>
5:13 pm - Saturday April 20, 8920

የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም!!! (የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ)

የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም!!!
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ለድርድር የማይቀርብና ለቋንቋው እድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ስርዓተ ትምህርት አስመልክቶ በትምህርት ሚኒስቴር የተሰጠው መግለጫ፤ የአፋን ኦሮሞን ተጨባጭ ሁኔታ የማይገልጽ መሆኑንና የክልሉ መንግስት በቋንቋ ጉዳይ ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳለው ህዝቡ ሊረዳ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን የማስተዳደር፣ የትምህርት ስርዓትን ማዘጋጀት፣ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ማዘጋጀትና አርሞ ውጤት መወሰን ለክልል የተሰጠ ስልጣን በመሆኑ በዚህ ላይ ጫና የሚያሳድር ማንም ሊኖር እንደማይገባ ገልጸው እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ በአፋን ኦሮሞ የሚሰጥ ትምህር እንደሚቀጥልም ነው ያሳወቁት።
የክልሉ መንግስት የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን ለማሳደግ ከዚህ በፊት በቋንቋው ትምህርት በማይሰጥባቸው አካባቢዎች ጭምር መማሪያ እንዲሆን እየሰራ በመሆኑ ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው አቶ ሽመልስ የገለጹት።
በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ ከክልሉ ስርዓተ ትምህርት ውጪ የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች ላይም በዚህ ዓመት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድም ተጠቅሷል
 —
“በአፋን ኦሮሞ ትምህርት አንደራደርም” ሲባል ልብ ሊባሉ የሚገባቸው  አራት ነጥቦች !!!
© ኄኖክ ኄኖክ
፩) ኦሮምኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ ከመሆኑ በፊት አማርኛ “ኦሮሚያ” የሚባለው ክልል ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ መሆን ይኖርበታል።
፪) አማርኛ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነው በአማራ ህዝብ ሰልፍና ፉከራ ሳይሆን በሁሉም ህዝቦች ሎጂካዊ ቅቡልነት ነው። በመሆኑም ኦሮምኛ የፌዴራሉ መንግሥት ተጨማሪ ቋንቋ ለመሆን ቢያንስ ኢትዮጵያዊያን በደንብ ሊያነቡት በሚችሉት የኢትዮጵያ ፊደል ተጽፎ በትምህርት እንዲሰጥ የቅድሚያ ቅድሚያ መሰራት አለበት።
፫) የቋንቋን ጉዳይ ፖለቲሳይዝ የማድረግን አስነዋሪ አካሄድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመግታት ሲባል ኦሮምኛን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አምስትና ስድስት ቋንቋዎችን በመጨመር የፌዴራል ቋንቋ ማድረግ የግዴታ ይሆናል።
፬) አሁን ባለው የቁጩ ሕገመንግሥት አማርኛ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንደሆነ በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጧል። በመሆኑም ተጨማሪ ቋንቋ የፌዴራል መንግሥት ቋንቋ ለማድረግ ህገመንግስቱን የግድ ማሻሻል ይጠይቃል።
Filed in: Amharic