>
5:13 pm - Wednesday April 19, 2524

አፍራሽ የተላከባት፤ እሳት የተለኮሰባት ቤተ ክርስቲያን በወርኃ ሐምሌ!!!  ( ዲ/ን አሻግሬ አምጤ)

አፍራሽ የተላከባት፤ እሳት የተለኮሰባት ቤተ ክርስቲያን በወርኃ ሐምሌ!!!
  ዲ/ን አሻግሬ አምጤ
እውነተኛይቱን እምነት ናቁ፤ መንገዷንም አቃለሉ መቅደሱንም እነሆ እንደ ዱር እንጨት ሰባበሩ በእሳትም አቃጠሉ ” 
 መዝሙረ ዳዊት ፥ 73
 ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአባቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት የተወገደበትን በአል በሚሊንየም አዳራሽ በማክበር ላይ በነበርንበት ወቅት በጅግጅጋ ሀገረ ስብከት አሥር አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለው፣30 የሚሆኑ ምእመናን ተገድለው ነፍሰ ጡሮችን ጨምሮ 100 የሚሆኑ ሴቶች መደፈራቸውን ሰማን።
በያዝነው ዓመት ደግሞ ሲዳማ ዞን ክልል ይሁንልን በሚል መነሻ  ከሐምሌ 11 እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም  ለሦስት ቀናት በተደረገ ረብሻ በሲዳማ፣ጌዴኦ፣አማሮና ቡርጅ ዞኖች  ሀገረ ስብከት በሁላና ቦና ዙሪያ ወረዳ አብያተ ክርስቲያን መቃጠላቸውን፤የምእመናን  ሕይወት ማለፉን፤ንብረታቸው መዘረፉን እና ከዘረፋ የተረፈው መቃጠሉን በሀገረ ስብከቱ የተቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ ማረጋገጡን አዋሳ ማእከል ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ዶያ ቅዱስ ሚካኤል፣ገታማ ገብረ ክርስቶስ እና ጭሮኔ ቅዱስ አማኑኤል ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውንና፣ሉዳ ቅዱስ ገብርኤል፣ሀገረ ሰላም ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፣ሀገረ ሰላም ቅድስት ሥላሴ፣ጭሪ ቅዱስ አማኑኤል እና ቀጨኖ ቅድስት ማርያም በከፊል የተቃጠሉ መሆናቸውን  ስንሰማ ቤተክርስቲያን በየዘመናቱ የምትቀበለውን ሰማዕትነት እንድንረዳ ያደርገናል።
በ1947 ዓ.ም የተመሠረተው  ዶያ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለጥፋት በተሰለፉ አካላት ሙሉ በሙሉ የተቃጠለ ሲሆን የአጥቢያው ምእመናን በሃይማኖት ተለይተው ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ የአሥር አባ ወራዎች ንብረት ተዘርፎ ቀሪው እንደተቃጠለ፤የ18 አባወራዎች ንብረት ተቃጥሎ መፈናቀላቸውን፣138 ንዋያተ ቅድሳት ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን፣ በጥፋት የተሳተፉት 91 ሰዎች መሆናቸውን  እና ከታቦተ ሕጉ እና ከአንድ የብራና መዝሙረ ዳዊት በቀር የተረፈ አለመኖሩን  ስንሰማ የስንዱዋን እመቤት ጽንዓት ተረድተን በሃይማኖት እንድንጸና የሞተ መንፈሳችንን ይቀሰቅሰዋል።
ገታማ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በ2008 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ከኅዳር 10 ቀን 2010ዓ.ም ጀምሮ አገልጋሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በአጥቢያው ሥር የሚገኙ የ13 አባወራዎች ንብረት ተዘርፏል፤ የ20 አባወራዎች ንብረት ተቃጥሏል፤70 ንዋያተቅድሳት ተቃጥለዋል፤33 አባወራዎች ተሰደው በየሰው ቤት ተጠልለዋል ተብሏል። ይህም የክርስቲያኖች ሕይወት ዕለት ዕለት በሰማዕትነት የደመቀ መሆኑን እንገነዘባለን።
አጥፊዎች የጭሮኔ ቅዱስ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያንን ልብሰ ተክህኖ እና የሰንበት ተማሪዎችን አልባሳት ለብሰው፣የካህናትን አክሊል ደፍተው፣የእጅ መስቀላቸውን ይዘው እየዞሩ ሲጨፍሩ ከቆዩ በኋላ  ቤተ ክርስቲያኑንም ንዋያተ ቅድሳቱንም ማቃጠላቸውን፣ የሉዳ ቅዱስ ገብርኤል እና የጭሮኔ ቅዱስ አማኑኤል ታቦተ ሕግ እስከ አሁን የት እንዳለ እንደማይታወቅ ስንሰማ ደግሞ የአጥፊዎችን ጭካኔ በተመለከትንበት የእግዚአብሔርንም ትዕግሥት ተረድተን እናደንቃለን።
በ1928 ዓ.ም  የተመሠረተው ሉዳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ተቃጥሏል፤በሮቹ፣መስኮቶቹ እና  ወንበሮቹ ተሰባብረዋል። ደጀ ሰላሙም ሙሉ በሙሉ ወድሟል ተብሏል።
ሀገረ ሰላም ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በ1909 ዓ.ም በደጃዝማች ባልቻ ሳፎ( በፈረስ ስማቸው ባልቻ አባ ነፍሶ) የተመሠረተች ናት። ጉዳት የደረሰበት ለሁለተኛ ጊዜ በ1968 ዓ.ም የታነፀው ቤተ ክርስቲያን መሆኑን፣  ሦስት ምእመናን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፣250 ምእመናን ደግሞ በቦሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን መጠለላቸውን፣በአጠቃላይ በደብሯ 603 ምእመናን ተጠልለው እንደሚገኙ መረጃው ያመለክታል። በተፈጠረው ረብሻ 765 ሰዎች መፈናቀላቸውን የማእከሉ መረጃ  ሲያመለክት  በአንድ በኩል የአጥፊዎችን አለመርካት በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ከደረሰባት የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባት ራሳቸውን ለአደጋ ያጋለጡትን፣የተበተኑትን ለመሰብሰብ  የቦሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ፣የደብሩ ምእመናን እና እስላም ክርስቲያን ሳይሉ የከተማዋ ነዋሪዎች  በጎ  ማድረጋቸውን ስንሰማ ዘመን የራሱን ሰማዕታት  እና በመንፈሳዊ ልዕልና አልጫውን  ዓለም የሚያጣፍጡ ሰዎች እንደሚያፈራ እንረዳለን።
እግዚአብሔር ለቅድስና ስፍራው ለማደሪያው ይዋጋል!
ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔር ን ቤተ መቅደስ ለማነጽ ከነብዩ ናታን ጋር ሱባኤ ገብተው ልምላሜ በሌለበት ዋእይ በበረታበት በበረሀ ወድቀው በጸለዩ ጊዜ የምድራዊዉ መቅደስ ለናታን፤ አማናዊቷ መቅደስ እመቤታችን ለቅዱስ ዳዊት ተገለጸችለት።
ዛሬ ቅድስት ቤተክርስትያናችንን መቅደሱን እናከብረዋለን፤ በመቅደሱ እንገዛለታለን፤ ማደሪያው ነውና እንሰግድለታለን።
ዳዊት በመዝሙር 73 የመቅደሱን ነገር ይናገራል፦
መቅደሱን ለማቃጠል ሰዎች እንዴት እንደተነሱ፤ አንድ ላይ ሆነው በየህዝባቸው በየወገናቸው ተጥራርተው መቅደሱን በመዶሻ በመጥረቢያ እንደሰባበሩ ሲያትት “አንድ ላይ ሆነው መጡ ከእንግዲህ ነብይ የለም አሉ እውነተኛይቱን እምነት ናቁ፤ መንገዷንም አቃለሉ መቅደሱንም እነሆ እንደ ዱር እንጨት ሰባበሩ በእሳትም አቃጠሉ ” ይላል
ጠላቶች በበአል (በጣኦቶቻቸው) ተመኩ፤ የማያውቀትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ።
እነሆ ወገኖች ሳሉ ጠላት ሆነው ተነሱ  የከንቱ አጋንንትን ምልክት ለራሳቸው አደረጉ፤  የእግዚአብሔርንም መታሰቢያዎች የክብሩንም መገለጫዎች ከምድር እንሻር (እናጥፋ) አሉ።
ዛሬ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን፦
ምልክቷ መስቀል ነው
ምልክቷ ደሙ ነው
ምልክቷ መቅደሱ ነው
ምልክቷ ማህተሙ ነው
ጠላት ግን ስለ ጥፉቷ በየወገኑ በየጎጡ ተሰባስቦ ተነስቷል። አዎ ዛሬም ጠላት በቅዱሳኑና በማደሪያህ ላይ እንደ ክፋታቸው መጠን እንደ ትእቢታቸ ልክ ተነስተዋል። ማደሪያህን አቃጥለዋል። መታሰቢያህንም ከምድር አጥፍተዋል እነሆ አንተ በሀይል ተነስ እጅህንም አንሳ!!!
ምእመናንም የእግዚአብሔርን ትዕግስት እያደነቁ፣ በጸሎት እየበረቱ  ቤተ ክርስቲያንን  ነቅተው መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
Filed in: Amharic