>
5:14 pm - Wednesday April 20, 8574

የሓጂ ጃዋር መሐመድ የመንፈስ ልጅ የሆኑት ቀሲስ በላይ መኮንን ኦሮሞ ወይስ ወላይታ? (አቻምየለህ ታምሩ)

የሓጂ ጃዋር መሐመድ የመንፈስ ልጅ የሆኑት ቀሲስ በላይ መኮንን ኦሮሞ ወይስ ወላይታ?
አቻምየለህ ታምሩ
ቀሲስ በላይ መኮንን በተደጋጋሚ የአቡነ ጴጥሮስ የስጋ ዘመድ እንደሆኑ ሲናገሩ ሰምተናል። ቀሲስ በላይ መኮንን እውነትም የአቡነ ጴጥሮስ የስጋ ዘመድ ከሆኑ ማንነታቸው ኦሮሞ ሳይሆን ወላይታ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ ኦነጋውያን እንደሚሉን ማንነታቸው ኦሮሞ ሳይሆኑ የወላይታ ተወላጅ ነበሩ። ይህንን የአቡነ ጴጥሮስ ማንነት የሚነግሩን  አብሮ አደጋቸው የወላይታ ተወላጁ  አቶ ዋና ዋጌሾ ናቸው። «የትምህርት አባት» በመባል የሚታወቁት   አቶ ዋና ዋጌሾ  በተወለዱ በ108 ዓመታቸው በቅርቡ  ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አቶ ዋና «የታሪክ አብነት ከባለታሪኩ» በሚል በ1998 ዓ.ም. ባሳተሙት መጽሐፍ  አቡነ ጴጥሮስን በግፍ በተገደሉበት ቀን ሳይቀር አግኝተው እንዳናገሯቸው፤ ማንነታቸውም የታሪክ ፀሐፊዎች በተዛባ ትርክት ምክንያት የሌላ ማንነት ለጥፈውባቸው እንደሚገልጿቸው ሳይሆን ወላይታ መሆናቸውን፤  በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በወላይትኛ ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር  ይነጋገሩ እንደነበርና ወላይታ ውስጥ የተወለዱበትን ሥፍራ ጭምር ከእሳቸው አንደበት መስማታቸውን በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።
አቡነ ጴጥሮስ ከወላይታ ወደ ሸዋ የመጡት  የትግሬ ተወላጁን የወላይታውን ንጉሥ ካወ ጦናን  ለማስገበር  የዘመተው የማዕከላዊ መንግሥት ጦር  አንድ  ክፍል የሆነው የሰላሌ ገዢ የነበሩት የራስ ካሳ ዳርጌ ጦር ማርኮ ወደ ሰላሌ ስላመጣቸው ነበር። በወቅቱ ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር  ወደ ሰላሌ የመጡና እዚያው ሰፍረው የቀሩ በርካታ  የወላይታ ተወላጆችም ነበሩ። አቡኑ ግን ሰላሌ ውስጥ ያደጉትና የተማሩት  ፍቼ በሚገኘው የራሳ ካሳ ግቢ ውስጥ  ነበር።
አቶ ዋና በጻፉት ማስታወሻቸው እንደነገሩን ራስ ካሳ ያዳደጓቸውን  አቡነ ጴጥሮስን  ይወዷቸው ስለነበር ሊድሯቸው ቢፈልጉም አቡኑ ግን  ወደ ሃይማኖት በጣም ያዘነበሉ ሰው በመሆናቸው ፍቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም። ራስ ካሳ ይህንን  የአቡነ ጴጥሮስን ፍቃደኛ አለመሆን  ለወቅቱ አልጋ ወራሽ ለራስ ተፈሪም ጭምር  ተነግረው ነበር። ሆኖም ግን አልጋ ወራሹ «ተወው ልመንኩስ ካለ አታስገድደው» ብለው ምላሽ መስጠታቸው ሊመነኩሱ ችለዋል። ቆይተውም ወደ ግብጽ ተልከው ጵጵስናቸውን ተቀብለዋል።
በወላይታ ወላጆች ልጆቻቸው በዐይን በሽታ እንዳይጠቁ   «በቄ» በመባል የሚታወቀውን የባህል ምልክት ያደርጋሉ። በወላይታ ዘንድ «በቄ» የሚባለው  በዐይን ግራና ቀኝ የሚደረገው ምልክት  የመሀል አገር ሰው በተለምዶ የ«የወላይታ ስሙኒ» እያለ የሚጠራው ምልክት ነው። የወላይታ ተወላጁ አቡነ ጴጥሮስም  እንደ ወላይታ ልጅነታቸው በቄ ወይም «የወላይታ ስሙኒ» በዐይናቸው ግራና ቀኝ የነበራቸው ሰው ነበሩ።
እንደሚታወቀስ ጳጳስ አይወልድም፤ ስለሆነም የስጋ ልጅ የለውም። በመሆኑም  አቡነ ጴጥሮስ የስጋ ልጅ የላቸውም። ቀሲስ በላይ መኮንን በተደጋጋሚ እንደነገሩን የአቡነ ጴጥሮስ የስጋ ዘመድ ከሆኑ ሊሆኑ የሚችሉት ትውልዳቸው ወላይታ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ማለት የቀሲስ በላይ መኮንን ወላጆች ከወላይታ ወደ ሸዋ የመጡት አንድም በገብር አልገብርም ዘመቻው  ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር  በራስ ካሳ ጦር   ተማርከው ራሱ ያስተዳደሩበት ወደለበረው ወደ ሰላሌ ተወስደው እንዲሰፍሩ የተደረጉ ናቸው፤ አልያም  በሌላ ጊዜ ከወላይታ፣ ወደ ሰላሌ ሄደው እዚያው ሰላሌ  የቀሩና  ማንነታቸው የቀየሩ ወላይታዎች ናቸው። በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደሰማናቸው  ቀሲስ በላይ የማንነትና ቋንቋ ጉዳይ ያንገበገባቸው ፖለቲከኛ ናቸው። እንዲህ በማንነትና በቋንቋ ፖለቲካ ቱግ ቱግ የሚል የፖለቲካ ሰው መጀመሪያ ራሱን መሆን ይኖርበታል።
ስለዚህ ቀሲስ በላይ እውነተኛ የማንነትና የቋንቋ ተቆርቋሪ ፖለቲከኛ ከሆኑ መጀመሪያ ራሳቸውን ለመሆን  የተጫነባቸውን የኦሮሞ ማንነት አውልቀው ጥለው በስጋ እዛመዳቸዋለሁ የሚሏቸውን  የአቡነ ጴጥሮስን እውነተኛ ነጋዳዊ  ማንነት ወይም የወላይታ ማንነትን መላበስ አለባቸው። ይህን ሳያደርጉ ለቋንቋና ማንነት እቆረቆራለሁ ቢሉ ሆድ ሲያውቅ ዶር ማታ ነው። የአቡነ ጴጥሮስን ማንነት ሳይዙ ወላይታ ለኢትዮጵያ በሰጠቻት ሰማዕት በአቡነ ጴጥሮስ ስም ማጭበርበር አይቻልም!
የቋንቋና የማንነት ጉዳይ የሚያንገበግበው ሰው ስለ ቋንቋና ባሕል መቆርቆሩን የሚያሳየው  ከሁሉ አስቀድሞ የተጫነበትን ባዕድ  ማንነት አውልቆ ጥሎ የራሱን ሲላበስ ብቻ ነው።  ቀሲስ በላይ መኮንንም እንደነገሩን የአቡነ ጴጥሮስ የስጋ ዘመድ መሆኑና የማንነትና ቋንቋ ጉዳይ የሚያንገበግባቸው ከሆነ መጀመሪያ ራሳቸው ወላይታ መሆን ይኖርባቸዋል።
Filed in: Amharic