>

የተዘጋ እስር ቤት ከመጎብኝት የዘጋችሁባቸውን እስረኞች ጎብኙልን!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የተዘጋ እስር ቤት ከመጎብኝት የዘጋችሁባቸውን እስረኞች ጎብኙልን!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የቀድሞውን ማዕከላዊ እስር ቤት በያመቱ የፍትሕ ቀን እያሉ መጎብኘቱ ትርጉም ይኖረው የነበረው አዳዲስ የፖለቲካ እስረኞች በሌሎች እስር ቤቶች ውስጥ ታጉረው እንዲሰቃዩ ባይደረግ ነበር።
ክብርት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ማዕዛ አሸናፊ (#TheFederalSupremeCourtofEthiopia) እባክዎ አዲስ አበባ በሚገኘው የፖሊስ ኮሚሽን ህንጻ ሥር የተሰሩ ቀዝቃዛ የእስረኛ ማጎሪያ ቤቶችን እና በየፖሊስ ጣቢያው ያሉ እስር ቤቶችንም እግረ መንገድዎትን በዚሁ ሳምንት ይጎብኙ። ከቻሉም ጦላይ እና ሰንቀሌ የፖሊስ እና የወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ለወራት ታስረው እየተሰቃዩ ያሉ ወገኖችዎ ፍትሕ አግኝተው እንደሆነ እና የሚገኙበትንም የእስር ሁኔታ ይጎብኙ።
የማዕከላዊ እስር ቤት መዘጋትን የዛሬ አመት እልል ብለን አወድሰናል። በሌሎች እስር ቤቶች ሰዎች እየተሰቃዩ በያመቱ እሱን ብንጎበኝ ፋይዳው ምኑ ላይ ነው? ከመደበኛ ማረሚያ ቤቶች ውጭ ባሉ እስር ቤቶች ውስጥ በተለይም ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች እንግልት እና ለመጥፎ የእስር አያያዝ እየተዳረጉ መሆኑን ብዙዎች እርሶ በሚመሩት ተቋም ስር ባሉ ችሎቶች ጭምር ቀርበው እየተናገሩ ነው።
የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ አጥብቀን እየጠየቅን የእስረኞቹ አያያዝም በአግባቡ ሊፈተሽ እና በሕገ መንግስቱ የተቀመጡ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸውም አበክረን እንጠይቃለን!
ፍትሕ ለግፉአን!!!
Filed in: Amharic