>

ኢትዮጵያ፤ ካልተገራ መንግስታዊ ሥልጣን ወደ ተዳከመ ሥርዓተ መንግስት! ለምን?!? (ያሬድ ሀይለማርያም)

ኢትዮጵያ፤ ካልተገራ መንግስታዊ ሥልጣን ወደ ተዳከመ ሥርዓተ መንግስት! ለምን?!?
ያሬድ ሀይለማርያም
ኢትዮጵያ የጉልበተኞች አገር ነች። ጉልበተኛ ያሻውን የሚያደርግበት፣ ሕግ እና ሞራል ከጉለብተኞች ጫማ ሥር የኖሩባት፣ ሕዝብ ከአንድ ጉልበተኛ ወደ ሌላ ጉልበተኛ ሲገላበጥ የኖረባት ምድር ነች። በአንዳንድ ጽሑፎቼ ላይ እንደገለጽኩት ባለፉት አመታት ከአንድ ጉልበተኛ ቡድን ወደ ሌላ ጉልበተኛ ቡድን ስትሸጋገር የመጣች አገር ዛሬ ደግሞ ወደ መንደር ጉልበተኞች እጅ ልትገባ አፋፍ ላይ ያለች ትመስላለች። መንግስታዊ ጉልበተኞች ጡንቻቸው እስኪዝል ድረስ አገር እና ሕዝብን ካላሸቁ በኋላ ለሌላ ጉልበተኛ አሳልፈው ሲሰጧት የቆየች አገር ዛሬ ያም ብርቆ ሆኖባት ከመንግስታዊ ጉልበተኛም ወርዳ የመንደር ጉልበተኞች እጅ ልትወደቅ እያዘመመች ይመስላል።
በመንግስታዊ ታሪክ ውስጥ በየትም አለም ቢሆን የመንግስት ሥልጣን የሚገለጸው በአራት መንገድ ነው። እነዚህ የሥልጣን መገለጫ መንገዶች በእንግሊዘኛው channels of power አንድ መንግስት የተፈጠረለትን ትክክለኛ አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጣ ያደጉታል። ከእነዚህ አራት መንገዶች የአንዱ መጓደል ወይም የሁሉም መዳከም የአገራዊ መንግስት መዋቅሩን አቅጣጫ ከማሳትም አልፎ አገር በመንደር ጉልበተኞች እጅ እንድትወድቅ ወይም እንድትበታተ ምክንያት ይሆናል። እስቲ እነዚህን የሥልጣን መገለጫዎች አንድ በአንድ እንቃኝ፤
፩ኛ/ የመጀመሪያው የመንግስት ሥልጣን መገለጫ ጡንቻ ወይም ኃይል ነው!!!
ይህ ሀይል የሚገለጸው በመንግስት ሥር በተዋቀሩ የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ የደህንነት እና ሌሎች ሕግ ለማስከበር በተዋቀሩ ኃይሎች ጥንካሬ እና ብቃት ላይ የሚወሰን ነው። ይህ ጉልበት ወይም ሥልጣን መንግስት በሕግ የተሰጠውን ተመጣጣኝ ጉልበት ተጠቅሞ ሕግ እና ሥርዓት የሚያስከብርበት (monopoly on violence) መገለጫ ነው። በአንባገነናዊም ይሁን በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ጡንቻ የአጠቃቀሙ መጠን እና ቦታ ይለያያል እንጂ ዋና ግቡ ሰዎችን በጉልበት አስገድዶ ለአንድ ሕጋዊ ሥርዓት ተገዢ ማድረግ ነው። ትልቁ ችግር የጡንቻው ጥንካሬ ሳይሆን የአጠቃቀሙ መጠን እና አግባብ ነው። እጅግ ጠንካራ ኃይል አደራጅተው ሕዝባቸውን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እና በሕግ አግባብ ብቻ የሚያስተዳድሩ አገሮች አሉ። ባለቻቸው ውሱን አቅም ተጠቅመውም በአለም የገነኑ አፋኝ ሥርዓቶች አሉ። ዋናው ጥያቄ ጡንቻው እማን እጅ ላይ ነው ያለው የሚለው ነው።
፪ኛ/ ሁለተኛው የሥልጣን መገለጫ ማህበረሰቡ የሚገዛበት ወይም የሚተዳደርበት የሞራል፣ የባህል፣ የልማድ፣ የኃይማኖት እና ከትውልድ ትውልድ ሲወራረሱ የሚጡና በትምህርት የተላለፉ እሴቶች እና እነዚህን እሴቶች መሰረት ያደረገ በመንግስት ተረቆና ተዘጋጅቶ የሚወጣ የሕግ ማዕቀፍ (ሕገ መንግስቱን ጨምሮ) ነው። ይህ የሕግ እና የማህበረሰ እሴት ማዕቀፍ በመንግስት እና በሕዝብ እንዲሁም በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ከመደንገግ እና ለመዳኛም መሰረት ከመሆኑ በላይ የመንግስት ጡንቻንም መገደቢያ ልጓም ነው። እነዚህን እሴቶች እና የሕግ ማዕቀፍ ወደ ጎን የገፋ ወይም አሳስቶ ዋጋ ያሳጣ ማህበረሰብ ሁሌም ለአደጋ እና ለጉልበተኞች የተጋለጠ ነው።
፫ኛ/ ሦስተኛው መገለጫ የጋራ እራይ እና የጋራ እጣ ፈንታ ያለው ማህበረሰብ የመፍጠር አቅም ነው። መንግስት ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ የጋራ አገራዊ እራይ ያለው፣ መነሻውን፣ የቆመበትን እና መድረሻውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ማህበረሰብ በትምህርት፣ በውይይት እና በሊሎች የማስገንዘቢያ መንገዶች ተጠቅሞ ለጋራ ጥቅም፣ ለጋራ እድገት እና ብልጽግና አብሮ የሚሰራ ማህበረሰብ መፍጠር መቻል አለበት። ይህ አይነቱ አጋራዊ እይታ እና ብሔራዊ እራይ ሊኖር የሚችለው በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ እቅዶች እና ፍኖተ ካርታዎች ላይ መግባባት ሲኖር ነው። ይህን አይነት ማህበረሰብ እና የፖለቲካ ባህል መፍጠር ያልቻለ ሥርዓት አንድም ሥልጣኑን በጥበብ እና በአግባቡ አልተጠቀመበትም፤ አለያም ያንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም እና ብቃት የለውም። ይህ ደግሞ የተበታተነ እና አገራዊ እራይ የሌለው፣ የሚጋጩ የፖለቲካ ህልሞች እና የሚጋጩ ጥቅሞች ውስጥ ያለ እርስ በርሱ የማይተማመን ማህበረሰብ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።
፬ኛ/ አራተኛው የሥልጣን መገለጫ ለዜጎች አስተዋጽዎ ወይም ድካም ተገቢውን ዋጋ መክፈል (reward) መቻል ነው። ዜጎች በአገራቸው ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው ከሚያደርጉት በርካታ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛው በማህበራዊ ፍትህ ላይ የተመሰረተ ፍትሀዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል መኖሩን ማረጋገጥ እና ዜጎች ባበረከቱን አስተዋጽዎ ልክ ድርሻቸውን እንዲያገኙ ማድረግ የሚችል መንግስታዊ የአሰራር ሥርዓትን መፍጠር መቻል ነው።
ከእነዚህ የአንድ ጠንካራ እና መልካም መንግስት የሥልጣን መገለጫ ከሆኑት ነገሮች መካከል ኢትዮጵያ ባሳለፈችው የረዥም ጊዜ ታሪኳ ውስጥ የተሳካላት እና ሳይስተጓጎች እየተንከባለለ የመጣው የመጀመሪያው የሥልጣን መገለጫ የሆነው ጡንቻ ብቻ ነው። ሊያውም በሕግ፣ በሞራልም ሆነ በሌሎች አገራዊ እሴቶች ያልተገራ እና መረን የለቀቀ የጉልበተኞች ሥልጣን።
የህግ ማዕቀፍ እና ሌሎች እሴቶች ቢኖሩም እነሱን በመጨፍለቅ እና አንዳንዴም እንደ መሳሪያ በመጠቀም ሥልጥን በጡንቻ ብቻ ሲገለጽ ቆይቷል። አሁን ያለንበት የለውጥ ሂደት ከዚህ አዙሪት ውስጥ ያወጣናል የሚል ተስፋ እና ምኞት ብዙዎቻችን ሰንቀን ቆይተናል። በመንግስት ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ለውጡ በተጀመረበት ወቅት ያሳዩት መነቃቃት እና አንዳንድ ጎልተው የታዩ እርምጃዎች ይች አገር ቢዘገይም ወደ ተሳካ የብሄረ መንግስት ልትገባ ነው የሚል ግምት እና እምነ በሕዝብ ዘንድ እንዲፈጠር አድርገው ነበር።
ይሁንና አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መንግስታዊ መዋቅሩ ሲፍረከረክ እና ሕግ የማስፈጸም አቅሙም ሲሳሳ ማየት ጀመርን። እያደርም መንግስትን ሊገዳደሩ የሚችሉ ትናንሽ ጡንቸኞች በየአካባቢ ማቆጥቆጥ ብቻ ሳይሆን የተገኘውን ተስፋም ሊያጨልሙ የሚችሉ እኩይ እርምጃዎችን በተደጋጋሚ መውሰድ መጀመራቸው እና መንግስትም ሊቆጣጠራቸው አለመቻሉ ወይም አለመፈለጉ ሕዝብ ዳግም በአገሩ ጉዳይ ተስፋ እንዲቆርጥ እና ጥልቅ ስጋት ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል።
ለውጡን ተከትሎ እያገገመ የነበረው መንግስታዊ ተቋም ምስረታ እና መነቃቃት ከወዲሁ ትላልቅ ፈተናዎች ከፉቱ ተጋርደዋል። የመንግስትን አቅም እና ብቃት የሚፈታተኑ ሌሎች ትናንሽ ኃይሎች (micropowers) ማቆጥቆጥ ጀምረዋል። መንግስት ያቀደውን እንዳይፈጽም፣ ፖሊሲ እንዳይነድፍ፣ የተነደፉ ፖሊሲዎች እንዳይተገበሩ፣ ሰላም እና ደህነት የማስጠበቅ ሥራውን እንዳያከናውን ማስቆም የሚችሉ እና እራሳቸውን በሚዲያ፣ በደጋፊዎች ወጀብ እና በገንዘብ ያደራጁ የመንግስትን እጅ ጠምዛዥ ኃይሎች ሆነዋል። ለዚህም የፌደራል መንግስቱ ያወጣው የትምህርት ፖሊሲ፣ በአዲስ አበባ የተሰሩ የጋራ መኖሪያ ሕንጻዎች ክፍፍል፣ የአዲስ አበባ የውኃ አቅርቦት እቅድ፣ የክልል እና የወሰን ጥያቄዎች እና ሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶችን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል።
የእነዚህ አይነት ክስተቶች መበራከት የመንግስትን ሥራ ከማደናቀፍ እና የሕዝብን እንቅስቃሴ ከመገደብ ባሻገር ማህበረሰቡ በመንግስታዊ ተቋማቶች ብቃት ላይ እምነት እንዲያጣ ያደርጋል። ጠንካራ እና ገለልተኛ የሆኑ መንግስታዊ ተቋማትም እንዳይፈጠሩ ወይም የተፈጠሩትም በነጻነት እንዳይሰሩ ትልቅ ጫና ይፈጥራል። አሁን ያለው የአብይ አስተዳደር በብዙ መልኩ መንግስታዊ ብቃቱ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል ለማለት ይቻላል።
የሕግ የበላይነትን ማስፈን አቅቶታል፣ ለሕዝብ ይፋ ያደረጋቸውን እቅዶቹን በነዚህ ቡድኖች ዛቻ እና ማስፈራሪያ ሳይውል ሳያድር ሲቀይር እና ሲዋዥቅ ይታያል፣ የተወሰኑ የአገሪቷን ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ማስተዳደር ያልቻለበት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። በተቃራኒው ደግሞ ደካሞችን እና የተቃዎሞ ሃሳብ ያንጸባረቁ ግለሰቦችን በቆየው የማፈኛ ስልት ተጠቅሞ በሽብር ወንጀል ለመክሰስ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ አስሯል።
ከዚህ በኋላ የአብይ አስተዳደር ሁለት እጣ ፈንታዎች ከፊቱ የተደቀኑ ይመስሉኛል፤
፩ኛ/ እነዚህን ትናንሽ ጉልበተኛ የመንደር ኃይሎች ሙሉ በሙሉ በሕግ ጥላ ሥር አድርጎ እና የሕግ የበላይነትን አረጋግጦ ከላይ ያሉትን የአንድ ጥሩ መንግስት የሥልጣን መገለጫ የሆኑ ባህሪያትን አሟልቶ በቃላት የተነገረውን የበለጸገች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የምትመጣበትን መንገድ መያዝ። ለዚህም ለውጡን ለማፋጠን ሊረዱ የሚችሉ ብሔራዊ አድረጃጀቶችን መከተል። ኢህአዴግም ሆነ ኦዴፓ እንደ መሪ ድርጅት ይህን ለውጥ በተፈለገው መንገድ ብቻቸውን የመምራት አቅም የሌላቸው መሆኑን በሚገባ መታዘብ ተችሏል። ይህ ለውጥ ሳይደናቀፍ በፊት ብሔራዊ የለውጥ አንቀሳቃሽ ግብረ ኃይል ማቋቋም የግድ ይላል። ይህን ከዚህ በፊት “አሻጋሪውንም የሚያሻግር የብሔራዊ ሸንጎ ይቋቋም” በሚል ጽሑፌ በዝርዝር ገልጬዋለሁ።
፪ኛ/ የአብይ አስተዳደር በሌለው አቅም እና በሌለው ድርጅታዊ ብቃት ይህን ለውጥ ብቻዮን ይዤ ሁሉም ነገር እኔ በማሰምረው መንገድ ይሔዳል የሚል ከሆነ እራሱንም ማዳን በማይችልበት ሁኔታውስ ከመውደቅም አልፎ አገሪቱን ችግር ውስጥ ይከታል። ከላይ የጠቀስኳቸው ትናንሽ የመንደር ኃይሎች ትላልቅ ጉልበተኞች የማይሆኑበት እድል የለም። እነዚህ ኃይሎች እንደ አንድ ኃይል እየተጠቀሙ ያሉት በራሱ በመስተዳድሩ እና በኢህአዲግ ውስጥ ያሉ ጥቅመኛ ካድሬዎችን ጭምር ስለሆነ ሥርዓቱ ገዝግዞ ለመጣል ሰፊ እድል አላቸው። አዝማሚያውም ከወዲሁ እሚያሳየው ይሄንኑ ነው። እነዚህ ኃይሎች ሙሉ ጉልበት ያገኙ ጊዜ ይህ አመራር እራሱንም ሆነ አገሪቷን ወደ ከፋ ችግር ሊከት ይችላል።
አገር በሕግ እና በተቋማት እንጂ በመሪዎች ቃል ብቻ አይጸናም።  
 
እነዚህን ጥያቄዎች ላንሳና ሃሳቤን ልቋጭ፤
+ ከፊታችን የሚካሄደው ምርጫ ይራዘም ወይም አይራዘም የሚለውን ለመወሰን የሚችለው ማን ነው? አሁን ባለው የፓርቲዎች የተራራቀ ህልም ተስማምተው መወሰን ይችላሉስ ወይ? በታቀደለት ጊዜ ቢካሄድ ለተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ክፍት ያልሆኑ ክልሎች እና አካባቢዎች ላይ ያለው ሁኔታ በምን ሊስተካከል ይችላል? በምርጫ ሕጉ ላይ የተነሱ እና ሚዛን የሚደፉ ቅሬታዎች እንዴት ሊስተናገዱ ነው? ህውሃትን ጨምሮ አንዳንድ ድርጅቶች ለምርጫው ህግ አንገዛም ቢሉ ማዕከላዊ መንግስቱ ምን የማስገደጃ አቅም እና መንገዶች አሉት? የሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ምርጫ ነክ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል።
+ ከብሔር ተኮር ውጥረት ወደ ኃይማኖት ተኮር ግጭት እያመራ ያለውን የፖለቲካ ንቁሪያ በምን መንገድ ማስቆም ይቻላል? መንግስት በጊዜ በቂ ትኩረት ሰጥቶ ሊፈታው ምን ያህል ተዘጋጅቷል? ፍላጎቱስ አለው ወይ? አንዳንድ የመንግስት አካላት ውጥረቱን በማባባስ እረገድ እየተጫወቱ ያለውን እኩይ ተግባር ከቃላት ሽንገላ ባለፈ ለማስቆም ቁርጠኝነቱስ አለ ወይ?
እየሳሳ በመጣው የመንግስት አቅም እና ይህን እንደ እድል እየተጠቀሙ ያሉ ትናንሽ ጉልበተኞች እየተበራከቱ ባለበት ሂኔታ ከላይ አፍጠው የመጡት መሰረታዊ ጥያቄዎች በጋራ ተጣምረው አገሪቱ ወዴት እያመራች መሆኑን መወያየት፣ መላ መሻት እና መመካከር የግድ ይላል።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic