>
5:13 pm - Wednesday April 18, 9696

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የኦጋዴኑ የበረሀው መብረቅ (ያሲን ወዳጄ ነህ)

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የኦጋዴኑ የበረሀው መብረቅ
ያሲን ወዳጄ ነህ
በኦጋዴን ካልካዩ በተባለች ቦታ 1871 የተወለዱት ታላቁ ጀግና ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ለእናት አገራቸዉ ነፃነት ከወራሪዉ የፋሽስት ጦር ጋር ከተዋደቁት ጀግኖች አርበኞች አንዱ ናቸው።
ፋሽስት ኢጣሊያ አገራችንን ለመዉረር የመጀመሪያዉን ጥይት የተኮሰችዉ በወልወሉ ግጭት ነበር። ነገሩ እንዲህ ነበር የሆነው…
የኢትዮጵያ መንግሥትና የዛኔ የሰሜን ሱማሊያ ቅኝ ገዥ የነበረችዉ ታላቌ ብሪታኒያ የድንበር ማካለል ለማድረግ ከኢትዮጵያ በኩል ፊታዉራሪ ተሠማ በንቴ ከታላቋ ብሪታኒያ በኩል ደግሞ ኮ/ል ክሊፎርድ ቀን ቆርጠዉ ወልወል ሲደርሱ የኢጣልያው ጦር አዛዥ ካፒቴን ሮቤርቶ ቺማሩታ አላሳልፍም በማለቱ በተፈጠረዉ ግጭት ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰዉ አለቀ።
የኢትዮጵያና ኢጣሊያ ጦርነት የመጀመሪያ ጥይት ተተኮሰ። ይህም የኢጣሊያ ሀገራችንን ለመውረር የተኮሰው የመጀመሪያው ጥይት ሆነ።
በዚህ ጊዜ ነበር ደጃች ዑመር ሰመተር ከቆራሄዉ ጀግና ከደጃዥማች አፈወርቅ ወ/ሰማያት ጋር የተቀላቀሉት። ደጃች ዑመር ሰመተር የሚመሩት የሱማሌ ጦር ጎርበሌ በተባለች ቦታ መሽጎ የጠላት ጦር በማጥቃት ከፍተኛ ድልን ተቀዳጀ።
በዚህ ድል የተደናገጠዉ የፋሽስት ኢጣሊያ መንግስት በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ላይ ኢትዮጵያን በመክሰስ ካሳ እንዲከፈለዉና ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ተላልፈዉ እንዲሰጡት ጠየቀ።ሽንፈቱ ያንገበገበዉ ፋሽስት ስድስት ባታሊዮን ጦር ልኮ ኤል ቡሬን ከበበ።የሁኔታዉ ክብደት የገባቸዉ ደጃዝማች ዑመር አፈግፍገዉ ለአምስት ወራት ጦራቸዉን ሲያዘጋጁ ቆዩና ፋሽስት ባልጠበቀዉ ሰዓት ደርሰዉ ያንን ስድስት ባታሊዮን ጦር ከጥቅም ዉጪ አደረጉት።በድል እየዘመሩም ሸላቦ ገቡ።ጠላት ግን አርፎ አልቀመጥ ብሎ ይተነኩሳቸዉ ጀመር።በዚህም ሸላቦ ላይ አይቀጡ ቅጣት ቀጡት።
በማስከተልም ወደ ቆራሄ ሄደዉ ገጠሙትና ድል አደረጉ። ሽንፈቱ የተደጋገመበት ጠላት በከፍተኛ ሁኔታ ተደራጅቶ መጣ።ጉርለጉቤ በተባለች ቦታ ላይ ከፍተኛ ጦርነት ተካሂዶ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በስድስት ጥይቶች ተመተዉ ክፉኛ ቆሰሉ።እስከ ነፃነትም ህክምናቸውን በውጭ ሲከታተሉ ቆይተው ከነፃነት በጏላ ወደ አገራቸዉ ቢመለሱም የጥይቱ ቁስል እያመረቀዘ ጤና ሲነሳቸዉ ቆይቶ መጋቢት 10 ቀን 1936 ዓ.ም በተወለዱ 61 ዓመታቸዉ አረፉ።
ባላምባራስ ዓብዶ ሀይድ የተባሉ የትግል አጋራቸዉ በቀብራቸው ላይ እንዲህ ብለዉ ነበር:-
.
ተገዳይ እወልወል እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ አፍዱግ ላይ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ቆራሄ እጠረፉ ዳር፤
ተጋዳይ ሀነሌ እጠረፉ ላይ፤
የመትረየሱ ሼክ የለበን መምህር፤
ሞት ጠራህ አንተንም ዑመር ስመተር!!!
ክብር ይህቺን ውድ ሃገር በደማቸው ላቆዩልን ጀግኖች አባቶቻችን
Filed in: Amharic