>

ጳጉሜን "የህሊና እስረኞች ሳምንት" ብላችሁ አስቡን! (ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ - ገብርየ)

ጳጉሜን “የህሊና እስረኞች ሳምንት” ብላችሁ አስቡን!
ክርስቲያን ታደለ ፀጋዬ (ገብርየ) 
በረራ ጋዜጣ
* በዓለም የስለላ ታሪክ «እጅግ ቀሽሙ ስለላ» ተብሎ የሚታወስ ይሆናል:: ተጠርጥረን የታሰርነዉ ከሰኔ 15ቱ የወንድሞቻችን ግድያ ጋር በተያያዘ የሚል ሽፋን ተሰጥቶት ብንታሰርም በምርመራ ወቅት ግን፦ «27 ዓመት የት ኖራችሁ ነዉ? አብይን ታደንቁታላችሁ ወይ? አርፋችሁ አትኖሩም ወይ? ፖለቲካ ለእናንተ ምን ያደርግላችኋል ወዘተ…» የሚሉ ናቸዉ::
ይኼን የባለተረኞች ገመና ለመፃፍ የተገደድኩበት በዋናነት ፡- አንድም የጳጉሜን ወር የሰላም ሣምንት በማለት አሥሮ የከፈነዉን ፍትሕ ለመሞሸር ሽር ጉድ የሚለዉን አካል ለመንቀፍ ፤ ሁለትም ለፍትህና እኩልነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ሩጠዉ ያልጠገቡ እምቦቅቅላዎችን ጭምር መሰዋዕትነት ከፍሎ ያስገኘዉን የለዉጥ ጭላንጭል ጩለሌዎች ነጥቀዉ ከመቼዉም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ኅልዉናዉ አደጋ ላይ ለወደቀዉ የአማራ ሕዝብ እየሆነ ስላለዉ ሁሉ መረጃ ለመስጠት ነዉ::
ሁላችሁም እንደምታዉቁት የሰኔ 15ቱን ክስተት ተከትሎ በርካታ ወገኖች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ «ተጠርጥራችኋል» በሚል ሽፋን በገፍና በግፍ ከታገትን እንሆ 2 ወራት አለፉ:: በወንድሞቻችን ግድያ የምንጠረጥራቸዉ ተረኞች ራሳችንን መጠርጠራቸዉ ሳያንስ፣ አሁንም በራሳችን የሃዘን ድንኳን ዉስጥ አማራ ጠልነታቸዉን በለመዱት የአፓርታይድ ጋን ሾመዉ «የፍትህ ጠላ ነዉ» ተጋበዙልን ማለታቸዉ ንትብ ህሊናቸዉን ብቻ ሳይሆን ለሕዝብና ሕዝባዊ ኃላፊነት ያላቸዉን ንቀት የሚያሳይ ነዉ:: ተረኞች ንቃተ ፓለቲካቸዉ የተሻለ የተባሉትን ሁሉ ፤ የአማራን የኅልዉና ትግል የሚመሩ ተቋማትን /አደረጃጀቶችን አመራርና አባላትን ፣ በአማራነታቸዉ አንገት ያልደፉ የጉልበት ሰራተኞችን ጭምር በግፍ ማሰራቸዉ በትረ ስልጣን በጨበጡ ማግስት «የአማራ ብሔርተኝነትን እናጠፋለን» ሲሉ የዛቱትን ለመተግበር ወቅትና አጋጣሚ ተጠቅመዉ በዕቅድ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸዉን ያረጋግጥልናል::
በዚች አጭር ማስታወሻ ልጽፍላችሁ የምፈልገዉ ቁም ነገር ግን የኮለኔል ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር አስሮ የፓለቲካ ስለላ እየሰራብን የመሆኑን ጉዳይ ነዉ:: ምን አልባትም ይኼ ጉዳይ በዓለም የስለላ ታሪክ «እጅግ ቀሽሙ ስለላ» ተብሎ የሚታወስ ይሆናል:: ተጠርጥረን የታሰርነዉ ከሰኔ 15ቱ የወንድሞቻችን ግድያ ጋር በተያያዘ የሚል ሽፋን ተሰጥቶት በምርመራ ወቅት ግን «27 ዓመት የት ኖራችሁ ነዉ? አብይን ታደንቁታላችሁ ወይ? አርፋችሁ አትኖሩም ወይ? ፓለቲካ ለእናንተ ምን ያደርግላችኋል ወዘተ…» የሚሉ ናቸዉ:: «አብንን እናፈርሰዋለን» ያለዉ መርማሪ ፓሊስ ንግግር ግን በናዝሬት የኦዲፓ-አዴፓ የጋራ መድረክ ላይ ኮለኔል ዐቢይ የተናገሩት መሆኑን ለምናዉቅ  እኛ የቀሽሙን ሥለላ ስክሪፕት ደራሲ ያረጋገጠልን ነበር:: አላማዉ የአማራዉ የኅልዉና ትግል ተቋማትን (አብን ፣ አስራት ፣ አተማ ፣ የአማራ ልዩ ኃይል ማፍረስ በሆነዉ ሴራ ኮለኔል ዐቢይ ባወገዙት የሽብርተኝነት አዋጅ መከሰሳችን በርግጥ በበዓለ ሲመታቸዉ ወቅት «ዋናዉ አሸባሪ ራሱ መንግሥት ነዉ» ሲሉ የተደመጡትን ያረጋገጠ ነዉ::
እናም ለኮለኔል ዐቢይ ንገሩልኝ ፣ የልጃቸዉ በግፍ መገደል ሃዘን ሳይበርድላቸዉ የሌላኛዉ ልጃቸዉ ደብዛ መጥፋት ሰቀቀን የሆነባቸዉ እማሆይ ዉብሰፈር አሳየ ያለቅሱብሃል በሉልኝ:: በግፍ በተገደለዉ አባቴ ምትክ እናቴ ወንድም ወይም እህት ትወልድልኛለች ብላ ስትጠባበቅ የነበረችዉ ማህሌት አሳምነዉ እያለቀሰችብዎ ነዉ በሉልኝ:: ማህሌትም ልክ እንደዲቦራ የሚሳሳላት አባት እንደነበራት ንገሩልኝ:: በግፍና ጠፍ ያገትካቸዉ ወገኖች፣ እናቶች፣ ሚስቶችና እህቶች እያለቀሱብዎት ነዉ በሉልኝ:: የኢትዮጵያ እናቶች «ይጸልዩልኛል» ያሏቸዉ የዋህ ልቦች በወይዘሮ ደስታ አሰፋ የተደረገዉን ቢሰሙ ፀጉር ነጭተዉ ያዝኑብዎታል በሉልኝ:: በከንቱ የተቀጩ የወንድሞቻችን ነፍሳትም ወደ ራማ ይጮህብዎታል:: የአማራ ሕዝብስ እንዲጠፋ ስለተፈረደበት ዘር ዝም የሚል ይመስልዎታል?
መዉጫ፡- ስለ ፍትህና እኩልነት የሚታገሉ ወገኖችን በግፍ በማገት ሰላምና እርቅ አይነግስም:: ሰላም ያለፍትህ ከነፍስ የተለየ ስጋ ማለት ነዉ:: ስለሆነም ለፍትህና እኩልነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊያን ፣ ለዴሞክራሲ ኃይሎች በተለይም ለአማራ ሕዝብና ወጣቶች የማስተላልፈዉ መልዕክት ቢኖር በተረኞች እገታ ስር የምንገኝ ወገኖች የሆነብን ሁሉ ስለ ፍትህና እኩልነት በመታገላችን በተለይም የዘር ፍጅት እየተፈጸመበት ስላለዉ አማራ ልሳን በመሆናችን መሆኑን ፣ በዚህ የተነሳም የሚመጣዉን እስር ከጫጉላ ፣ ሰማዕትነትንም ከጽድቅ የምንቆጥር መሆኑን ፣ የሕዝባችንን ህልዉና በማረጋገጥ ማሕበራዊ ፍትሕ የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከመቼዉም ጊዜ በላይ አንድ ልብ መካሪ ፣ አንድ ቃል ነጋሪ መሆን የተገባ መሆኑን ታናሻችሁ የአደራ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ:: ደግሞም እየሆነ ያለዉ ሁሉ የማሸነፋችን ምልክት ፣ የድል ዋዜማ ላይ የመገኘታችን አብሳሪ ነዉ:: ሲመሽ ነገ ጀምበር አትወጣ ይሆን ብየ ተጠራጥሬ እንደማላዉቀዉ ሁሉ የአማራ ትግልም አያሸንፍ ይሆን የሚል ቅንጣት ሥጋት አይገባኝም:: ጀምበርም ትወጣለች ፣ ትግላችንም ያሸንፋል:: ለተረኞችም እዉነተኛ ፍትህ ምን እንደሆነ እንገልጽላቸዋለን:: እስከዚያዉ ግን የ2011 ጳጉሜን «የህሊና እስረኞች ሳምንት» ብላችሁ አስቡን::
Filed in: Amharic