>

ለመንግሥታቱ ድርጅት የቀረበ ይግባኝ ?!? አጼ ኃይለ ፡ ሥላሴ ( አሰፋ ሀይሉ)

ለመንግሥታቱ ድርጅት የቀረበ ይግባኝ ?!?

ጼ ኃይለ ፡ ሥላሴ
ሠኔ 1928 ዓ.ም. / ጁን 1936፤ ጄኔቫ፤ ስዊዘርላንድ/
አሰፋ ሀይሉ
«እኔ ፤ ቀዳማዊ ፡ ኃይለ ፡ ሥላሴ ፤ የኢትዮጵያ ፡ ንጉሠ-ነገሥት ፤ እዚህ ፡ ዛሬ ፡ የቆምሁት ፡ ለሕዝቤ ፡ የሚገባውን ፡ ፍትህ ፡ ለመጠየቅ፣ እና ፡ ከስምንት ፡ ወራት ፡ በፊት ፡ ሃምሣ ፡ ሃገራት ፡ በተሰበሰቡበት ፡ ጉባዔ ፡ የዓለማቀፍ ፡ ሥምምነቶችን ፡ የጣሰ ፡ ወረራ ፡ ተፈፅሟል ፡ በማለት ፡ ሃገሬን ፡ ለማገዝ ፡ የተገባላትን ፡ ቃል-ኪዳን ፡ ጭምር ፡ ለመጠየቅ ነው ፡፡
«በእርግጥ ፡ በዚህ ፡ የመንግሥታት ፡ ድርጅት፡ ጉባዔ ፡ ላይ ፡ የአንድ ፡ ሃገር ፡ ርዕሰ ፡ ብሔር ፡ በቀጥታ ፡ መጥቶ ፡ ተናግሮ ፡ ያወቀበት ፡ ጊዜ ፡ የለም ፡፡ ነገር ፡ ግን ፡ ደግሞ ፡ የመንግሥታቱ ፡ ድርጅት ፡ አባል ፡ የሆነ ፡ አንድ ፡ ሕዝብ ፡ በሌላው ፡ በተቃጣበት ፡ ኢ-ፍትሃዊነት ፡ የግፍ-ቀማሽ ፡ እንዲሆን የተደረገበትም ሆነ ፤ በምንቸገረኝነት ፡ በወራሪው ፡ ኃይል ፡ መከራን ፡ እንዲቀበል ፡ የተተወበት ፡ ጊዜም ፡ ደግሞ ፡ የለም፡፡ እንደገናም ፡ ደግሞ ፡ እስከዛሬ ፡ ዓለም ፡ ባሣለፈችው ፡ ታሪክ ፡ አንድ ፡ መንግሥት ፤ በምድሪቱ ፡ ባሉ ፡ ነዋሪዎች ፡ ሰብዓውያን ፡ ዘንድ ፡ ሁሉ ፡ እጅግ ፡ ትልቅ ፡ ክብር ፡ የሚቸራቸውን ፡ ዓለማቀፍ ፡ የሰው ፡ ልጅ ፡ መብት ፡ ድንጋጌዎችንና ፡ የተስፋ-ቃሎች ፡ ወደ ፡ ጎን ፡ በማለት ፤ አስቦበትና ፡ በዘዴ ፡ አቅዶ ፤ የሌላውን ፡ ሃገር ፡ ንፁሃን ፡ ሕዝብ ፡ ዘግናኝ ፡ በሆነ ፡ አደገኛ ፡ የመርዝ ፡ ጋዝ ፡ ሊጨርስ ፡ የተነሣበት ፡ ክስተትም ፡ እንዲሁ ፡ ታይቶ ፡ አይታወቅም ፡፡
«እና ፡ ለአንድ ፡ ንጉሠ-ነገሥት ፡ በቀጥታ ፡ ፊታችሁ ፡ ቀርቦ ፡ መናገሩ ፡ ያልተለመደ ፡ ቢሆንም ፤ ነገር ፡ ግን ፡ የአንድን ፡ ለዘመናት ፡ በነፃነት ፡ የኖረን ፡ ሕዝብና ፡ መንግሥት ፡ ነፃነት ፡ ለማስከበር ፡ ሲሉ ፡ በመጨረሻ ፡ እስትንፋሳቸው ፡ እየተፋለሙ ፡ ያሉትን ፡ ሕዝቦቼን ፤ ከፊት ፡ ሆኜ ፡ በአውደ ፡ ግንባር ፡ እየመራሁ ፡ ከምዋደቅበት ፡ ተነስቼ ፤ አሁንም ፡ የእነርሱን የሕዝቦቼንና ፡ የሃገሬን ፡ ነፃነት ፡ ለመከላከል ፡ ያለብኝን ፡ ተቀዳሚ ፡ አደራና ፡ ኃላፊነት ፡ ለመወጣት ፡ ስል ፡ ነው ፡ ባልተለመደ ፡ ሁኔታ ፡ በቀጥታ ፡ እዚህ ፡ ዤኔቫ ፡ ድረስ ፡ መጥቼ ፡ ከፈታችሁ ፡ የቆምሁት ፡፡
«እስካሁንም ፡ ከድንጋጤያቸው ፡ ያልተላቀቁት ፡ እዚህ ፡ አጅበውኝ ፡ የቆሙት ፡ ባልደራሶችም ፡ በሕዝባችን ፡ ላይ ፡ ስለሆነው ፡ መቅሰፍት ፡ ሁሉ ፡ እማኞች ፡ ሆነው ፡ ሊያስረዱ ፡ ይችላሉ ፡፡ በሃገሬ ፡ ሕዝብ ፡ ላይ ፡ የተሰነዘረው ፡ ሊገለፅ ፡ የማይቻል ፡ አስፈሪ ፡ ሥቃይ ፡ እና ፡ እልቂት ፡  በሌሎች ፡ ሃገሮች ፡ ላይ ፡ እንዳይደርስባቸው ፡ እንዲያተርፋቸው ፡ ለእርሱ ፡ ለሁሉን ፡ ቻይ ፡ አምላክ ፡ ፀሎቴን ፡ አደርሣለሁ ፡፡
«እዚህ ፡ ዤኔቫ ፡ ላይ ፡ አብረውኝ ፡ ለተሰበሰቡ ፡ የሃገራት ፡ እንደራሴዎች ፡ በየሃገራቸው ፡ ለሚያስተዳድሯቸው ፡ በሚሊዮን ፡ የሚቆጠሩ ፡ ወንዶችን ፣ ሴቶችንና ፣ ሕፃናትን ፡ ሕይወት ፡ ለመጠበቅ ፡ አደራ ፡ ያለባቸው ፡ እንደመሆናቸው ፡ መጠን ፤ በሕዝቦቻቸው ፡ ላይ ፡ ከፊታቸው ፡ የተደቀነባቸውን ፡ አስከፊ ፡ አደጋ ፡ የመግለጽ ፡ ግዴታ ፡ እንዳለብኝ ፡ አምናለሁ ፡፡ ይህንንም ፡ ግዴታዬን ፡ የምወጣው ፡ በሃገሬ ፡ በኢትዮያ ፡ ላይ ፡ የደረሰውን ፡ የሚዘገንን ፡ ዕጣ ፡ ፈንታ ፡ ዘርዝሬ ፡ ለእናንተ ፡ በመግለፅ ፡ ነው ፡፡ የኢጣልያ ፡ መንግሥት ፡ በተዋጊ ፡ ጦረኞች ፡ ላይ ፡ ብቻ ፡ አይደለም ፡ እኮ ፡ ጦርነት ፡ ያካሄደው ፡፡ ከምንም ፡ ሁሉ ፡ በላይ ፡ የጥቃቱ ፡ ዒላማ ፡ ያደረገው ፡ ሕዝቦችን ፡ ነው — ከአውደ ፡ ውጊያ ፡ ሥፍራዎች ፡ በብዙ ፡ ርቀት ፡ ላይ ፡ የሚገኙ ፡ ሠላማዊ ፡ ነዋሪዎችን ፡ ነው ፡ የጦርነት ፡ ዒላማው ፡ ያደረገው ፡፡ ይህንንም ፡ የሚያደርገው ፡ ሕዝቦቻችንን ፡ ለማስበርገግ ፡ እና ፡ በጅምላ ፡ ፈጅቶ ፡ ለመጨረስ ፡ ሲል ፡ ነው ፡፡
«… ይህን ፡ እጅግ ፡ ኋላ ፡ ቀር ፡ የሆነ ፡ ከሠብዓውያን ፡ የማይጠበቅ ፡ ሕዝብ በበዛባባቸው ፡ ከጦርነት ፡ በራቁ ፡ ቦታዎች ፣ በሠላማዊ ፡ ዜጎች ፡ ላይ ፡ የተወሰደ ፡ የጭካኔ ፡ ዘዴ ፡ እና ፡ እርምጃ ፡- የሰው ፡ ልጅ ፡ ጥንታዊ ፡ አውሬያዊ ፡ ባህርይ ፡ በዘመናዊ ፡ መልክ ፡ ተራቅቆ ፡ መምጣት ፡ የሚለው ፡ ቃል ፡ ብቻ ፡ ሊገልጸው ፡ ከሚችል ፡ በቀር ፡ ሌላ ፡ ምህንያት ፡ አናገኝለትም ፡፡… በምትወረሩ ፡ ጊዜ ፡ ከጎናችሁ ፡ ነን ፡ ብላችሁ ፡ ቃላችሁን ፡ የሰጣችሁን ፡ እናንት ፡ የመንግሥታቱ ፡ ድርጅት ፡ ሃምሣ-ሁለት ፡ ሃገራት ፡ ወኪሎች ፡- እውን ፡ ስለ ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ምን ፡ ለማድረግ ፡ ነው ፡ ፍላጎታችሁ ? እና ፡ ደግሞ ፡ በተለይ ፡ የጋራ ፡ የደህንነት ፡ ቃል-ኪዳናችንን ፡ ለመጠበቅና ፡ በተለይ ፡ አቅመ-ደካማውን ፡ ከጉልበተኛ ፡ ወራሪ ፡ ለመታደግ ፡ ከፍተኛ ፡ አደራ የወደቀባችሁ ፤ ነገ በእኛ ፡ ላይ ፡ የደረሰብን ፡ ሥቃይና ፡ አደጋ ፡ ዳግም ፡ በተለይ ፡ በእናንተ ፡ ላይ ፡ ተነጣጥሮ ፡ ሊሠነዘርባችሁ ፡ እንደሚችል ፡ የሚታሰበው ፡ እናንት ፡ ኃያላን ፡ ሃገሮችስ እስቲ ልጠይቃችሁ ፡- እውን ፡ ለኢትዮጵያ ፡ ስትሉ ፡ ምን ፡ ዓይነት ፡ እርምጃ ፡ ነው ፡ ልትወስዱ ፡ ያሰባችሁት ?
«… እናንት ፡ የዓለም  ፡ መንግሥታት ፡ እንደራሴዎች ፡- እኔ ፡ እዚህ ፡ ዤኔቫ ፡ ድረስ ፡ መጥቼ ፡ እነሆ ፡ ከፊታችሁ ፡ የቆምሁት ፡ ከአንድ ፡ የሃገር ፡ መሪ ፡ የሚጠበቅበትን ፡ ከፍተኛውን ፡ የሕዝቤን ፡ አደራ ፡ ለመወጣት ፡ ነውና ፡ ውስጤን ፡ የሚሰማኝን ፡ ብሶትና ፡ ሕመም ፡ ችዬ ፡ በፊታችሁ ፡ ቆሜ ፡ የፍትህ ፡ ልመናችንን ፡ ሣቀርብ ፡ የምጠይቃችሁ ፡ አንድን ፡ ነገር ፡ ብቻ ፡ ይሆናል ፡- ወደ ፡ ሕዝቦቼ ፡ ተመልሼ ፡ ይዤላቸው ፡ የምሄደው ፡ ምን ፡ የሚል ፡ ምላሻችሁን ፡ ይሆን ፡ ልትሰጡኝ ፡ የፈቀዳችሁት ??»
— ጃንሆይ በዚያን ክፉ ወቀት ላይ የተሰጣቸው ምላሽ ጆሮ ዳባ ልበስ የሚል ነበር ፡፡ የጃንሆይ ቃልም አልቀረም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰው እነሆ በሌሎቹም ላይ ሆነ፡፡ በ1937 ዓ.ም. የመንግሥታቱ ድርጅት በኦፊሴል ፈረሰ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ተተካ፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ብቸኛዋ ነፃ ባለጥቁር ሕዝቦች የመንግሥታቱ ማህበር አባል ነበረች፡፡ በአቢሲኒያ ላይ በወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ መንግሥት የደረሰው ግፍ ሁልጊዜ ሲታወስ ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ በጀግኖች አርበኞቿ እና በወዳጇ በእንግሊዝ እገዛ ሃገሯን ከፋሺስቶቹ ነፃ አወጣች፡፡ ፋሺስቶቹን የተካው የኢጣልያ መንግሥትም ለደረሰው ጥፋት በኢጣልያ መንግሥትና ሕዝብ ስም ይፋዊ ይቅርታ ጠይቆ ጠቀም ያለ ካሣ ከፈለ፡፡ ለጥፋት ኃይሎች ለተሰዉት – ቁጥራቸው ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን – እና በተለይም በአንዲት ጀንበር በአዲስ አበባ ከተማ በየካቲት 12 ቀን በፋሺስት ኢጣልያ ወታደሮች ለተጨፈጨፉ ሠላማዊ ሰዎች – መታሰቢያ ይሆን ዘንድ – ዛሬ በአዲስ አበባ፤ ስድስት ኪሎ አደባባይ ላይ የሚገኘውን የሠማዕታት ኃውልት – የኢትዮጵያና ኢጣልያ ሕዝቦችን ወዳጅነት እንዲዘክር – በኢጣልያኖች ታንፆ ተተከለ፡፡
ሠላም ለዓለም ይሁን ፡፡ አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic