>

ይድረስ ከተከበሩ ዶ/ር አረጋ ይርዳው፤ (ውብሸት ሙላት)

ይድረስ ከተከበሩ ዶ/ር አረጋ ይርዳው፤
ውብሸት ሙላት
ይቺን አስነተኛ ጦማር ወደ እርስዎ ብትደርስ ብዬ መጻፌ፣ የደገኛው ንጉሥ፣ የሚካኤል አሊን (ንጉሠ ወሎ ወትግሬ)፣ የመቶኛ ዓመት ዕለተ እረፍት ምክንያት በማድረግ ነው።
 ንጉሥ ሚካኤል የደሴ ከተማ መሥራች መሆናቸው የታወቀ ነው። ይህንስ ጉዳይ ለእርስዎ ማስታወስ ለቀባሪው እንደማርዳት ነው የሚሆነው። ደግሞም እርስዎስ ደሴ ከተማ፣ ለዚያውም ከንጉሥ ሚካኤል ልጅ፣ ከወ/ሮ ስኂን ትምህርት ቤት አይደል የተማሩት?
ይቺን ጦማር የምጽፍለዎት ግን ከደሴ ከተማ፣ ከፒያሳ እስከ አራዳ ጫፍ ድረስ የሚዘልቀውን ጎዳና (መንገድ) በሚመለከት ነው።
የተከበሩ ዶ/ር አረጋ፥
ይህ መንገድ ንጉሥ ሚካኤል ጎዳና ይባል እንደነበር መቼም የሚያጡት አይመስለኝም። ይህን ጎዳና፣ የንጉሥ ሚካኤልና፣ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ በእርስዎ ስም እንዲጠራ መወሰኑ የታወቀ ነው። “ዶ/ር አረጋ ይርዳው ጎዳና” የሚል ጽሑፍም ከፒያሳ ወደ አራዳ መሄጃ መነሻው ላይ “ታፔላ”ም አለ።
የተከበሩ ዶ/ር አረጋ፥
መቼም የከተማ ተስተዳደሩም ይሁን የያኔው ብአዴን የንጉሥ ሚካኤልን፣ የደሴ ከተማን መሥራች፣ አሻራ ለማጥፋት፣ ከንጉሥ ጋር የተጣሉም የጠሉም ስለሆኑ እንጂ፣ ደሴ ከተማ ላይ ሌላ ጎዳና ጠፍቶ አይደለም የንጉሥ ሚካኤልን ጎዳና “ቀምተው” በእርስዎ ስም መሠየማቸው። ከፒያሳ ወደ መናኸሪያ ቢሉ፤ ከፒያሳ ወደ አገር ግዛት መች ጎዳና ጠፍቶ?
የተከበሩ ዶ/ር አረዳ፥
ይቺን ደብዳቤ ስጽፍልዎት ከማንም የበለጠ ለደሴም ለንጉሥ ሚካኤልም እንደሚቆረቆሩ እርግጠኛ  በመሆን ነው።
ዶ/ር አግጋ፤ ለረጅም ጊዜ በንጉሥ ሚካኤል ስም ይጠራ የነበረውን መንገድ በወቅቱ የነበረው የከተማው አስተድደርም ብአዴንም በእርስዎ ስም መሰየሙ፣ ለተንኮልም እርስዎንም ከሕዝብ ጋር ውጥረትና ቅራኔ ውስጥ ለመክተት ብሎም የወለላውን፣ ደገኛውን፣ ጀግናውን፣ የንጉሥ ሚካኤልን አሻራ ለማጥፋት የተሾረበ ሴራ እንጂ ሌላ አይደለም። ሐውልት እንይዳቆም መደረጉ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አይጠየፍ አዳራሹ ውስጥ ተሳቢ መኪና እያስገቡ ይደረግ የነበረውን የጥፋት ፕሮዤ የሚያውቁት ነው።
እናም፣ ዶክተር የደሴ ከተማ አስተዳደር በእርስዎ ስም የተሠየመውን ጎዳና “ይቀማ” አንልም። ምክንያቱም እርስዎም የእኛው ነዎት።
እንደው ዛሬ ጳጉሜ 3 ቀን ካረፉ መቶ ዓመታቸው ነው። ንጉሥ ሚካኤል ከሰማይ ቤት ሆነው፣ ያችን የቀረችውን ትንሽ መታሰቢያ ጎዳናም ተሰርዛለች፤ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ጎዳና ተብላለች ማለትን ቢያውቁ እርስዎ ምን ይሰማዎት ይሆን? በሆነ መንፈስ፣ ወ/ሮ ስኂን ሚካኤል የአባቷ መታሰቢያ መንገድ ለእርስዎ መሰጠቱን መስማት ብትችል ምን ይሰማዎታል?
እንደው፣ ያችን ጎዳና ለንጉሥ ሚካኤል ይመልሱላቸው። ዶክተር አረጋ የንጉሥ ሚካኤልን መንገድ ይመልሱላቸው።
አክባሪዎ!
ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም.
Filed in: Amharic