>

በውርደት ዘመን የኩራት ቀን!!! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

በውርደት ዘመን የኩራት ቀን!!!
ሀይለገብርኤል አያሌው
ይህ ትውልድ ምን የሚያኮራ ነገር ሰርቷል በዘመኑ::  ከርሃብ ስደትና የተራዘመ ጭቆና ውጪ ምን አትርፉል:: የትኛው ትውልድ ሊወርሰው የሚችል አሻራስ አለው ? ከአለም በድህነት ውራ  የእህዛብ መጫወቻ የባህር አሳ ቀለብ መሆን ነው ኩራቱ:: ደረቅ ዳቦ እንደ መና ብርቅ መብራትና ውሃ በፈረቃ በሆነበት ሃገር ኩራት ምንድን ነው:: ጥሮ ግሮ የሰራው ቤት ወራሪ ሰፋሪ እየተባለ ጎዳና ላይ መበተኑ የባለግዜ መቀለጃ የተረኞች መለማመጃ መሆን ያኮራ ይሆን?
ኩራታችን ሆኖ የኖረው ትምክህታችን ዛሬም ሆኖ ያለው አባቶቻችን መስፈሪያ የለሽ ዋጋ ከፍለው ያቆዩት ነጻነት : ብራና ፍቀው የጻፉት ታሪክ ዋሻ ፈልፍለው ቋጥኙን ንደው ያነጹት እጹብ ድንቅ ቤተ እምነት ከባዕዳን ተጽዕኖ ሳይበረዝና ሳይከለስ ተጠብቆ የኖረው ባህላችን ካልሆነ ኢትዮጵያዊ ሌላ ምን የሚኮራበት አለው::
ከትላንት ውጪ ዛሬ ምን አለን? ኩራታችን እረግፎ ታሪካችን በረከሰበት ያውም በዚህ ዘመን የኩራት ቀን ብሎ ማሰብ ቀልድ አልያም ጅልነት ነው:: የጥንታዊ ጋርዮሽ አስተሳሰብ በናኘበት በሃገር ውስጥ ሆኖ ሃገር የሚያፈርስ መንጋ በፈለቀበት ለሺህ ዘመናት አብሮ የኖረ ሕዝብ በጥላቻ ተፋጦ በጦርነት ሊጠፋፋ ቋፍ ላይ ባለበት በዚህ ጊዜ የኩራት ቀን ብሎ ማወጅ ታላቅ ስላቅ ነው::
ሰዎች ተራቡ ሲሏት ለምን ኬክ አይበሉም እንዳለችው ቅምጥል ያልበላንን የሚያኩ በቅንጦት አጀንዳ ከመሰረታዊ ሃገራዊ ጉዳይ የሚገፉን ፖለቲከኞች ብሄራዊ የኩራት ቀን ከሚያውጁ በእራሱ ሃገርና ታሪክ መኩራት ያልቻለውን ለቤተመንግት ቅርብ የሆነውን መንጋ እራሱን እንዲያውቅ ቢሰሩ መልካም በሆነ ነበር::
መጽሃፍ ክብራቸው በነውራቸው እንዲል ጥላቻና ስስት በነገሰበት ዘረኝነትና  ጭካኔ በናኘበት : ታሪክ ማጥፉት ቅርስ ማውደም እንደ መልካም በተቆጠረበት  : ሰንደቅን መናቅ የራስ ፊደልን ጠልቶ የውጪ መቀላውጥ ፋሽን በሆነበት በዚህ አስጨናቂ ግዜ ኩራቱ ከየት ነው::
ጠቅላይ ሚኒትሩና የአጀንዳው ቀራጮች ስውር አላማቸውን ለማሳካት የመረጡት አቅጣጫም ከሆነ የሚሳካ አይመስለኝም:: እውነተኛ ከሆኑ የሃገርና የሕዝብ ጉዳይ ካሳሰባቸው ጫፍ የደረሰው የእርስ በእርስ ብሄር ተኮር ፍጥጫ ወደ ለየለት ግጭት ከማምራቱ በፊት ብሄራዊ የእርቅና የሰላም ጉባዔ ቢያስቀደሙ ነገን በተሻለ ተስፉ ማየት በቻልን ነበር::
ዛሬ በውርደት ምድረበዳ ብንወድቅም ቀና ብለን እንድቆም ሕይወታቸውን ለተቤዡን! የባርነት ስሜት የበታችነት ስነልቦና እንዳያጠቃን የሞራል ስንቅና የኩራት ምንጭ ለሆናችሁን ጀግኖች አባቶቻችን አምላክ በሰማይ ይክፈላችሁ : ለዘለዐለም ክብር ይግባችሁ!!!!
Filed in: Amharic