>

አንድነታችንን የመበጣጠስ ቀጣይ ፕሮጀክት; (መሐመድ አሊ መሐመድ)

አንድነታችንን የመበጣጠስ ቀጣይ ፕሮጀክት;
መሐመድ አሊ መሐመድ
አያቶላህ ጃዋርና ጀሌዎቹ በኢትዮጵያዊነት አስተሳስረው ያቆዩንን ክሮች ለመበጣጠስ እየሸረቡ ያለውን ሴራ ስፋትና ጥልቀት በመረዳት ውስጤ መድማቱ አልቀረም። ይኸኛው አንድነታችንን ለመበጣጠስ የተያዘው ፕሮጀክት ቀጣይ ክፍል መሆኑ ነው።
– በመጀመሪያ በብሔር/በጎሳ እንድንደራጅ; በዳይና ተበዳይ ተባብለን እንድንቧደን; “እኛና እነሱ” እየተባባልን የጎሪጥ እንድንተያይ ተደረገ።
– ቀጥሎ በኢትዮጵያዊነት ሊያስተሳስሩን በሚችሉ የጋራ እሴቶቻችን; በታሪካችን; በባህሎቻችን; በሰንደቅ ዓላማችን ላይ በስፋት ተዘመተበት።
– ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተነጋግረን መግባባት የምንችልበት የጋራ ቋንቋ እንዳይኖረን አማርኛንና ሀገር በቀል ፊደላችንን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ እጅግ በረቀቀ ዘዴ እየተሠራበት ነው።
– እነሆ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ዘርና ቋንቋን መሠረት ባደረገው የአስተሳሰብ ነቀርሳ ለመበከል የሚራወጡ ወገኖችን እየታዘብን ነው።
– አሁን በተያዘው አካሄድ (trend) ነገ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ውስጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማወቅ አይቻልም።
“የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን” የሚባል መቋቋሙ ከሃይማኖቱ ይልቅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አንድምታ ያለው ጉዳይ ነው።
“የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን” ሲባል የሚሰጠው ስእል “ኦሮሚያ” የሚባል ሀገር መፈጠሩንና ከኢትዮጵያ መገንጠሉን ነው። ለምሳሌ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን አለ። በድሮው ዘመን ግን ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ስለነበረች የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚባል አልነበረም። ኤርትራ ስትገነጠል ራሷን የቻለች ሀገር በመሆኗ በራሷ ስም የሚጠራ ቤተክርስቲያን አስፈልጓት የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተመሰረተ።
ዛሬ ደግሞ የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተለይቶ ከተቋቋመ ኦሮሚያ የምትባል ሀገር መፈጠሯንና ከኢትዮጵያ መገንጠሏን የሚያሳይ ሀይማኖትን ሰበብ ያደረገ ፖለቲካዊ ክስተት ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ካለችና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያከብር መንግሥት እና ሕግ ካለ ይህን ህገወጥ እንቅስቃሴ ሊያስቆመው ይገባል።
ይህ ጉዳይ እኔ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ አይደለሁም በሚል በዝምታ የሚታለፍ አይደለም። ሌላው ቢቀር ምን እየተደረገና ወዴት እያመራን እንደሆነ በአንክሮ ልንከታተለው ይገባል።
ለማንኛውም አላህ/እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት!!!
Filed in: Amharic