>

ወንጀላቸው በሕይወት መትረፋቸው ይሆን? (ጌታቸው ሽፈራው)

ወንጀላቸው በሕይወት መትረፋቸው ይሆን?
ጌታቸው ሽፈራው
ዐቃቤ ሕግ  በእነ ጄ/ል ተፈራ፣ ኮ/ል አለበል……እና ሌሎችም ላይ፣ በቅድመ ምርመራ ክስ ላይ ምስክሮችን አሰምቷል። ከተጠርጣሪነት ወደ ምስክርነት ከተዛወሩት መካከል አንደኛው ኮ/ል አለባቸው ነው። ኮ/ል አለባቸው “የማውቀውን እመሰክራለሁ” ቢልም እነሱ የሚፈልጉትን መስክር ሲሉት “ሀምሳ አመቴ ነው። በዚህ እድሜዬ በንፁሃን ላይ በሀሰት አልመሰክርም” ማለቱ ተሰምቷል። በዚህም ምክንያት ሶስት ቀን ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኝ ተደርጓል። ፍርድ ቤት መቅረብ ሲኖርበት እንዳይቀርብ ሆኗል።
በቅድሚያ ምርመራ ክስ ላይ በ15 ተጠርጣሪዎች ላይ አምስት ምስክሮች ቀርበዋል። 15 ተከሳሾች  ላይ የተመሰከረው  የሚያስከስስ አይደለም። ለዛም ይመስላል እነ ኮ/ል አለባቸው ምስክር ሁኑ የሚባሉት።
በተለይ ኮ/ል አለበል አማረ እና ኮ/ል ባምላኩ አባይ ሊገደሉ ጊዜ ተቆርጦላቸው እንደነበር ምስክሮቹ አረጋግጠዋል። ስራ አመራር የሚባለው ተቋም ውስጥ ታግተው በነበረበት ወቅት “ፊተችሁን አዙሩ” ተብለው ተቀምጠው ሊገደሉ እንደነበር፣ እርምጃውን ውሰዱ ከተባሉ አካላት መካከል የተወሰኑት ባለመስማማታቸው እንደተረፉ ተገልፆአል። “ግደሏቸው” ተብለው የነበሩት የፀጥታ አካላት “አንገድልም” ሲሉ “አንተ ትጠየቃለህ፣ አንተ ትጠየቃለህ” እየተባባሉ ክርክር ውስጥ እንደነበሩም ለመወቅ ተችሏል።  በዚህ ጭቅጭቅ መሃል “አንገድልም” ያሉት ተሰሚነት ስላገኙ በሕይወት ተርፈዋል። ሆኖም በሕይወት መትረፋቸው እንደወንጀል ሳይቆጠርባቸው አልቀረም! ታዲያ  እነዚህ ሰዎች ወንጀላቸው በሕይወት መትረፋቸው ካልሆነ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?
Filed in: Amharic