>

ዐቢይ አሕመድ መቀሌ ከተመሰረተው የሕወሓት የባላደራ መንግሥት ጋር «ግልጽ ጦርነት» ውስጥ ይገባ ይሆን? (አቻምየለህ ታምሩ)

ዐቢይ አሕመድ መቀሌ ከተመሰረተው የሕወሓት የባላደራ መንግሥት ጋር «ግልጽ ጦርነት» ውስጥ ይገባ ይሆን?
አቻምየለህ ታምሩ
ሕወሓት «የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም» በማለት «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓት» ያለውን ለማዳን «የፌዴራሊስት  ኃይሎች»  ያላቸውን ሰብስቦ  የሁለት ቀናት ጉባኤ አጠናቅቆ ቀጣይ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተባብር ኮምቴ አቋቁሟል፤ የአቋም መግለጫም አውጥቷል። ሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች ተስማሙበት በተባለው የአቋም መግለጫ «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን» ለመታደግ አለማቀፍ ጥሪ ቀርቧል። የመቀሌው ጉባኤ በመንግሥትነት የተሰየመውን የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ የመንግሥትነት ሥልጣን በግልጽ ውድቅ ያደረጉ ኃይሎች  ስብስብ ነው።
በመንግሥትነት የተሰየመውን የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ «ኃላፊነቱን አልተወጣም» በማለት የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ ዋና ሥራው የሆነውን «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን»  የማዳን አላማ ይዞ የሚቋቋም ማናቸውም ስብስብ የባላደራ መንግሥት ነው። ይህ የመንግሥትን ዋነኛ ስራ ለመስራት የተመሰረተ  የባላደራ መንግሥት ግልጽ የሆነ  በመንግሥት ላይ የተመሰረተ  ሌላ መንግሥት ነው።
ባጭሩ በመንግሥት ላይ መንግሥት የመሰረተው፣ «የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም» በማለት «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን» ለማዳን ጉባኤ የተቀመጠውና ቀጣይ መንግሥታዊ ስራዎች የሆኑትን ሕገመንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን ለመታደግ አለማቀፍ ጥሪ ያቀረበው የመቀሌው የሕወሓት ስብስብ የባላደራ መንግሥት ነው።
ዐቢይ አሕመድ ከዚህ በፊት የፖለቲካ ድርጅት ባልሆነውና ሥልጣን የመያዝ አላማ ከሌለው በእስክንድር ነጋ ከሚመራው የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ጋር «ግልጽ ጦርነት» ውስጥ እንደሚገባ ነግሮን ነበር። ዐቢይ አሕመድ ከአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ጋር ጦርነት ውስጥ እገባለሁ ያለው «ምክር ቤቱ ምርጫ ሳያሸንፍ ባላደራ፣ ባደራ የሚል ጫዎታ ውስጥ ገብቷል» ብሎ ነው። ምክር ቤቱ ግን የሲቪክ ተቋም እንጂ ምርጫ የመሳተፍና የፖለቲካ ሥልጣን የመያዝ አላማ እንደሌላው ግልጽ አድርጓል።
የዐቢይ አሕመድን መንግሥት በመንግሥትነት ተቀብሎ የፖለቲካ ሥልጣን የመያዝ አላማም ፍላጎትም ከሌለው ከአዲስ አበባ ምክር ቤት ጋር «ግልጽ ጦርነት» ውስጥ እገባለሁ ያለን ዐቢይ አሕመድ አሁን በግልጽ የሚፈተንበት ወቅት መጥቶለታል። ሕወሓት «የዐቢይ አሕመድን አገዛዝ ኃላፊነቱን አልተወጣም» በማለት የመንግሥት ዋና ተግባር የሆነውን «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን» የመታደግ ሥልጣን ነጥቆ «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን» ለማዳን የሚል መንግሥታዊ አላማ ይዞ በመቀሌ ከተማ የባላደራ መንግሥት መስርቷል።
የወቅቱ ወሳኝ የፖለቲካ ጥያቄ ዐቢይ አሕመድ ለመቀሌው የባላደራ መንግሥት ግብረ መልሱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። ዐቢይ አሕመድ መቀሌ ላይ ከተፈጠረው የሕወሓት የባላደራ መንግሥት ጋር ግልጽ ጦርነት ውስጥ ይገባ ይሆን? ነው ዐቢይ አሕመድ ግልጽ ጦርነት ውስጥ የሚገባው የመንግሥት ዋና ተግባር የሆነውን «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን» የመታደግ ሥልጣን ነጥቆ  «ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓቱን» ለማዳን በሚል መንግሥታዊ አላማ  የተቋቋመውን  የመቀሌ የባላደራ መንግሥት እሹሩሩ እያለ የባላደራ መንግሥት የማቋቋም እቅድም አላማም ከሌለው ከአዲስ አበባው ምክር ቤት ጋር ብቻ ነው?
መቀሌ የተቋቋመው ባላደራ መንግሥት መሪ ፋሽስት ወያኔ  «ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግ እየመጣሁ ነው» እያለ ነው!
«ሕወሓት ኢትዮጵያን ዳግም ለማዳን መስራት እንደሚገባው ተነገረ
ሕወሓት/ ኢሕአዴግ በእኅት ድርጅቶች በተፈፀመባት ክህደት ወደ መቀሌ ተመልሳ ይቺን  ሀገር ለአፍራሾች  አሳልፋ በመስጠትዋ ከባድ ስህተት እንደፈፀመች ተነገራት።
ስለዚህ ኢትዮጵያ አጋጥሟት ካለው ሀገር የመፍረስ አደጋ ለማዳን ሕወሓት ከትግራይ ሕዝብ ጋር ተናባ ሰላምና ልማት ትግራይ ላይ እንደፈጠረችው ሁሉ በተፈጸመባት ክህደት  ሳትደናገር ኢትዮጵያን ለማዳን በአፋጣኝ መስራት ይገባታል ተባለ።»
Filed in: Amharic