>

ሰማያዊ ፓርቲ ያዘጋጀውን የዜጎች ቃል-ኪዳን ሰነድ (ሕገ መሰረት) ለህዝብ ይፋ አደረገ

Blue partyየዜጎች ቃል-ኪዳን ሰነድ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ

ክፍል ፩
መግቢያ
ይህ የዜግነት ቻርተር (ቃል-ኪዳን እና ሕገ-መሠረት) ከፖለቲካዊ አድናቂነት ነጻ የሆነ፤ ሁሉን-አቀፍ ምሰሶ የሆኑ መርህዎችን ያካተተ የማሕበረሰብ (የሲቪክ) ንቅናቄ ሰነድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከየት ወደ የት ለሚለው አንገብጋቢ ጥያቄም መሰረታዊ መልስን ያቀፈ ራዕይን የሚያስተጋባ የኩሩ ዜጎች መለያ ነው፡፡ ይህም ማለት፡-
• ቃልኪዳኑ ግልጽና ሁሉን-አቀፍ ሕብረተሰብ ለመገንባት የሚጠቅሙ የሲቪክ ባህሎችን ለማዳበር፤
• በዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት፤ ሉዓላዊነት፤ ማህበረሰባዊ የራስ-በራስ አስተዳደርን የመሳሰሉ ልምዶች እንዲሰፍኑ በጠቅላላው መልካም የስልጣን አጠቃቀም ስነ-ምግባርን እውን ለማድረግ ለተነሳሱ ዜጎች፣ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች የአንድነትና የወል ራእይና መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግል፤
• በዓለም-አቀፍ ተቀባይነት ያገኙ የሰብአዊ፣ የሲቪል፣ የባህልና የፖለቲካ ሁለንተናዊ መብቶች በመንግሥት ብቻ ሳይሆን ነገ ለልጆቻችን የምናወርሰውን በጎና መልካም ነገር ሁሉ በሚያስብ መንፈስ በዜጎችም እንዲጠበቁ የሚያስችል የሲቪክና የፖለቲካ ጥምር እንቅስቃሴን እውን ለማድረግ አስፈላጊነቱን ለማስገንዘብ፤
• የረጅም ጉዞ እንቅስቃሴውን ፍሬያማ ለማድረግ ደግሞ ለግለሰብ ነጻነትና ክብር መጠንቀቅ፣ የህብረተሰብን ጥቅም ማቀፍ፣ የተለያዩ ባህሎችን ማክበር እና አዎንታዊ አመለካከት እንዲዳብር በማድረግ መሠረታዊ እሴቶችን መደገፍ ዋና ተግባሩ ነው፡፡

ስለሆነም የዛሬው ትውልድ የነገይቱን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚገነባባቸው የኢትዮጵያዊነት መንፈስና የስልጣኔያችን መለዮች መሆናቸውን አጉልቶ ለማሳየት፤
• አበው ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዳሉት፤ የሲቪክ ማህበራትን ንቃትና በአንድ ግንባር ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ የምንሻው ህዝባችንን ከአገዛዝ ስርአት እና ከጨቋኝ መንግስታዊ ስርዓት ለማውጣት ብቻ ሳይሆን ተመልሶም ለጭቆና እና ለአገዛዝ እጅ ላለመስጠትና ላለመንበርከክ መብቱን እና ሰብአዊ ክብሩን አስጠብቆ ከማንም ሳይለምን በፍቅር ተደራጅቶ ለመቆም ዋስትና የመሆን ሚና ስላለው ነው፡፡ ይህም በመሆኑ መብትና ግዴታዎችን በጽኑ እውን ለማድረግ የሚካሄደውን ትግል ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲደግፉ ጥሪውን ለማስተጋባት፣ በመጨረሻም
• ኢትዮጵያውያን በነፃነት መብትና ግዴታችንን በማክበር በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ አዲስ የአስተዳደር ባህል እንድናዳብር እና ይህ መልካም አስተሳብ ተግባራዊ መሆን ያለበት ወቅትም በመሆኑ ይህ ሰነድ አስፈላጊነቱ እጅግ የጎላ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ የምንዘረጋው ሥርዓት ሃቀኝነትንና ዜጎችን ሉዓላዊ ያደረገ፣ የምንመርጣቸው መሪዎችም ለሕዝብ አገልግሎትና ተጠያቂነት የገቡትን ቃል በመወጣትና ባለመወጣት የሚመዘኑ እንዲሆኑ ስለምንመኝ ነው፡፡
ይህ የቃል-ኪዳን ሰነድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጠንካራ የጋራ እንቅስቃሴ አድርገው ለእኩልነትና ለፍትህ የቆመ መንግስት በመመስረት ሀገራዊ ሉአላዊነትን፤ ሰብአዊ ክብርን እና የዜጎች ነፃነትን እንዲያስከብሩ የተዘጋጀ ሕገ-መሠረት ነው፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተጠሪ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ይህንን ሕገ-መሠረት አይተው እንዲወያዩበት፤ እንዲተቹበት እና የማሻሻያ ሀሳብ በማቅረብ ሰነዱ ውስጥ የተዘረዘሩትን መርሆዎችና አላማዎች በድርጅታዊ ፕሮግራሞቻቸው ውስጥ እንዲያካትቱ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
ክፍል ፪
ኢትዮጵያ ከየት ወደ የት?
እያንዳንዱ ትውልድ ከአባቶቹና ከእናቶቹ የወረሳቸውን መልካም የሆኑ ነገሮች ሁሉ የመጠበቅና ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር አስታርቆ የማቅረብ እንዲሁም ኢትዮጵያን የመጠበቅና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ዘመናዊዋ ኢትዮጵያም ሁሉም ዜጎቿ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በእኩል ተሳትፎ የሚያደርጉባት የተሰፋ ምድር መሆን እንዳለባት አያከራክርም፡፡
የአሁኑን ትውልድ ምኞትና ተስፋ አዎንታዊ ለማድረግና ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ በመገንዘብ፣ ከአመለካከት አንፃር የጋራ ስምምነት እንዲኖርና ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ በውል ተረድቶ የውደፊት ምኞቱን እና ተስፋውን መንደፍ አንገብጋቢ ተግባራችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በቀላሉ የማይካዱ የውርስ ገጽታዎች ስላሉት ለተነሳንበት ዓላማ የሚጠቅሙትን ለምሳሌ ያህል እንጠቁማቸው፡-
• ባለፉት ብዙ ምዕተ-ዓመታት አንዴ ሲጠብ አንዴ ደግሞ ሲሰፋ በኖረው የኢትዮጵያ ግዛት ጎልተው የሚታወቁ በአንድ ጎሳ ወይም ነገድ ስም ብቻ ወይንም ክልላዊነት የተመሰረቱ ሉዓላዊ መንግስታት አልነበሩም፡፡ እርግጥ የተለያዩ መንግስታት በየዘመኑ ሃይልና ጉልበትን መሰረት ባደረገ አካሄድ የስልጣን መደላድላቸውን ሲያጠናክሩ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን እንደአንድ አገር ህዝብ ደስታና ሃዘኑን በጋራ እየተካፈለ አብዛኛውን ጊዜ ተዛምዶና በባህል ተወራርሶ ኖሯል፡፡ ይህ የተዋረሰ ባህል እርስ-በርስ እየተቆራኘ ለቀሪው ትውልድ ያቆየው ባህል ዘመናዊ ዲሞክራሲን ለመገንባት ምቹ መንደርደሪያ መሆኑ አያከራክርም፤
• በሀገሪቱ ውስጥ ክርስትና፣ እስልምናና ባህላዊ የሃይማኖት ሥርዓቶች ተፈቃቅደውና ተከባብረው መኖራቸው የአንጋፋዋ ኢትዮጵያን አብነት ያሳያል፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሀገር በመሆኗ፣ ተባብረው የሚኖሩበትንና የአናሳዎቹን መብት ለማስከበር የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ማድረግ አስፈላጊነቱ ግልጽ ነው፤
• አልፎ አልፎ ከታዩት ከባድ የፈተና ዘመኖች በስተቀር ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ጠንካራ መለያዎችን ተጋርተዋል፡፡ በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ልዩነትም ቢሆን ቆለኛው ከደገኛው፣አርሶ-አደሩ ከአርብቶ-አደሩና ከነጋዴው ጋር በኢኮኖሚ ተደጋግፈው በባህል እየተወራረሱ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ገዳማት፣ አድባራትና መስጊዶች እንዲሁም የማህበረሰብ ተቋማትና የሰፈር ሽማግሌዎች ተቃራኒ ፍላጎቶችን በማስታረቅ ረገድ ለወደፊት የሚበጁ ሰላማዊ አደራዳሪ ተቋሞችን የምንገነባበት የባህል ቅርስ አጎናጽፈውናል፤
• ኢትዮጵያ በአፈ-ታሪክ ብቻ ሳይሆን የረጅም ስልጣኔዋ መለያ በሆነው የሥነ-ጽሁፍ ታሪኳን (ፊደሎቿን) በመጠቀም ከትውልድ ወደ ትውልድ የሞራል፣ የፖለቲካ እና የቁሳቁስ ባህሎችዋን ስታስተላልፍ የኖረች አገር ናት፡፡ ከውጭ ስልጣኔዎች ጋር ባላት ግንኙነት ጭፍን ኩረጃ ሳይሆን የሚበጇትን ተቀብላ በረቀቀ ዘዴ ከባህሏ ጋር አጣጥማ የማስፋፋት ችሎታ የነበራትም አገር ናት፡፡ ለምሳሌ የሃይማኖት ገጽታን በሚመለከት፣ ከሌሎች አገሮች የሚለያት አርማዋ ከኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን ጋር የተጣመሩ የአይሁዳዊ፣ የክርስትናና የእስልምና እምነቶች አብረው ለብዙ ዘመናት በሰላም መኖራቸውን ነው፡፡ እንዲሁም
• የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦርነትና የፖለቲካ ሽብሮችና ውጥንቅጦች ጠባሳዎች ይታይባታል፡፡ ከነዚህም በኢጣሊያ ሁለት ጊዜ የተፈፀመባት ወረራዎችና ከዚያ ማግስት የተማከለ መንግስታዊ ቢሮክራሲ ለመፍጠር የተካሄዱ ሹኩቻዎች፣ በ1966 ዓ.ም በአብዮት ስም ሶሻሊዝም የተሞከረበት የመከራ ዘመን፣ በኤርትራ መዋሃድና እንደገና መገንጠል ወቅት የተካሄዱት የእርስ-በርስ ጦርነቶችን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡
የነዚህ አስከፊ ጥቃቶች ውጤቶችና ፍልሚያዎች ብዙ ናቸው፤የርስ-በርስ መተማመን መቦርቦር፤ በአንዳንድ ወጣት ዜጎቻችን አስተሳሰብ ላይ በሃገር ከመኩራት ይልቅ ወደ ማፈር ቀስ በቀስ መለወጥ፣ የድህነት መናርና የወጣቱ ተስፋ ማጣት፣ ቡድናዊነትና ወገናዊነት በግልጽ የሚታዩ ችግሮች ሲሆኑ እስካሁን ድረስ መፍትሄ አልተበጀላቸውም፡፡
በየወቅቱ የስርአቱ ካድሬዎች ጠብና ግጭት ማስወገጅያ ባህላዊ ልማዶችን በማጥፋትና ሽማግሌዎችን በመወንጀል ሕዝቡ በሃገር ሽማግሌዎች እና በመንግስት ሹማምንቶች ላይ ምንም አይነት እምነት እንዳያሳድር አድርገውታል፡፡
ይህ ስር እየሰደደ የመጣው የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ቀውስ ጎላ ወዳሉ ሁለት ድምዳሜዎች ላይ ያደርሰናል፡፡

1ኛ) የምንገነባውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በባለቤትነት እንድንቀበለውና እንድንኮራበት ከተፈለገ ጥራት ባላቸው የመንግስታዊ ስልጣን አያያዝ ባህሎቻችን ላይ የተመሰረተ መሆን እንደሚኖርበትና፤

2) ለዘላቂ ብልጽግና፣ የዜጎችንም ሆነ የመንግስትን ሉዓላዊነቶች ለማስከበርና ለአፍሪካ ቀንድ መሪነትን ለመጎናጸፍ ከውጭው ዓለም ጋር በጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ ትስስር ሲዘረጋ መሆኑን ነው፡፡ የጋራ እድልን በጋራ ለመወሰን የሚያስችለንም ነው፡፡
በአይበገሬነት የቆየውና ቢወድቅ ነጥሮ የሚነሳው ኢትዮጵያዊ ክብር እና ጨዋነት ወደፊት ፍትሃዊነት የሰፈነበትን የመንግስት አወቃቀርና አሰራር ለመዘርጋትና “የነፃ-ዜጋ” ልደትን ለማብሰር እንደመሰረት ልንጠቀምበት ያስችለናል፡፡ ነፃ ዜግነት የጋራ ጥቅምን ከግል ጥቅም ጋር አጣጥሞ የሚያራምድ የልበ-ሙሉ እና የኩሩ ኢትዮጵያዊ መለያና አርማ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ትንሳኤ በሚመለከት ይህ ሰነድ የሚያራምደውን ፅንሰ-ሃሳብ የሚያሳዩ ሦስት ዋና ዋና መሰረታዊ መርሆች ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህም፣
1) የሕዝብ ውክልና እና አለኝታ ያለበት አስተዳደር፣
2) ብዙሃኑ የአናሳዎችን መብት የሚያከብሩበት እና
3) የኢኮኖሚ ነፃነት ናቸው፡፡
እነዚህ መሠረታዊ መርሆዎች ተጨባጭ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሀድሶ ዕቅዶችን ለመንደፍ የሚያገለግሉ ምስሶዎች ይሆናሉ፡፡ ሦስቱ የማይነጣጠሉ መሠረታዊ መርሆዎች ለዘላቂ ሰላም፣ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ማንነትንና በፍትሐዊ መንገድ የህዝብ ባለስልጣንነትን ያንፀባርቃሉ፡፡
ክፍል ፫
የኢትዩጵያ የሕዝብ አስተዳደር መለያ ምን ምን ናቸው?
ነፃነት መሰረታዊ ትርጉሙ ብዙ አማሪጮችን ማግኘት ሲሆን፤ ለፍትሐዊ የህዝብ አስተዳደር ቅድመ መሰረቱ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ መሰረታዊ ትርጉሙ ነፃ ሕዝብ የመምረጥ መብቱን በስራ ላይ የሚያውልበት የውሳኔ መስጫ መንገድ ነው፡፡ በህዝብ ሉዓላዊነት የተመሰረቱ ወኪላዊ የዲሞክራሲ ይዘቶች–ግለሰባዊ (ሊበራል) እንዲሁም ወልአዊ (ሶሻል)–የዜጎችን መብቶችን (ማለት ህይዎትን፣ ነጻነትን፣ ሃብትን) በውክልና በማስከበር ደረጃ አብነትን የያዙ ናቸው፡፡ የዚህም መሰረቱ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያገኙትን መብቶች ያካተተ ርዕስ-ሕግ በጽሁፍ ማጽደቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ይህ የቃል-ኪዳን ሰነድ መልካም የሆኑ ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና ልንዘነጋቸው የማይቻለን የዘመናችን እውነታዎችን ያካተተ ርዕስ-ሕግ እንዲዘጋጅ የሚጠይቀው፡፡
ስለ አገራችን ዲሞክራሲ ያለን አመለካከት በአገሪቷና በሌሎች ተመሳሳይ አገሮች የፖለቲካ ታሪክ ልምዶችና ተሞክሮዎች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተጫኑብን ሶስቱ ህገ-መንግስቶች ይህ ነው የሚባል ፍትህ፣ እኩልነትና ብልፅግና አለማስገኘታቸው ግልጽ ነው፡፡ በብልጣ-ብልጥ ገዢዎች እጅ የሕዝብ ማደናገሪዎች ከመሆን አላለፉም፡፡ ነገር ግን በወረቀት ላይ የተቀመጡ ተገቢ መብቶች ይዋል ይደር እንጅ ሕዝቡ ሲነቃ እንዲከበሩለት ስለሚታገል ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ቀስ በቀስ ሥር መስደድ ቋሚነታቸውን መርሳት ስህተት ነው፡፡
ከተሞክሮ እንደተማርነው እንከን-የለሽ የወረቀት ርዕሰ-ህግ በግብር ላይ መዋል የሚፋጠነው ትብብርንና የጋራ ኅላፊነትን ሳይታክቱ ለመብት ዘብ የመቆም ፈሊጥን ማዳበር ነው፡፡ በሰለጠኑት አገሮች ያንዱ መብት መገፈፍ የሁሉም መብት እንደመገፈፍ የሚቆጠረው አፍንጫ ሲመታ ዓይን ማልቀሱ አይቀርም እንደሚባለው ነው፡፡ ይኸ ባሕል በአገራችን ገና ጮርቃ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ለጊዜው ምሽጋቸው በከተሞች የተወሰነው የፖለቲካ ድርጅቶች የገጠሩን መራጭ ማንቃትና መልሶም ከዚህ ሰፊ ሕዝብ ብልህ አስተሳሰብ መማር ግዴታቸው ነው፡፡
ማንኛውም የመንግስት አስተዳደር መብቶችን ሲጥስ እያንዳንዱ ዜጋ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እንዲችል በዓለም-አቀፍ ደረጃ የሚሰራባቸው ስሌቶች በስነ-ስርዓት እንዲመዘገቡለት መጣር አለበት፡፡ ይህ ቃል-ኪዳን የሚደግፈው ርዕሰ-ሕግ በሰብዓዊነታቸውና በዜግነታቸው ብቻ የሚገቧቸውን መብቶች ለጊዜው ስልጣን የያዘ አስተዳደር ሊጥሳቸው እንደማይችል በማያሻማ መንገድ የሚያስቀምጥ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ መብቶች ከበደልና ከፍርሃት ነጻ መሆንን፣ የሕግ የበላይነት መስፈንን፣ የማስብና ሃሳብን በነፃነት መግለጽን፣ በአብይ የአገሪቱ ጉዳዮች ውሳኔ ላይ ተሳታፊ መሆንን፣ ከችጋርና ድንቁርና ነጻ መሆንንና በሁሉም መስክ እኩል መብት ማግኘትን የሚያካትቱ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባትን ርዕሰ-ሕግ ሙሉ ይዘት በቅድሚያ ለመዘርዘር የዚህ የቃል-ኪዳን ሰነድ አላማም ሃላፊነትም አይደለም፡፡ ዳሩ ግን በውል ሊታሰብባቸው የሚገቡ አንዳንድ መሠረታዊ መመሪያዎችን ልንጠቅስ እንወዳለን፡፡ በዚህም መሠረት በዜጐችና በመንግሥት መካከል በግልጽ ውል ሆኖ የሚያገለግል ርዕስ-ሕግ፡-
• በከፍተኛ የሕዝብ ውክልናና ተሳትፎ የሚዘጋጅ፣
• ለሁሉም ዜጐች የፖለቲካ እኩልነትን የሚያረጋግጥና፣
• የሴቶችን ተሳትፎ የሚያበረታታና ሃላፊነትን የሚያጐናጽፍ፣
• መሰረታዊ የኑሮ ፍላጎቶች ካልተሟሉ ሌሎች መብቶች ሁሉ ምንም ፋይዳ ስለማይኖራቸው የነዚህን መብቶች አውራነት የሚያረጋግጥ፣
• ዜጐች በመንግሥት ላይ ያላቸውን የመምረጥ እና እያገለገለኝ አይደለም ብለው ባመኑበትም ወቅት በሰላማዊ መንገድ ከስልጣን የማውድ ሥልጣን በግልጽ የሚያስቀምጥ፣
• የሕግ የበላይነትን የማክበር ባህል በሕዝብና በባለስልጣኖች ዘንድ ሙሉ በሙሉ እንዲሰርፅ የሚያመቻች፣
• የግለሰብ መብቶችን በማይጥስ መንገድ ሁሉንም ባህሎች ካለአድልዎ የሚያጠናክር፣
• ግልፅና አስተናጋጅ ማህበረሰብንና በውድድር ላይ የተመሠረተ የገበያ ኢኮኖሚ ስርዓትን የሚያጎለብትና እንዲሁም
• የመንግሥት ሥራ አገልግሎትን በተመለከተ ግልፅነት፣ ታዛዥነትና ታማኝነት እንዲሰፍኑ ሁኔታዎችን የሚያመቻች መሆን ይኖርበታል፡፡
የምናምንባቸውን መርሆዎች በተግባር ልንተረጉማቸው ይገባል፡፡ ለዚህም ሲባል ነው የፖለቲካ ሥርዓት በህግ የበላይነት ስር እንዲሰፍን የግለሰቦችንና የነፃ ድርጅቶች ንቁ ጥበቃ የማያስፈልገው፤ አምባ ገነኖችም እነዚህን የመብት ሐዋርያዎች ምርኮኛ አድርገው ስልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ ለሕዝብ ለማስረከብ ፈቃደኛ የማይሆኑት፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ርእሰ-መንግስትን በባለቤትነት የሚያቅፈው ዘላቂ ሰላምን፣ የህግ የበላይነትንና ፍትሕን አራማጅ ሆኖ ሲያገኘው ነው፡፡ ስለዚህ አዲሱ ርእሰ-ሕግ ሲረቅ ካለፉት ዘመናት ከተደረጉት ጥረቶችና ልምዶች የተገኙ ትምህርቶችን ያካተተና ከዚህ በታች በተዘረዘሩት መሠረታዊ መመሪያዎች ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት የቃል-ኪዳን ሰነዱ ያምንበታል፡፡ ስለዚህ ተረካቢውና ተከታዩ ትውልድ በባለቤትነት የሚጎናጸፈው መንግስታዊ ስርዓት የሚከተሉትን ይዘቶች ማንፀባረቅ ይገባዋል እንላለን፡-
(ሀ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ግዛት ማስከበር፡-
የኢትዮጵያ ሕዝብ በረዥም ታሪኩ ነፃነቱንና አንድነቱን ጠብቆ በማቆየት በዘር በቋንቋ በሃይማኖት ሳይከፋፈል በማህበራዊ አሩ በቀላሉ የማይበጠስ ዝምድናና ትስስር ፈጥሯል፡፡ በዚህ ሁሉ የታሪክ ሂደት ውስጥ ታዲያ ታፍራና ተከብራ የኖረችውን ሃገራችንን ዳርድንበሯን እና ሉአላዊነቷን በማስጠበቅ ቀደምት አባቶቻችን ለሃገራቸው ክብር ሲሉ የከፈሉትን መስዋእትነት በማሰብ እና በመዘከር ለቀጣይ ትውልድ በማስተማር እና በማሳወቅ አዲሱ ትውልድ በሀገሩ እና በማንነቱ የሚኮራ እንዲሁም በሀገሩ ሉአላዊነት እና ዳር ድንበር ላይ ምንም አይነት ድርድርና ሰጥቶ መቀበል የሚል አስተሳሰብ እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሰውም አንፈልግ የኛንም አንሰጥ የሚለው የዘመናት እምነታችን እንደመለያ ለትውልድ ሊተላለፍ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያና ጐረቤቶቿም የቀጠና ውል በማጽደቅ ቋሚ ሰላምንና ለጋር ጥቅም መዛመድን ማጠናከር ይበጃቸዋል፡፡
(ለ) የግለሰብ መብቶች ቀደምትነት፡-
የዲሞክራሲ ስርዓት ይዘት የሚመነጨው ከግለሰብ መብት ስለሆነ ነፃ ግለሰቦች የሚኖሩበት አገር ደግሞ በምንም መልኩ የቡድንን መብት ሊያፍን የሚችልበት አካሄድ ስለማይፈጥር የብዙሀኑን ጥቅምና የጥቂቶችን መብት ማስከበር በሚችል መልኩ የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህም ሲሆን ግን ማህበረሰቡ የሚጸየፋቸውን ነውሮችን እና ጎጂ ልማዶችን እውቅና አይሰጣቸውም፡፡ “አንድ ዜጋ አንድ ድምፅ” ባለበት የአስተዳደር ሥርዓት፣ ግለሰቦች የፈለጉትን ድርጅት መደገፍ ከመቻላቸውም ሌላ ባህላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸውን ማክበርና ማጎልበት በሚያስችል መልኩ መብትን ያጎናጽፋቸዋል፡፡ ይህም ሲባል ዴሞክራሲ የብዙሃንን ፍላጎትን ብቻ የሚያስተናግድ ሳይሆን የአናሳ ቡድኖችንም መብት የሚያስከብር ስርዓት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
(ሐ) ለሕልውና መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማግኘት ዋስትና፡-
በቂ ምግብ መጠለያና ልብስ ማግኘት የህልውና መስረት ስለሆነ እንደ መሰረታዊ መብት ተቆጥሮ መንግስታት ለዜጎቻቸው የማሟላት ሃላፊነታቸው ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውም መሆኑን አምነው ሲተገብሩት ይታያል፡፡ ስለዚህ በሃላፊነት እና በተጠያቂነት ሕዝብን የሚያገለግል መንግስት (ምንም ደሃ ቢሆን) በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቹ በረሀብ እያለቁ፤ ህፃናት በምግብ እጥረት በረሃብ ህይወታቸው ሲቀጠፍ እና በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ በሽታዎች ሲጠቁ እያየ እንዳላየ የሚያልፍ ህሊና ሊኖረው ስለማይችል ማንኛውም በህዝብ ይሁንታ የተሰየመ መንግስት እነዚህን መሰረታዊ መብቶች የማሟላት ግዴታ ይኖርበታል፡፡
(መ) የሃገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ(ዎች) እንዲኖር ማድረግ
ሐገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች ያሉባት ሃገር እንደመሆ መጠን ህዝቧ ተከባብሮና ተፋቅሮ የመኖሩ ባህላችን እንደተጠበቀ ሆኖ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት ይኖርብናል፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት ሁሉም የሃገሪቷ ዜጎች በየአካባቢያቸው የሚጠቀሙበትን ቋንቋቸውን የመጠቀም እና የማዳበር መብታቸው እንደተከበረ ሆኖ የሀገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማቀላጠፍ የብሔራዊ ቋንቋ(ዎች) መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
(ሠ) የመሬት ባለቤትነት መብትና ዋሰትና
የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ከዜግነት ጥያቄ እኩል ሆኖ መወሰድ አለበት፡፡ ስለሆነም መሬት የግለሰብ መሆን ይኖርበታል፡፡ በግለሰብ ይዞታ ስር ያልሆነ እና በወል ያልተያዘን መሬት መንግስት በአደራ የማስተዳደር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡
(ረ) ያልተማከለ መንግስታዊ ስርዓት፡-
ያልተማከለ መንግስታዊ ስርዓት ሲባል በሀገሪቱ የሚዋቀሩ የራስ ገዝ ክፍላተ ሀገራት የሚኖሩትና አሃዳዊ ያልሆነ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ክፍላተ ሀገራት ታሪካዊ ትስስርን እና መልካዓ-ምድራዊ አቀማመጥን ከግምት የሚያስገባ መሆን ይኖርበታል፡፡ መንግስታዊ አውታሮች የእርስ በእርስ ቁጥጥር እንዲኖራቸው ሆነው መዋቀር ይገባቸዋል፡፡
(ሰ) ሁሉን-ወካይ የፍትህ፡ የወታደርና የሲቪል አገልግሎቶች፡-
መሠረታዊ መብቶች ሊጠበቁ የሚችሉት የሀገሪቱን ማኅበረሰብ ጥቅምና ፍላጎት የሚወክሉ በችሎታቸው የሚመረጡ የወታደር፣ የሲቪልና የደህንነት አገልግሎቶች ሲቋቋሙ ነው፡፡ እነሱም ሁለት መመሪያዎችን ማክበር አለባቸው፡-
1ኛ) የሲቪል አስተዳደሩ፤ የወታደራዊው ተቋም እና የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት የስራ ድርሻቸው በግልጽ በህግ የተደነገገ መሆን ይኖርበታል፡፡
2ኛ) ሁሉም መንግስታዊ ተቋማት በመካከላቸውም ሆነ ከዜጎች ጋር ቅራኔዎች በሚፈጠርበት ወቅት በህግ ፊት እኩል እና ያለምንም ጣልቃገብነትና አድሎ የፍትህን የበላይነት የመቀበል ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡
(ሸ) ነፃና ፍትሃዊ የገበያ ስርዓት፡-
ማንኛውም ዜጋ የግል ንብረቱ ሕጋዊ ዋስትና አግኝቶ በፈለገበት የአገሪቱ ክፍል የመኖር፣ የመስራት፣ በነፃ ገበያ ተወዳድሮ የማምረትና የማትረፍ መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ ውድድር ያለበት የገበያ ስርዓትን ለመገንባት መንግስት ከሚፈጽማቸው ሃላፊነቶች መካከል ዋነኞቹ አድልዎ የሌለበት የውድድር ሥርዓት መፍጠር እና ዋጋን ማረጋጋት ናቸው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም መልኩ የንግድ ስራ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መሳተፍ አይችሉም፡፡ በፓርቲ የተያዙ የንግድ ኩባንያዎች ካሉ ወደፊት በሃገሪቱ የፍትህ ስርአት አማካኝነት አግባብ ያለው ውሳኔ ይሰጥባቸዋል፡፡ መንግስት በየትኛውም መልኩ ከፍርድ ቤቱ የፍትሕ አካካት ውሳኔ ውጪ ተsማቱን ወይም ኩባንያዎቹን የማገድ፤ የመዝጋት፤ የመውረስ ወይም የማዋሃድ ስልጣን አይኖራቸውም፡፡
(ቀ) ነፃና ተጠያቂ የሲቪክ ማህበራት እና የፖለቲካ ፓርቲ ተቋማት፡-
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ውስጥ በተለይም የዝቅተኛውን የማህበረሰብ ክፍል በአጋርነት የሚያገለግሉ በርካታ የሙያ፣ የርዳታ፣ የምሁራን፤ የጋዜጠኞችና የሲቪክ ድርጅቶች አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ በተለይም ስርዓት አልበኝነት ለመግታት ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ምክንያት ማህበራት ከማንኛውም አይነት ተፅዕኖዎችና አፋኝ ሕጎች ነጻ በሆነ መልኩ የመንቀሳቀስ እና የመስራት መብታቸው በህግ ሊጠበቅላቸው ይገባል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶች መሠረታዊ አላማቸው መንግስታዊ ስልጣንን ለመጎናፀፍና በሃገሪቱ ሃብት አያያዝ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ ለማስፈጸም ነው፡፡ ይኸ ሁኔታ ሁለት ጉዳዮችን ያስነሳል፡፡
አንደኛው– ለህዝብ የቆሙትን ወይም በዲሞክራሲያዊ መንገድ በህዝብ የተመረጡትን ለመለየት የጠራ የፖለቲካ የውድድር ስርዓትን መዘርጋት ሲሆን
ሁለተኛው፡- የተመረጠ ፓርቲ ወደ ሙስናና አምባገነንነት እንዳያዘቀዝቅ ማነቆዎች ሆነው የሚያገለግሉ አድልዎ አልባ ተቋሞችን ማጠንከር ነው፡፡
ስለሆነም የሲቪክ ማህበራትን መንከባከብና ንቅናቄዎቻቸው የአገርን እና የህዝብን ጥቅም እስክልተጋፋ ድረስ ማበረታታት አስፈላጊ ነው፡፡
ክፍል ፬
የዲሞክራሲ እድገትና የሲቪክ እንቅስቃሴ መንታነት
የዚህ ቃል ኪዳን ይዘት ለሕዝብ ከሚቀርቡ የተለያዩ የፖለቲካ ስርዓቶች ጋር አይጋጭም፡፡ ዋነኛው ጥሪ ኢትዮጵያዊያን ካለምንም ተጽዕኖ ከዘመኑ ምኞታቸውና ከክብር ባህላቸው ጋር የሚጣጣመውን የአስተዳደር ስርዓት የመምረጥ መብታቸው ይጠበቅ የሚል ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥሮ ባህሪያቸው ስልጣን ለመጎናፀፍ በመሆኑ እድልዎ-አልባና የተደላደለ የውድድር መስክን ለማመቻቸት ነው፡፡ የፖለቲካና የህግ ተቋሞች ግንባታ ትክክለኛ ፈር እስከያዘ ድረስ የሕዝብ አለኝታ በእነዚህ ተቋዋማት ላይ በአንድ ጊዜ የሚፈጠር ሳይሆን በሂደት መዳበር እንደሚኖርበት ማስታወስ ለትግስት ይረዳል፡፡
የአሁኑ ትውልድ በዓለም ነፃ ሕዝቦች ማህበረሰብ ውስጥ የሚገባውን ቦታ እንዲያገኝ ለማድረግና የእጣውን ባለቤትነት ለማሳወቅ ቋሚ የነፍስ-ወከፍ እንቅስቃሴ ማድረግ ዋና ቁልፍ ነው፡፡ ምንግዜም የማይታክቱት የኢትዮጵያ ልጆች መብታቸውን ለማስከበር “አገርህን አድን” ርብርብ ላይ ቸል እንደማይሉ እምነታችን ነው፡፡

ኢትዮጵያ በልፅጋና በልጆችዋ ተከብራ በነፃነት ለዘለዓለም ትኑር!

Filed in: Amharic