>

ኃይማኖት እና ቋንቋን ሽፋን ያደረጉ የፖለቲካ ሸፍጦች ወይስ ...?   (ያሬድ ሀይለማርያም)

ኃይማኖት እና ቋንቋን ሽፋን ያደረጉ የፖለቲካ ሸፍጦች ወይስ …?  
ያሬድ ሀይለማርያም
ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናውችን ያለፈች አገር ናት። ቢሆንም ከአደጋ አፋፍ ግን እርቃ አታውቅም። በየጊዜው አስፈሪ ከሆኑ አደጋ አፋፍ ጫፍ ደርሳ፤ አንዳንዴ የጥፋት ቁልቁለቱን ጀምራ ይች አገር ልትጠፋ ነው፤ ልትበታተን ነው ስትባል መልሳ እንደ አገር እየቀጠለች እዚህ ደርሳለች። ችግር እንደጥላ የሚከተላት፤ አንዳንዴም ችግርን ወዳለበት ተከትላ ይምትሄድ አገር ትመስላለች። ንቁሪያ፣ መፈራረጅ እና መጠላለፍ ያልተለዩት ፖለቲካዋ ዛሬም እንዳላማረበት አሁን ከፊታችን የተጋረጡት አዲስ የሚመስሉ አሮጌ ችግሮቻችን ያሳብቃ።
አገሪቱ ከአርባ አመታት በፊት ትተራመስበት በነበረ የችግር አዙሪት ውስጥ ዛሬም ከግራ ቀኝ እየተላተመች ትገኛለች። ችግሮቻችንን በመፍትሔዎች እየቀየርን ወደፊት የሚሄድ  ማህበረሰብ መፍጠር ባለመቻላችን በተመሳሳይ ችግሮች ለዘመናት የምንማቅቅ፤ ወደር የማይገኝልን የፖለቲካ ድኩማን ሆነናል።
እስቲ ማህበረሰባችንን እያወዛገቡ እና ግራ እያጋቡ ካሉት እና በአዳዲስ አቆፋዳ ታጅለው የመጡትን ዘመን ያፈጁ ችግሮቻችንን አንድ በአንድ እያነሳን እንወያይባቸው። በዚህ ጽሑፍ የወቅቱ ዋና የውይይት ርዕስ በሆኑት የቋንቋ እና የኃይማኖት ጉዳይ ላተኩር።
+ የቋንቋ ጉዳይ
በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት በውስጡ ካካተታቸው መሰረታዊ መብቶች መካከል አንዱ እና ትልቅ ግምት የሚሰጠው ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እና ሁሉም የአገሪቱ ቋንቋዎች የመንግስትን እውቅና እንዲያገኙ የሚደነግገው አንቀጽ ነው። ይህን ተከትሎ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ማለት ይቻላል ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። ክልሎች የዝቅተኛ እና መለስተኛ ደረጃ ትምህርትን በበላይነት እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት ከተጣለባቸው ምክንያቶችን አንዱም ይሄው ነው። አማርኛን የፌደራል መንግስቱ የሥራ ቋንቋ ማድረጉም አማራጭ የሌለው ትክክለኛ እርምጃ ነው። ቋንቋን በተመለከተ ግን ሕገ መንግስቱ ያለበት ትልቅ ክፍተት ከአንድ በላይ ብሐራዊ ቋንቋዎች እንዲኖሩን አለማድረጉ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሚነሱት ቅሬታዎች አንዱ ኦሮሚኛ ልክ እንደ አማርኛ ቋንቋ የፌዴራሉም ሆነ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ለምን አልሆነም የሚል ነው። ለዚህም የሚሰጠው አመክኒዮ  የኦሮሞ ሕዝብ ቁጥር ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው የሚል ነው። ከዚህም ተነስተው አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪቃም የተናጋሪው ቁጥር በአንደኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ቋንቋ ነው በሚል ይገልጹታል። ይህ እጅግ ከተወላገደ የብሔረተኝነት ምልከታ የመነጨ እና አማሪኛን ቋንቋ የአማራ ሕዝብ ብቻ አደርጎ ከመቁጠር የሚነሳ የተዛባ እሳቤ ወይም ከፖለቲካ ግብ የመነጨ ምልከታ ነው።
አማሪኛን የአማራ ሕዝብ በአፍ መፍቻነት የሚጠቀምበት ቋንቋ እንጂ በባለቤትነት የያዘው ንብረት አይደለም። በእርግጥ ቋንቋው እንዲያድግ ትልቁን ድርሻ ከተጫወቱት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አማራው ግንባር ቀደም ቦታ ይይዛል። ነገር ግን ቋንቋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቋንቋ ከሆነ እጅግ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል። ቋንቋው እንዲያድግ የተደረገበት ታሪካዊ ሂደት ፍትሃዊ ነበር አልነበረም የሚለውን ትያቄ አንስቶ መወያየት ይቻል ይሆናል። ሌሎች ቋንቋዎች ከአማሪኛ እኩል እንዳያድጉ የተደረገባቸውንም ጫና አንስቶ በዝርዝር ታሪክን መመርመር እና በዛም ላይ መወያየ ይቻላል። ነገር ግን ዛሬ ያለውን እውነታ ሊቀይረው አይችልም። ከአማራው የህብረተሰብ ክፍል ውጭ የቀረው ኢትዮጵያዊ እርስ በራሱ ለመግባባት የሚጠቀምበት ቋንቋ አማርኛ ነው።
አንድ ኦሮሞ ከአንድ ትግሬ፣ አንድ ትግሬ ከአንድ ጉራጌ፣ አንድ ጉራጌ ከአንድ አኝዋክ፣ አንድ አኝዋክ ከአንድ ሐረሪ፣ አንድ ሐረሪ ከአንድ አፋር፣ አንድ አፋር ከአንድ ሱማሌ፣ አንድ ሲማሌ ከአንድ ሲዳማ፣ አንድ ሲዳማ ከአንድ ጋሞ፣ አንድ ጋሙ ከአንድ ጉሙዝ፣ አንድ ወላይታ ከአንድ ስልጤ፣ ወዘተ … ሊግባቡ፣ ሊገበያዩ፣ ሊወዳጁ እና ሃሳብ ሊለዋወጡ የሚችሉት አንዱ የሌላውን ቋንቋ እስካልቻለ ድረስ ለጊዜው በአማሪኛ ብቻ ነው። ስለዚህ አማሪኛ አንድ አማራ በሌለበት ቦታ ሁሉ በሌሎች ማህበረሰቦች መካከል ይነገራል። የአማርኛ ቋንቋ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል አማራ ባልሆኑ ብሄረሰቦች መካከል ለመግባቢያነት እያገለገለ ያለ ቋንቋ ነው። በበርካታ የአገሪቱ ገጠራማ ክፍሎች ጭምር ተዘዋውሮ የመስራት እድል ገጥሞኝ ስለነበር በድፍረት ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአማርኛ ይግባባል፣ ይናገራል፣ ይሰማል፣ ገበያ ይገበያያል። ይህን ለማየት በመላ ኢትዮጵያ ተዘዋውሮ ለማየት እድል ያልገጠመው ሰው አንድ አፍታ መርካቶ ብቅ ቢል ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊወክል የሚችል ሕዝብ እንዴት እና በምን ቋንቋ እንደሚግባባ መታዘብ ይችላል።
ይህን ሃቅ ወደ ጎን ገፍቶ ለፖለቲካ አጀንዳ ማሻቀጫ እንዲሆን አማርኛ በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎች አንዳንድ ክልሎች በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዳይሰጥ የሚደረገው ትንቅንቅ ግቡ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። በምንም መልኩ የዜጎችን በአፍ መቻ ቋንቋቸው የመማር መብትንም የሚጥስ አይደለም። ልጆች ከአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጨማሪ ሁለት እና ሦስት ቋንቋዎችን የመማር አቅም እንዳላቸው በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ከማረጋገጣቸውም በላይ አውሮፓ ጥሩ ምሳሌ ነች። የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገርባቸው እንደ ቤልጂየም ያሉ የአውሮፓ አገራትን ማየት በቂ ነው። አላማው ለልጆቹ የወደፊት እድል መስፋት እና ጥቅም ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን አገሪቱን የተጠናወታት ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፖለቲካ ትርክት የፉክክር እና ሽኩቻ መገለጫ መሆኑ ነው።
+ የኃይማኖት ጉዳይ፤ 
ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ትልቁን ድርሻ ከተጫወቱት አገራዊ ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ቤተ ኃይማኖት ናቸው። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እና የእስልምና ኃይማኖት ተቋማት ናቸው። እነዚህ ሁለት የእምነት ተቋማት የአገሪቱን ሁለት ሦስተኛ የሚሆነውን ሕዝብ ለሁለት ከፍለው የያዙ እና በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማኒያንን በውስጣቸው ያካተቱ ናቸው። እነዚህ ኃይማኖቶች በተቋም ደረጃ ጠንካራ እና ገለልተኛ ሆነው አይደለም ለአገር አንድነት አስተዋጽዎ ያበረከቱት። በዛ እረገድ ተቋማቶቹ እና መሪዎቻቸው ለነገስታት እና ለገዢዎች ሲያጎበድዱ ስለኖሩ አንዳንዴም የመጨቆኛ መሳሪያ ሆነውም አገልግለዋል።
በተቋም ደረጃ ለፍትህ፣ ለእውነት እና ለአርነት የመቆም መልካም ዝናም የላቸውም። ይሁንና በሥራቸው የያዙትን ሕዝብ ግን ሲጸልይም፣ ሲጾምም፣ ጽዋ ሲጣጣም ሆነ ሌሎች ኃይማኖታዊ ባዕሎቹን ሲያከብር የብሔር እና የዘር አጥር ወይም የቋንቋ ስብጥርነቱ ሳይከልለው በአብሮነት ዘመናትን እንዲሻገር አድርገውታል። አንድም መስጂድ ይሁን ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሰበሰቡ ሺዎች አማኒያን በየቋንቋቸው ወይም በዘራቸው ምክንያት የሚያገሉበትን ሁኔታ አላየንም። በተቃራኒው በዘር በሽታ የተለከፉ ሰዎች እራሳቸውን አግልለው ሲቧደኑ እንጂ። ቢያንስ ባለፉት አርባ መታት ውስጥ ኦሮሞ ስለሆን ወይም አማራ ስለሆንክ ወይም ትግሬ ስለሆንክ ወይም ሌላ ብሔር ተወካይ ስለሆንክ ተብሎ የአምልኮት ቦታ ላይ እንዳይገኝ የሚከለከል ወይም በቋንቋው እንዳይጸልይ ማዕቀብ የተጣለበት የህብረተሰብ ክፍል አለ ብዮ አላምንም። ካለም እና መጠቀስም ካለበት በትግራይ ክልል በአክሱም ከተማ በሙስሊም አማኒያን ላይ የተደረጉ የጸሎት እና የመቀበሪያ ቦታ የነፈጉ የተጽዕኖ ሕገ ወጥ እርምጃዎች ናቸው።
የእስልምና እምነትን ለመከፋፈል የተሞከረው ሴራ ከሽፎ አማኒያኑ ከግጭት እና ንትርክ ወጥተው በአንድ ላይ በመቆማቸው ደስታችንን በገለጽን በአጭር ጊዜ ውስጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ኢላማ ያደረገ አድስ የሴራ እንቅስቃሴ መከፈቱ የአገሪቱ አሳር ገና አለማብቃቱን ነው የሚያሳየው። ዛሬ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ እየተደረገ ያለው ዘመቻ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ እየተደረገ ካለው ዘመቻ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
ከመብት አንጻር ማንም ሰው ወይም የህብረተሰብ ክፍል በፈለገው የእምነት ጎራ እራሱን የማደራጀትም ሆነ የፈቀደውን እምነት የመከተል ሙሉ መብት አለው። ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ሊቋቋም የታሰበውንም የኦርቶዶክስ ቤተ ክህነት ጉዳይ ስንመለከት የኦሮሞ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር ከመነጨ ቅን መንፈስ ነው ብሎ ለማሰብ የማያስችሉ በርካታ ምልክቶችን ከወዲሁ እያየን ነው።
ግለሰቡ ቀደም ሲል ኦህዴድ/ኦዴፓን በመወከል ምርጫ ተወዳድረው የፓርላማ አባል የነበሩ፣ በክልሉ ውስጥ በህዴድ/ኦዴፓ ተሹመው የፖለቲካ አገልግሎት ላይ የቆዩ እና በመንግስት ካድሬነት የሚታወቁ ሰው እንደሆኑ የወጡት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ቤተ ክህነት ይህን እንቅስቃሴ አጥብቆ ቢያወግዝም እና መንግስት በኃይማኖቱ ስም የሚሰጡ መግለጫዎችን እንዲያስቆም ጥሪ ብታደርግም ሰሚ ያገኘት አትመስልም። በጥቅሉ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለመከፋፈል የተጀመረው ንቅናቄ ጉዳዩን ከኃይማኖታዊ ጉዳይ ይልቅ ፖለቲካዊ እንድምታው እንዲጎላ አድርጎታል። ለዚህ ተልዕኮ በክልሉ መንግስት እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ እና አክራሪ በሆኑ እና የሌላ እምነት ተከታይ በሆኑ ፖለቲከኞች ጭምር በአደባባይ በሚታይ መልኩ የሚደረገው ድጋፍ የእንቅስቃሴውን ተልዕኮ በግላጭ ያሳያል። ህውሃት የጀመረችው የሙያ ማህበራትን በተለጣፊና በጎሳ ማህበራት የመተካቱ ስልት ዛሬ በኃይማኖት ተቋማት ላይ በከፋ መልኩ አግጦና አፍጦ መምጣቱ ወዴት እየሔድን ነው ያስብላል።
ከቋንቋ እና ኃይማኖት ጋር ተያይዘው የሚነሱትን ውዝግቦች እና ንትርኮች ከወዲሁ በአገር ደረጃ መፍትሔ የማይበጅላቸው ከሆነ እና መንግስት ጉዳዩን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተነጋግሮ በአግባቡ እንዲፈታ አወንታዉ ሚናውን ከወዲሁ መወጣት ካልቻለ እያደር የፖለቲካ ውጥረት እና አለመረጋጋት ሊፈጠር ይችላል። ሌሎቹ ችግሮቻችንን ሳንፈታ ባናት በአናቱ ችግር የሚፈበርኩት እኩይ ኃይሎች የመከራ ቀናችን ሊረዝ ይችላሉ። ይህን ፈታኝ ጊዜ በጥንቃቄ ለማለፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ አቃፊና አሰባሳቢ በሆኑት ማንነቶቹ ዙሪያ ተሰባስቦ ወደ ገደል የሚገፉትን ኃይሎች እምቢኝ ሊላቸው ይገባል።
በቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic