>

አድሮ ቃርያ ፖለቲካ፤ የማይበስለው የኦሮሞ ብሄረተኝነትና የደቀነው አደጋ!!! (መስከረም አበራ) 

አድሮ ቃርያ ፖለቲካ፤ 

የማይበስለው የኦሮሞ ብሄረተኝነትና የደቀነው አደጋ!!!

መስከረም አበራ

በሃገራችን የጎሳ ፖለቲካን በማስኬድ በኩል እድሜ ጠገቡ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሲሆን ስኬታማው ደግሞ ህወሃት መራሹ የትግሬ ብሄርተኝነት ነው፡፡ማንኛውም የዘውግ ብሄርተኝነት ትግሉን የሚጀምረው አስቀያሚ የጠላት ምስል በመሳል ነው፡፡ የትግሬ እና የኦሮሞ ብሄርተኞች ደግሞ በያሉበት ሆነው የፖለቲካ ሸራቸውን ወጥረው የጠላት ስዕል ስለው ሲጨርሱ የሚመጣው ምስል ተመሳሳይ ነው:- ሰባት ቀንድ ያለው፣ ጨካኝ እና ጨቋኝ የአማራ ምስል! በዚህ የተነሳ ሁለቱም የአማራ የሆነ ነገርን ሁሉ እኩል ይጠላሉም; ይፈራሉም፡፡ ይህ የኦሮሞ እና የትግሬ የጎሳ ፖለቲከኞች ዞረው ዞረው የሚገጥሙበት ሁነኛ መገናኛቸው ነው፡፡ ለዚህ ነው የኦሮሞ ብሄርተኞች የዛሬ ሳምንት ዘቅዝቆ ገርፎ ጥፍራቸውን ከነቀለው ህወሃት ይልቅ ከዛሬ አንድ መቶ አመት በፊት በኦሮሞ የጦር ጀነራሎች ጭምር ታጅቦ ግዛት ለማስፋፋት የዘመተው ምኒሊክ የበለጠ ክፉ መስሎ የሚታያቸው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኞች በህወሃት ላይ አንጀታቸው አይጠናም፡፡ ተገላቢጦሹ ግን ለህወሃት አይሰራም፡፡ህወሃት ከስልጣን አምሮቱ በተቃራኒ ቆሞ፣ የማይፈልገውን ሲሰራ ላገኘው ኦሮሞ ቀርቶ ትግሬም የሚራራ አንጀት፣ ይቅር የሚል ልብ የለውም፡፡ተገልብጦ መገረፍ ያለበት የበላው በአፉ እስኪመጣ ተዘቅዝቆ ይገረፋል፣ ጥፍሩ መነቀል ያለበት ይነቀላል፣ ጀርባው መተልተል ያለበት ይተለተላል-ህወሃት እንዲህ ነው! ለኦሮሞ ብሄርተኞች ግን ዋናቸው አማራን በመጥላት መተባበሩ ላይ ነው፡፡ ከዛ በመለስ ላለው ነገር ቂም የለም!በማዕከላዊ፣ በዝዋይ፣ በሸዋሮቢ፣ በቂሊንጦ እስርቤት የተደረገባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ አማራን ለማሸመድመድ በሚደረገው ትብብር ያካክሱና የበደል እዳ ይሰርዛሉ፡፡ ከእነሱ ጋር የማይሰረዝ የበደል ዕዳ ያለበት “ባለ ሰባት ቀንዱ አማራ” ብቻ ነው፡፡ ይህ ነገር ለትግራይ መራሹ ባልንጀራቸው ህወሃት አይሰራም፡፡

ህወሃት ዘረፋውን ህጋዊ የሚያደርግበትን ስልጣኑን እስካልተጋፋው ድረስ ሰባት ቀንድ አድርጎት ከኖረው አማራው ጋርም ቢሆን ተባብሮ የበላይነቱን የማፅናቱ ትርጉም ያለው ስራ ላይ ይበረታል፡፡ ለዚህ እማኝ መጥራት ካስፈለገ የህወሃቱ አቶ መለስ ሌላው ቀርቶ ከገዛ የጎሳ መሰሎቻቸው ህወሃቶች ዘንድ የተጋረጠባቸውን የመሰንጠቅ አደጋ ለማምለጥ አማሮቹን ብአዴኖች ብርቱ ምርኩዝ አድርገው ነበር፡፡አቶ መለስ ይህን አደጋ ለማምለጥ በህወሃት ስብሰባ ውስጥ በአዴኖችን እንደ ህወሃት አባል ስብሰባ ውስጥ አስገብተው እስከማስቆጠር የሚደርስ አይን አውጣ አካሄድ ሄደው እንደነበር የስንጥቃቱ ተሸናፊ ቡድን ፊት አውራሪ አቶ ገብሩ አስራት በአንድያ መፅሃፋቸው ገልፀውታል፡፡

አማራን በመጥላቱ ረገድ የኦሮሞ እና የትግሬ ብሄርተኞች ተመሳሳይ ውስጣዊ ባህሪ ቢኖራቸውም ከኦሮሞዎቹ በተለየ የህወሃቶች ፍላጎታቸውን የማስፈፀም ስትራቴጅ ቆሞ ቀር አይደለም፡፡አስፈላጊ ሲሆን ራሱን አማራን ተጠቅመው አማራውን ለመቅበር ይሰራሉ፡፡ ይህ ከትጥቅ ትግሉ ዘመን ጀምሮ ባደረጉት የስትራቴጅ ለውጥ የሚመሳከር ሃቅ ነው፡፡ ትጥቅ ትግሉን ሲጀምሩ ለትግራይ ዝናብ አጠርነት ሳይቀር አማራውን ሊወቅስ የሚቃጣው ማኒፌስቶ ፅፈው፣ አማራ ባለበት ሃገር ትግራይ አትኖርም ብለው ትግራይን ሊገነጥሉ ተዋጉ፡፡ በኋላ ትግራይን በሙሉ ከደርግ ነፃ ምድር አድርገው የመገንጠሉን ነገር ሲያስቡት የትግራይ ብቻ ጌታ ከመሆን ይልቅ የኢትዮጵያ ጌታ ቢሆኑ የተሻለ የጌትነት ትርጉም እንደሚሰጥ ተረድተው ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ሆነ፡፡

ይህ ጉዞ የሚደረገው ደግሞ “የባለ ሰባት ቀንዱን” አማራ ደጃፍ እያለፉ ብቻ መሆኑን ስለተረዱ ተረካቸውን ቀየሩ፡፡ አማራ ሲሉ ድፍን አድርገው ጠላት ያደረጉትን አማራ ሸንሽኖ በተለያየ ቅርጫት የሚያስቀምጥ ተረክ አመጡ፡፡ አዲስ አበባ እስኪደርሱ ሶስት አይነት የአማራ አመዳደብ አመጡ፡፡ አንደኛው ጭቁን አማራ እና የአማራ ገዥ መደብ የሚል ነበር፡፡ ቀጣዩ ደግሞ የአማራ ጨቋኝ መደብ መፀነሻው የሸዋ አማራ እና ሌላው አማራ የሚል ሆነ፡፡ የመጨረሻው ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን የሚቀበል ተራማጅ አማራ (ለህወሃት ጌትነት አጎንባሽ) እና የማይቀበል ትምክህተኛ አማራ ተብሎ ምድር ላይ ሊፈልጉት የሚያስቸግር የአማራነት ቅርጫ በመለስ ዜናዊ ምናባዊ አለም ተሳለ፡፡ ይህ ስዕል ዋነኛ አላማው አማራን ራሱን ተመርኩዞ አማራውን የመቅበር እና በመቃብሩ ላይ የትግሬ ስርወ-መንግስት መመስረት ነው፡፡ በመለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የተደረገው ፖለቲካዊ እርምጃ ሁሉ የሚመሰክረው ይህንኑ ነው፡፡

አማራው ራሱ የተቆፈረትን ጉድጓድ እሰከማያጤን ድረስ ብአዴን በሚባል ፓርቲ ስር ተደራጅቶ ራሱ የሚታረድበትን ቢለዋ ሲስል፣ የሚቀበርበትን ጉርጓድ አርቆ ሲቆፍር የኖረው አስማት በሆነው የህወሃት አደናጋሪ፣ ተለዋዋጭ እና መሰሪ የፖለቲካ ስትራቴጅ ሳቢያ ነው፡፡ ህወሃት በ1968 የፃፈውን ማኒፌስቶ እያነበበ አዲስ አበባ እንደማይደርስ አሳምሮ የሚያውቅ ክሱት ፓርቲ ነው፡፡ ይህን ማኒፌስቶ መሳቢያ ውስጥ አስቀምጦ አማራውን በተመለከተ አቋሙን እየቀያየረ አዲስ አበባ ገባ ማለት ግን በ1968ቱ ማኒፌስቶ ላይ ያስቀመጠው ስለ አማራ ህዝብ ያለው ትክክለኛ አመለካከት ተቀይሯል ማለት አይደለም፡፡ የተቀየረው ክፉ ስራውን የማስፈፀሚያ በጎ ስትራቴጅዎች ማውጣት ብስት ላይ የደረሰው የአቶ መለስ ጭንቅላት ነው፡፡

በመሰረታዊ ክፋቱ የማይቀየረው የአቶ መለስ ጭንቅላት ጠላቱን ወዳጅ አስመስሎ መያዝንም ያውቅበት ነበርና የሚጠላቸው አማሮች ታላቁ መሪ እያሉ አቤት ወዴት ሲሉለት እንዲኖሩ የሚያደርግ ጥራዝ እየፃፈ ይግታቸው ነበር፡፡ ይህ የአቶ መለስ ብልጫ ቢሆንም ከመላው ህወሃት መሰሪነት የሚቀዳ ነገርም አይጠፋውም፡፡ ሌሎቹ የህወሃት መሪዎች እንደ አቶ መለስ ያለ የቆርጦ ቀጥልነት ብቻ ሳይሆን የማንበብ ብልፅግና ባይኖራቸውም ጠላትን ወዳጅ አስመስሎ ማሻሸቱ ላይ ከአቶ መለስ እምብዛም የማይርቅ እኩይነት አያጡም፡፡የህወሃት አመራሮች ማንነት ግን እኩይነት ብቻ አይደለም-የሚፈልጉትን ጠንቅቆ የማወቅ ብቃታቸውን ባንወዳቸውም ልንቀበለው የሚገባ ሃቅ ነው፡፡ ህወሃቶች የሚፈልጉትን ያውቃሉ፤ ለዛም ሳያቋርጡ ጠንክረው ይሰራሉ፡፡ ሰፋ አድርገን እንየው ከተባለ ደግሞ እንደ አንድ ሰው የሚሰራ፣ በጥቅሻ የሚግባባ ካድሬ እና ደጋፊ በክልላቸው መስርተዋል፡፡ ካድሬዎችቻቸውም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው የፓርቲ አመራሮቻቸው የሚያመጡት የስትራቴጅ ለውጥ በድሮ በሬ ለማረስ ካለመቻሉ የተነሳ ለጋራ ግብ ሲሉ ያደረጉት እንደሆነ ለመረዳት እንጨት አይጨርሱም፡፡ ይህ የደጋፊዎቻቸው ነገር የመረዳት ብቃት የህወሃት አመራሮች በስልጣን ሳሉ መንገዳቸውን ቀና አድርጎላቸው ኖሯል፤ አሁን ከስልጣን ከወረዱም አቃፊ ደጋፊ መጠለያ ሆኗቸዋል፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኞችን ግን ከወቅታዊ የፖለቲካ ተለዋዋጮች ጋር የሚሰናሰሉ ትርጉም ሰጭ ስትራቴጅዎችን ነድፎ ወደ ስኬት መንገድ በመጓዙ ብልሃተኝነት ረገድ እንደ ባልንጀሮቻቸው እንደ ህወሃቶች ክሱቶች አይደሉም፡፡ አላማን ጠንቅቆ በማወቅ ረገድም የሚቀራቸው ብዙ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፖለቲካቸው ህወሃት ያየውን ስኬት ማየት አልቻለም፡፡ አላማችን የሚሉት ህወሃትም አላማው እንደሆነ የሚታወቀው የአማራን ሁለመና መፍራት እና ማሳደድ ነው፡፡ ልዩነቱ ህወሃት አማራን የመጥላቱን ስሜት ስልጣን ላይ እንዳይሰነብት ደንቃራ እንዳይፈጥርበት በተቻለ መጠን አምቆት ጥላቻውንም ስልጣኑንም ሳያጣ ረዥም ዘመን መንበር ላይ መቆየት ችሏል፡፡ ህወሃት ይህን የሚያደርገው ከላይ በተጠቀሱት የአማራ ጥላቻ ተረኮቹን ተጠቅሞ አማራውን ራሱን እየሸነሸነ በሚያደናግርበት ስትራቴጅው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ህወሃቶች ከኦሮሞ ብሄርተኞች የሚለዩት ስልጣን ላይ መሆናቸው ረባሽ እንዳይሆኑ የሚከለክል ትልቅ ክብር እንደሆነ ማወቃቸው ነው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኞች ግን ስልጣን ላይ ሆነውም ስልጣን ላይ ሳይወጡ በፊት ስልጣን ፍለጋ ያደርጉት በነበረው መረበሽ የሃገሪቱን ፖለቲካ ማወክ ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ የራሳቸውን ቤተ-መንግስት የመቀመጥ ታላቅነት ላይ ጭቃ እየወረወሩ እንደሆነ የሚገባቸው አይመስልም፡፡ሌላው ኢትዮጵያዊ ከኦሮሞ የሆኑት የለማ ቡድን የሚባሉ ስብስቦች ስልጣን ላይ ሲወጡ በእልልታ የተቀበላቸው የኦሮሞ ብሄርተኞችን የስልጣን አምሮት ብርታት፣ የተበደልን እሪታቸውን ምሬት አስተውሎ በዚህ ሰላም ከመጣ ይሁንላቸው ብሎ እንደሆነ የገባቸው አይመስሉም፡፡ ይህን ያህል ለፖለቲካዊ ስነ-ልቦናቸው ስብራታቸው ታስቦ ወደ መንበረ ስልጣን ለሚያደርጉት ትግል ከመላው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ መሰጠቱን ከበጎ ነገር የወሰዱት አይመስልም፡፡ ካላማረሩ፣ ካላጉረመረሙ ፖለቲካ የሰሩ አይመስላቸውም፡፡ እንደውም ስልጣን ላይ ከመውጣቱ ይልቅ መሬት ላይ ሆነው ከጥንት እስከዛሬ ስልጣን ላይ ያለው አካል በደለን ብለው በማማረሩ ይበልጥ የሚረኩ ይመስላሉ፡፡ ከስልጣን ይልቅ በማማረር የሚደሰት የፖለቲካ ተዋናይ በሃገር ፓርላማ ላይ ከፍተኛ ቁጥር መያዙ ብቻ ሳይሆን የሃገር መንበረ ስልጣን መያዙ የሃገራችን ወቅታዊ ፖለቲካ ትልቅ ፈተና ነው፡፡

በተለያየ ስም ይጠሩ እንጅ ከላይ በተጠቀሰው የማማረር ፖለቲካዊ ስነ-ልቦና ረገድ ሁሉም የኦሮሞ ብሄርተኞች ተመሳሳዮች ናቸው፡፡ ማማረር ከመውደዳቸው የተነሳ ጎሳቸውን ተተግነው ስልጣን ላይ የተቀመጡትን የራሳቸውን ጎሳ ጠ/ሚኒስትር ለአማራው ጥቅም በመስራት አስገራሚ ጥርጣሬ ይጠረጥሯቸዋል፤ የአማራን ፖለቲካዊ ፍላጎት በማስፈፀም ተላላኪነት ያማርሯቸዋል፡፡ አማራው በበኩሉ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ጥቅም ለማስከበር አማራውን የሚጋፉ የኦሮሞ ብሄርተኛ አድርጎ ያክፋባቸውል፡፡ በዚህ መሃል ጠ/ሚኒስትሩም ጠንከር አድርገው የሚይዙት (ይዘውት ከሆነም በቋሚነት የሚገልፁት) አንድ የማይለዋወጥ አቋም ስለሌላቸው ድንግርግሩ ብሷል፡፡ ይህ ድግርግር ለሃገራችን ህልውና እጅግ አስጊ ጉዳይ ስለሆነ እንዴ መጣ ብሎ መነሻውን መመርመሩ ለኢትዮጵያ ብሄርተኛው ጎራ በተለይ እጅግ አስፈላጊ ነው።

የኦሮሞ ብሄርተኞች እርስ በእርስ በመቆራቆስ፣ በመሰነጣጠቅ አና በመጠላለፍ የታወቀ ፖለቲካ የማራመድ የሰነበተ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡ በርካታ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፓርቲዎች ቢኖሩም አንድነት ልዩነታቸው የት ላይ እንደሚያርፍ አይታወቅም፡፡ ይህ ከኦሮሞ ብሄርተኞች ድክመት የተነሳ ብቻ የመጣ ሳይሆን ከራሱ የዘውግ ፖለቲካ ተፈጥሮ የሚነሳ ችግር ነው፡፡ የዘውግ ፖለቲካ ከዘውግ፣ ወደ ጎሳ፣ ከጎሳ ወደ ጎጥ፣ ከጎጥ ወደ ወንዝ በሚደርስ ማለቂያ የሌለው መከፋፈል እና ማነስ እያነሰ የሚሄድ የፖለቲካ አደረጃጀት ነው፡፡ በዚህ ላይ የዘውግ ፖለቲካዊ አደረጃጀትን ክፍፍል ተከትሎ በሁሉም ደረጃ በቋሚነት የሚሰለፍ የሃይማኖት ክፍፍል አለ፡፡ስለዚህ የኦሮሞም ሆነ የሌላ ዘውግ ፖለቲካዊ አደረጃጀት በመበጣጠስ እና በመለያየት ዘይቤ መታጀቡ የማይቀር ሃቅ ነው፡፡

ሆኖም ጥሩ መሪ እና የመነጣጠልን ክፉነት የሚረዳ አስተዋይ ተከታይ ከተገኘ ይህን መለያየት ማስቀረት ባይቻልም መቀነስ ይቻላል፡፡ ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው የህወሃቱ መሪ መለስ ዜናዊ እና የትግራይ ብሄርተኞች ጥሩ ተከታይነት ነው፡፡ ከውጭ ሆነን ለምናየው ከብረት የጠነከረ ህብረት ያለው የሚመስለን ህወሃት አደዋ፣ ሽሬ፣ አክሱም በሚል አውራጃዊነት የተከፋፈለ ድርጅት ነው፡፡ ሆኖም ክፍፍሉ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ጥሩ መሪ እና ጥሩ ተከታይ ተባብረው አፍነው ይዘውታል፡፡ ይህ አይነቱ የጥሩ መሪ እና የጥሩ ተከታይ ግጥምጥሞሽ ለኦሮሞ ብሄርተኞች የገጠመ አይመስልም፡፡ ነገር ግን የመላውን ኢትዮጵያዊ ድጋፍ ያገኘው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከትግሬ ብሄርተኞች ይልቅ ይህን ለማድረግ የሚስችል መልካም እድል ገጥሟቸው ነበር -ትልቁን ስዕል አይተው መጠቀሙን ቢችሉበት ኖሮ!የኦሮሞ ብሄርተኞች ያልቻሉት ነገር ከፖለቲካ ተለዋዋጮች ጋር አብሮ መራመድን ብቻ ሳይሆን አብሮ ለመራመድ ለሚሞክሩ መሪዎቻቸውን ጆሮ መስጠቱን ነው፡፡ የወቅቱ የኦሮሞ ናሽናሊስቶች መሳ የሚሆኑት ህወሃት በ1968 በፃፈው አማራን አይቼ ልጥፋ በሚለው ማኒፌስቶው ኢትዮጵያን ለመምራት ቢሞክር ከሚለው ምናባዊ ሁኔታ ጋር ነው፡፡ ህወሃት ግን ይህን ማኒፌስቶ ከስንት አመት በፊት ወደ መሳቢያ ከቶ ወደ ትልቁ የስልጣን ማማ ለመውጣት እንደገሰገሰ ማሰብ ነው፡፡ ይህን ማሰብ ህወሃት እና በኦሮሞ ናሽናሊስቶች መሃከል ያለውን የብልሃት ርቀት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ህወሃቶች የ1968ቱን ማኒፈስቶ የፃፉትን መሪዎችን ራሳቸውን ተጠቅመው፣ የፓርቲያቸውን የማይሆን አካሄድ መቀየር እና ባለ ድል መሆን ሲችሉ የኦሮሞ ናሽናሊስቶች ግን የለማ ቡድን የሚባለውን አዲስ ትውልድ ተጠቅመው ትልቅ ሃገር ከማስተዳደር ይልቅ ኦሮሚያ ኦሮሚያ በሚያስበልለው የማነስ አባዜ ላይ ቆመው ቀርተዋል፡፡

የለማ ቡድን የሚባለው ስብስብ ከጥቂት አመታት በፊት የአኖሌን የጥላቻ ሃውልት ለማሰራት በየኮሚቴው ተሰማርቶ ተፍ ተፍ ሲል የነበረ፣ ማንኛውም የኦሮሞ ብሄርተኛ ከተቀዳበት የኦነግ እሳቤ ምንጭ የተቀዳ፣ ከመለስ ዜናዊ እግር ስር ቁጭ ብሎ ኢትዮጵያ እንዴት የአማራ ብቻ እንደሆነች የሃሰት ተረክ ሲጋት አንገቱን እየነቀነቀ ሲስማማ የነበረ ቡድን ነው፡፡ ይህ ቡድን የስትራቴጅ ለውጥ ሲያደርግ ጦር የሚሰብቁበት የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደሚያስቡት እርሾው የሆነውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት አለቅልቆ ደፍቶ ሲጠላው የኖረውን አማራ ብሄርተኝነትን እንደመንፈስ አስገብቶ፤ ለአማራ ጥቅም ሊሰራ አይደለም፡፡ በጎሳው ስልጣን ላይ የወጣ የኦሮሞ ብሄርተኛ ለአማራ ጥቅም ይሰራል ብሎ የማሰቡ ገራሚ አስተሳሰብ እንዴት ብሎ ወደ አእምሮ ጓዳ ሊመጣ እንደቻለ የሚደንቅ ነው፡፡ ይህን ግራ የተጋባ እሳቤ ያሰበው የኦሮሞ ብሄርተኛ በቀላሉ ሊያነሳው የሚገባው ጥያቄ ሌላ መሆን ነበረበት፡፡ይሄውም ትናንት የአኖሌ ሃውልትን ያሰሩ ሰዎች ዛሬ እንዴት እንዲህ ያለ የስትራቴጅ ለውጥ ሊያመጡ ቻሉ የሚል ቢሆን ወደ እውነታው የሚያደርሳቸው መንገድ ይሆን ነበር፡፡ በለማ ቡድን የሚመራው የኦሮሞ ብሄርተኛ የስትራቴጅ ለውጥ ማድረጉ ማንኛውንም ዘር በጥላቻ እያዩ ወደ ስልጣን መጠጋት መጨረሻው እንደ ህወሃት እየለፈለፉ መሞት እንደሆነ ስለሚያውቅ የተሻለ መንገድ መከተሉ ነበር፡፡ ይህ ማለት ስትራቴጅ ለወጥን ባዮቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች (የለማ ቡድን) የቀደመ የአማራ ጥላቻቸውን በአንድ ጀንበር ጠርገው ጥለው ለአማራ ጥቅም እስከ መቆም በደረሰ ሰማያዊ ፍቅር ውስጥ ወደቁ ማለት አይደለም፡፡ ይልቅስ ህወሃት ያኔ ድሮ እንዳደረገው ወደስልጣን የሚያደርስ ወይም ስልጣን ላይ የሚያሰነብታቸውን የተሻለ መንገድ መከተላቸው ነው፡፡

በተረፈ የፓርቲ ፕሮግራሙን በአማራ ጭራቅነት ምስል የመሰረተ የዘውግ ፓርቲ ይዞት የኖረውን ጥላቻ በስድስት ወር አሽቀንጥሮ ሌላ ይሆናል ማለት ህወሃትም “አማራን አልጠላም ገዥውን መደብ እንጅ” ያለውም እውነት ነበር ማለት ነው፡፡ የህወሃት ገዥ የሆነው “አማራን መርጬ ነው የመጣላው” የሚለው ተረክ እውነት አለመሆኑ የሚመሳከረው አፈር ገፊውን የአማራ ገበሬ ከሃገሪቱ ዳርቻ ሲያሳድድ፣ ሲያፈናቅል እና ሲገድል የመኖሩ ሃቅ ነው፡፡ ኦህዴድም አማራን ጭራቅ አድርጎ ከመሳሉ ስትራቴጅ እልፍ ብለን ከአማራ ፖለቲከኞች ጋር በምንፈጥረው ህብረት ኢትዮጵያን እናድናለን ሲል አማራን በተመለከተ የነበረውን የትናንቱን ዝቅ ሲል የውድድር ከፍ ሲል የጥላቻ ስሜት እርግፍ አድርጎ ትቷል ማለት እንዳልሆነ ማመሳከሪያው ብዙ ቢሆንም በአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ አማራውን ቀዳሚ ባለጋራ አድርጎ የሚሰራው ደባ ነው፡፡ ደባው ሲጋለጥ ደግሞ ትናንት አጋሬ ነው ብሎት የነበረውን ብአዴንን ስሙን እየጠራ በፃፈው ማስፈራሪያ አይሉት መግለጫ ውስጥ ይብራራል፡፡በዚህ መግለጫ ኦዴፓ/ኦህዴድ የአማራው ወኪል ነኝ ባዩን አዴፓ/ኦህዴድን በተመለከተ የቀድሞ እሳቤውን የኦሮሞ ብሄርተኞች በሚያስቡት እና ኦዴፓን የአማራ ጉዳይ አስፈፃሚ አድርገው በሚከሱበት መጠን እንዳልቀየረ የሚያመላክቱ ሃሳቦችን አስቀምጧል፡፡ኦዴፓ/ኦህዴድ በመግለጫው “አዴፓ፣ ብአዴንን ማን የሌላው ብሄር ጠበቃ አደረገህ?”፣ “ድሮ በለመድከው የትምክህት አካሄድ ለመሄድ የምትሞክረው ነገር አያዋጣም”፣ “የአዲስ አበባ ጉዳይ የእኔ ብቻ ጉዳይ ነው አያገባህም” አይነት ግልፅ ሃሳቦችን አስፍሮ ስትራቴጂ እንጂ ማንነቱን እንዳልቀየረ ያመላክታል፡፡

የለማ ቡድን በሚል አዲስ ስትራቴጅ ወደ ስልጣን የመጣው ኦህዴድ/ኦዴፓ ማማረር የሚወዱት የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደሚሉት ልቡ ኦሮሙማን ከድቶ ዘወትር ለሚያባንናቸው የአማራ ጥቅም የሚሰራ እንዳልሆነ ማሳያው ብዙ ነው፡፡ የኦህዴድ ባለስልጣናት የጃዋርን እና የፌስቡክ ሰራዊቱን ፊት እያዩ የተናገሩትን የሚሽሩ መሆናቸው፣ ምርጫውን አስመልክቶ “ባህላችንን የማያከብር ወደ ክልልላችን እንዳይደርስ” እስከማለት የደረሱበት ገራሚ ንግግር፣ በክልላቸው የሰፈሩ የሌላ ጎሳ ተወላጆችን በስመ ህገወጥነት በክረምት ሳይቀር ሲያፈናቅሉ፣ ሰው በተሰበሰበበት ጉባኤ “ማን የኦሮሞ ቤት ይፈርሳል አለና ነው ኦሮሞዎች የሰው ጦርነት የምትዋጉት?” እስከማለት የደረሱበት ሁሉ የኦዴፓ/ኦህዴድ ልብ የሚያወራውን ያህል ከኦነግ አይነት አግላይ ብሄርተኝነት ርቆ እንዳልሄደ ማሳያ ነው፡፡

ለምን ርቆ አልሄደም የሚለው ሊያነጋግር ይችላል፡፡ ምክንያቱም ሁለት አይነት ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛው ራሱ ኦህዴድ/አዴፓ ሲል ማክረሩን ትቼ ለኢትዮጵያም ለኦሮሚያም እሰራለሁ ያለው ቃሉ ህወሃት ለኢትዮጵያ እሰራለሁ እንዳለው በኢትዮጵያ ስም ካልሆነ ለጎሳ መስራት እንደማይቻል ገብቶት፣በአዲስ ስትራቴጅ ማለትም በኢትዮጵያ ስም ለጎሳው ሊሰራ መታጠቁ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ኦዴፓ/ኦህዴድ እውነትም መለወጥ፣ ኢትዮጵያንም ኦሮሚያንም መምራት እንደሚቻል ገብቶት በተቀየረ ማነት ሃገር ሊመራ አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ከተተከሉበት የኦሮሙማ ጥበት ወደ ኢትዮጵያን የማስተዳደር ግዝፈት ፈቀቅ ማለት የማይሆንላቸው የኦሮሞ ብሄርተኞች ውግዘት በፈለገው መንገድ እንዳይራመድ ስለከለከለው እዛው እያዘገመ መቆየትን ዘዴ አድርጎ ይዞት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የኦሮሞ ብሄርተኞች የማይነቃነቅ እና የማይሻሻል የኦሮሙማ እሳቤ ለአዲሱ ኦዴፓ/ኦህዴድ እርምጃ እንቅፋት ብቻ ሳይሆን ነገ የምርጫ ደጀኑ ከሆነው የኦሮሞ ህዝብ ጋርም ሊያቆራርጥ የሚችል ክፉ አደጋ ያዘለ አካሄድ ነው፡፡ ይህን አደጋ በመፍራት ኦዴፓ/ኦህዴድ የሚያስበው እንደ ራሱ ለውጥን የመሻት ዝንባሌ ሆኖ የሚሰራው ግን ከኦነግ በላይ ኦነግ ሆኖ ለመታየት መሰቃየትን ያከለ ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የተቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደናግር ብቻ ሳይሆን በኦህዴድ ስም በጥበቱ እና በጭካኔው በሚያውቀው በኦነግ መንፈስ የመመራት ጥርጣሬ እና ስጋት እያሳደረበት ይገኛል፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የለማ ቡድን የሚባለው ስብስብ በኦህዴድ/ኦዴፓ በኩል ሃገሬን አስመልሳለሁ ያለውን ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ እምነትም ሳያገኝ፤ ኦዴፓ/ኦህዴድ እንደ ኦነግ ካልሆነ ደስ የማይላቸውን የኦሮሞ ብሄርተኞችንም ሳያስደስት ከሁለት ያጣ ሆኖ ይቀራል፡፡ በዚህ መሃል ያለው ትልቁ አደጋ ሃገራችን ወደማትወጣበት የእርስበርስ እልቂት እና መፈራረስ የማምራት እድሏ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ተበጥብጣ እና ፈርሳ ኦሮሚያ እንደ ገነት በሆነ ሰላም መኖር የምትችል የሚመስላቸው የኦሮሞ ብሄርተኞች ደግሞ ይህ የሚያሳስባቸው ነገር አይደለም፡፡ የራሳቸው ጎሳ ሰዎች የፈደራል ስልጣን ላይ ወጥተው የሚያደርጉትን ነገር ትቂት ጊዜ ወስዶ ለማየት ትዕግስት የሌላቸው የኦሮሞ ብሄርተኞች ኦሮሞ ስልጣን በያዘ ዘመን ሃገር ፈረሰ የመባሉ የታሪክ ተወቃሽት አማርኛ በኦሮሚያ ክልል ከሶስተኛ ክፍል ጀምሮ በትምህርትቤቶች ይሰጥ መባሉ የሚያሳስባቸውን ያህል እንኳን ከቁብ የሚያስገቡት ቁምነገር አይመስልም፡፡ እንዲህ ባለው አድሮ ቃሪያ የፖለቲካ አካሄድ ተዋናዮች የገመድ ጉተታ ውስጥ የተሰነቀረው የሃገራችን እጣ ፋንታ ከመቸውም ጊዜ በላይ አሁን አሳሳቢ ነው፡፡

Filed in: Amharic