መሣሪያችን ቢሆንም በዚህ ብቻ ተወስነን መቀመጥ ያለብን አይመስለኝም፡፡
ለዚህ ሁሉ መደፈር መዋረድ ያበቃን የወያኔ አገዛዝ (ነባሩም ሆነ አዲሱ) መሆኑ የማያጠያይቅ ቢሆንም፤ በመንፈሳዊነት የዛሉ፣ መንፈሳዊነቱ የሌላቸው (ሆዴ ይቅላ ደረቴ ይሙላ ብለው ከዕኩያን ጋር ማኅበር የገቡ)፣ ጥቂት የማይባሉትም ጨርሶም ከተዋሕዶ እምነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው (መዋቅራችንን ተጠቅመው ከውስጥ እየቦረቦሩን ያሉ ነቀዞች) ቅጥረኛ መናፍቃንና የወያኔ ካድሬዎች መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡

ለማንኛውም የህልውና ጉዳይ ቀዳሚ ነውና የውስጣችንን ጉድ በጊዜው ጊዜ እንመለስበታለን፡፡ ከቤ/ክህነቱ ቁንጮ ጀምሮ መሠረታዊ ችግር እንዳለ እናውቃለን፡፡ የቁንጮውንም አቋም በሚገባ እናውቃለን፡፡ ግን ስለዚህ ማውራቱ ጊዜው አይደለም፡፡ በሲኖዶሱም ሆነ በቤተክህነቱ ውስጥ ጥቂት ለቤ/ክ ተቆርቋሪ አባቶቸ ካላችሁና ቤተክርስቲያን ራሷ እና የቤተክርስቲያን ሀብቷ ምእመናን ናቸው ብላችሁ ካመናችሁ (ከእንግዲህ ወዲህ ልጆቻችንን ለነጣቂ ተኩላዎች አንሰጥም የሚል አቋም ከያዛችሁ እና የእውነተኛ እረኛነትን ሚና ለመወጣት ከቆረጣችሁ) ከዐቢይም ሆነ ከአገዛዙ ባለሥልጣናት ጋር በቤተክርስቲያናችን/በእምነታችን ጉዳይ ላይ አትደራደሩ፡፡ አፍኣዊ ይቅርታ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ የሸፍጥ ፖለቲከኞች ልምዳቸው ነው፡፡ ቢያደርገውም እንኳን በርሱ አገዛዝ ጥፋት ካህናትና ምእመናን በመሠዋታቸውና አብያተክርስቲያናት በመቃጠለቸው በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፉን ሊያስቀር አይችልም፡፡ የአባትነት ክብርና ተሰሚነት ይዛችሁ ለመቀጠል ቢያንስ በቤተክርስቲያናችን/በምእመናን ጉዳይ የአገዛዙን ፈቃድ ከመፈጸም እንድትቆጠቡ በልጅነት እንጠይቃችኋለን፡፡

ከእንግዲህ ወዲህ ከመለካውያን (ቤተመንግሥቱ) ጋር ያላችሁን ግንኙነት በሚገባ አስቡበት፡፡ ማንም ቤተመንግሥት በጉልበት የተቀመጠ መምዕላይ፣ ዘረኛና መንደርተኛ ባሰኘው ጊዜ እንደ አህያ ጆሮ አይጎትታችሁ፡፡ አገራዊ ጉዳይ ካለው መጥቶ ያነጋግረችሁ፡፡ ውክልናችሁ የሰማያዊ መንግሥት የነገሥታት ንጉሥ የመድኃኔዓለመ ክርስቶስ ነውና፡፡ ለሰማያዊው መንግሥትና ለሕይወት ባለቤት እንጂ ለቄሣሮች አትንበርከኩ፡፡ ጥሪአችሁንና የምትወክሉትን መንፈሳዊ ጉባኤ አክብሩ፡፡ ራሳችሁን አክብራችሁና አስከብራችሁ እኛ ልጆቻችሁንም የምታስከብሩ ሁኑ፡፡ ያኔ የአባትና የልጅ (የማዘዝና የመታዘዝ) ግንኙነት ይሠምራል፡፡
በጸሎታችን ሰማያዊው መንግሥትን ከመማፀን፤ በምድራዊው ሕግ ደግሞ ለቄሣሮች ተቃውሞአችንን ከማሰማት የሚከለክለን ምድራዊ ኃይል አይኖርም፡፡ ሆኖም የምናመልከው የሥርዓት አምላክ በመሆኑ ሁሉንም በሥርዓት እናድርገው፡፡

የእነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ÷ አቡነ ጴጥሮስ÷የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ፣ የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ÷የቅዱስ አትናቴዎስ÷የአርሴማ ቅድስት ልጆች በኅብረት ተነሱ፡፡ በአምሳለ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሰላምታ የምናቀርብላት፣ እግዚአብሔርን መለመኛና የባሕርይ ስግደት ማቅረቢያ፣ የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ መፈተቻ፣ የኀጢአት ማስተሥሪያ፣ የጸሎት፣ የንጽሕናና የበረከት ቤት የሆነችውን፤ ከልደት እስከ ሞት ወግና ማዕርግ ማያችን፣ በክብር መሸኛችንና መሸጋገሪያችን የሆነችውን እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ይታደግልን ዘንድ የኢትዮጵያን አምላክ እና ወላዲተ አምላክን ይዘን ሠራዊተ ዲያቢሎስን እንፋለመው፡፡

መቃተ ክርስቲያናትን የዘመናት ባለቤት የጊዜያት ጌታ በጎ እንድንሠራበት ዕድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍሥሐ ስለሰጠን እናመስግነዋለን፡፡

ወግ አይቀርምና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ መልካም ዓውደ ዓመት እመኝላችኋለሁ፡፡

Filed in: Amharic