>
5:13 pm - Tuesday April 18, 2017

የተዓማኒነት ጉድለት ያለበት መንግሰት ….. [ኣቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ]

መንግሰት የሚባለው ነገር ምን እንደሆነ ግራ ገብቶኋቸው ግራ የሚያጋቡን የመንግሰት ኃላፊዎች ያሉበት ሀገር ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ በሃላፊነታቸው ደረጃ የሚመጥን ማስተካከያ ለመውሰድ አቅምም ፍላጎትም የላቸውም፡፡ የተሸከሙት ሃላፊነት መንግሰት ብለው ለሚያስቡት አንድ ግዑዝ ነገር ለአገልጋይነት እንጂ፤ እነርሱ የመንግሰት አካል እንደሆኑ አይረዱትም፡፡ ይህን እንድንል የሚያደርገን መንግሰታችን ብለን በኩራት ግብር የምንከፍለው፤ መንግሰታችን ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም አንዲገቡ የሚያደርግልን ተቋም ነው፤ ሀገራችን በልማት በልፅጋ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ስርዓት ነው፣ ይህ ሁሉ ሆኖም ችግር ቢገጥመን በገለልተኝነት በፍትህ ስርዓት ዳኝነት የምናገኝበት ነው፤ ብለን ማመን ቢቸግረን ነው፡፡ እነዚህ የመንግሰት ሃላፊ ተብዬዎች እነርሱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ሲያቅታቸው እኛ በእንድ ወይም በሌላ መንገድ ችግራቸውን በጠቆምናቸው ወደ ትክክለኛ ደረጃ ማደግ ትተው እኛ ወደ እነርሱ እንድንወርድ፣ እንድንዋረድ፣ ለሆዳችን እንድናድር ወደ ገደል ይጎትቱናል፡፡
እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ መንግሰት የሚባለውን አካል ለመደገፍ፤ በህግ የተሰጠውን ተግባር አንዲወጣ ማገዝ እንደ ዜጋ መብቴ ነው ብቻ ሳይሆን እንደ ግዴታም የምመለከተው ነው፡፡ አሁንም የማደርገው ነገር ሁሉ የማድረገው በዚሁ መንፈስ ግዴታዬን ለመወጣት ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሚደረግለትን ድጋፍ መቀበል የማይችል መንግሰት ሆኖዋል፣ ልክ ጥሩ ምግብ ሲያጎርሱት እንደሚያስመልሰው በከፍተኛ ደዌ እንደተያዘ በሽተኛ፣ ወይም ቤት እንዲጠብቅ ጠላት ሲመጣ እንዲያነቃን ያሳደግነው ውሻ በተቃራኒው ቤተኛውን በሙሉ መናከስ እንደጀመረ ውሻ ሆኖዋል፡፡ መንግስት ምክር አይሰማም ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው ምክር የሚሰጡትን ለማጥፋት በከፍተኛ ትጋትና ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ነው እየተሰማን ያለው፡፡ ይህ ድርጊቱ በቀጣይ ዜጎች ከመካሪነት ወጥተው ሀገርን ወደማይጠቅም አውዳሚ አማራጭ መስመር እንዲገፉ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እሰከ አሁን የተገፉትን ሳይጨምር፡፡
ዛሬ የመረጥኩትን ርዕስ እንድመርጥ ያደረገኝ መንግሰት ሰሞኑን እያሳየ ያለው ባሕሪ ነው፡፡ መቼም መንግሰት የሚገለፀው በመንግሰት ሃላፊዎች ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሰትን የሚመሩት ግለሰቦችም ሆኑ አካላት በመንግሰት ሃላፊነት ላይ የሚመድቧቸውን ሰዎች በህዝብ ፊት እንዲቀሉ ማድረግ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች እንዲቀሉ ሲያደርጉ የሚቀሉት አበረው መሆኑን እንዲሁም መንግስት የሚባለውን ሰርዓት የሚመራው አካል ጭምር ነው፡፡ እራሱ የሾመውን አካል ጭምር ማለት ነው፡፡
ይህን ሀሳብ ያነሳሁት አቶ ጌታቸው ረዳ የተባሉ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቃል አቀባይ “መንግሰት አቶ አንዳርጋቸውን አልተረከበም” ብለው በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ለህዝብ ይፋ አደረጉ፡፡ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል በመግለጫው “የየመን መንግሰት እንዲይዛቸው አደረግን የዚያኑ ዕለት ተረከብናቸው” አለ፡፡ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ጅግንነቱን ለመግለፅ የመንግሰት ቃል አቀባዩን ማዋረድ ለምን አስፈለገ? ከዚህ ቀደም እንደልምድ ሆኖ የመንግሰት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ከፍተኛ ሹም የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ሆን ተብሎ በሚመስል ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ተቃርኖ ያለበት አሰተያየት እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳም እኝህን ከፍተኛ የመንግሰት ሹም የሚያምን ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ግለሰቦችን የማዋረድ ድርጊት መንግሰትን የሚጠቅመው እንዳልሆነ ግን ግልፅ መሆን አለበት፡፡ የመንግሰትን አቋም እንዲነግሩን የተመደቡ ሰዎች “አይታመኑም” ማለት አጭር እና ግልፅ በሆነ ቋንቋ “መንግስት አይታመንም” ማለት ነው፡፡ የተዓማኒነት ጉድለት ያለበት መንግሰት ሲመራን ደስ አይለንም፤ ለዚህም ነው መንግስት አንዲታመን የምንወተውተው፡፡ ይህ የምንሰጠው አሰተያየት በምንም መልኩ የሀገርን ገፅታ ማበላሸት ሳይሆን፤ ሀገራቸንን ወክለው የሚዋሹትን የመንግሰት ሹማምንት በመምከር ለሀገር ገፅታ ግንባታ መትጋት ነው፡፡ ብንዋሽም ለሀገር ገፅ ግንባታ ሲባል ዝም በሉን ከሆነ መርዕ አልባነት ስለሚሆን መስማት ቢቻልም መስማማት አይቻልም፡፡ ያለምግባባታችን ምንጩ በመርዕ ጉዳይ ያለመስማማት ነው፡፡
የመንግስ ተዓማኒነት የሚጎዱ ብዙ ድርጊቶች ማንሳት ቢቻልም፤ አሁን ደግሞ የፓርቲያችን አባል የሆነውን ሀብታሙ አያሌውን በምንም ምክንያት ቢይዙት መንግሰትን ለመማን በፍፁም ዝግጁ አይደለንም፡፡ መንግሰት ሁሌም እንደሚለው ክምር ማስረጃ አይደለም አንድ ገፅ ማስረጃ ያቀርባል ብለን አንጠብቅም፡፡ ይህን ለማለት የሚያሰደፍር በቂ ተሞክሮ አለን፡፡ ከብዞዎቹ አንዱ አንዱዓለም አራጌን ለእስር ያበቁበት መረጃ ነው፡፡ በህይወቴ ከደነገጥኩበት ቀን አንዱ አንዱዓለም አራጌ የታሳረ ዕለት ነው፡፡ ምከንያቱም የቀረበበት ክስ “ከግንቦት ሰባት” ከሚባለው “ሁሉን አቀፍ” የሚበል የትግል ስልት ከሚከተል በውጭ ሀገር ከሚገኝ ፓርቲ ጋር ግንኙነት አለው የሚል ስለ ነበር ነው፡፡ በወቅቱ አንዱዓለም አራጌ ላይ የሚያቀርቡትን መረጃዎች በጉጉት ነበር ስጠብቅ የነበረው፡፡ ነገር ግን አንድም ማስረጃ ሳይቀርብበት፣ አዳፍኔ ምስክሮችም እንደሰለጠኑት አሟልተው ሳይመሰክሩ የሰላማዊ ትግል ጓዳችን “በአሸባሪነት” ጥፋተኛ ነው ተብሎ እድሜ ልክ ተፈረደበት፡፡ ከዚያን ቀን ወዲህ ማንም ላይ ማስረጃ አለኝ ቢሉ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ መንግሰት በሚፈፅማቻው ተግባራት ምክንያት ተዓማኒነቱን እየጎዳው ይገኛል፡፡ ቀበሮ መጣ እንደሚለው ውሽታም እረኛ ማለት ነው፡፡
በእኔ እምነት ከሳሾቹም ሆነ ፈራጆቹ የሰጡት ውሳኔ “ክምር ማስረጃ” አለን ያሉትን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቃል ለማክበርና ለማስደሰት እንደነበር መጠራጠር አያሰፈልግም፡፡ እርሳቸውም ደስታቸውን ሳያጣጥሙት በተፈጥሮ ህግ ተለይተውናል፡፡ የቀረበውን ክምር ማስረጃ ታሪክ መዝግቦ ይዞታል ከሳሹችም ሆኑ ፈራጅች በታሪክ ፍርድ ፊት እንደሚቆሙበት ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ አሁን በምንፅፈው፣ በምንናገረውም ሆነ ከዚህ በፊት በያዝነው አቋም ሁላችንም የታሪኩ አካል ነን፡፡ ሊፈርድብን ወይም ሊፈርድልን፡፡
የዛሬ ዓመት አካባቢ በደሴ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማስተባበር ከተመደበ ቡድን ጋር ተንቀሳቅሼ ነበር፡፡ ወቅቱ ደግሞ አንድ የሙስሊም የሀይማኖት አባት የተገደሉበት ነበር፡፡ በወቅቱ በደሴ ከተማ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር አብዛኛው የከተማ ነዋሪ “የሀይማኖት አባቱን የገደላች መንግሰት ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በሰልፍ ላይ የተገኙ ሰዎችም “እየገደሉ ገደሉ አሉን” የሚል መፈክር በከፍተኛ ሰሜት እያሰሙ ቅሬታቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ በግሌ መንግሰት በዚህ ደረጃ ወርዶ በግለሰቦች ግድያ መጠርጠሩ ምቾት አልሰጠኝም፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ያገኘኋቸውን የመንግሰት ሹሞች በዚህ ደረጃ መንግሰት መጠርጠሩ እንደሚያሳዝን አሁንም ቢሆን መስራት ያለባቸው የተቃዋሚዎች ስራ ነው እያሉ በአላስፈላጊ ፕሮፓጋንዳ ከሚጠመዱ፤ መንግሰትን በዚህ ደረጃ ለመጠርጠር ገፊ የሆነው ችግር ምንጭ ምን እንደሆነ እንዲመረምሩ አሳቤን አካፍያቸው ነበር፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ እኔንም ከአሽባሪና አክራሪነት ጋር ደምረው ልወደድ ባይ ጋዜጠኞች ዶክመንተሪ ፊልም ሰሩብኝ፡፡ ሀይ የሚል አልነበረውም ይልቁንም በተለያየ አጋጣሚ የማገኛቸው ኢህዴጎች የኢቲቪን ድራማ እያዩ እኔን መኮንን ነው የያዙት፡፡ እኔን በዚህ ደረጃ ከመጠርጠር እራሳቸውን መጠርጠር የሚቀላቸው ይመስለኛል፡፡ የእኔ ጥያቄ መንግስት ለምን በዚህ ደረጃ ይጠረጠራል? የመንግሰት ተዓማኒነት መጎደልን ለማሳየት ከዚህ የተሻለ ማስረጃ ማቅረብ ይከብዳል፡፡ እንዴት መንግሰት በግለሰብ ግድያ ይጠረጠራል? ሹሞቹ ግን ይህ አላሳፈራቸውም ቅድሚያ የሰጡት ለፕሮፓጋንዳው ነው፡፡
የተለያዩ ሀገሮቸን ለመጎብኝት እድል አጋጥሞኛል መንግስት ሊገድልህ፤ ሊያስገድልህ፤ በማጅራት መቺ ሊያስመታህ ይችላል ተብሎ የሚታመንባቸው ሀገሮች እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የወደቁ ወይም በመውደቅ ላይ ያሉ መንግሰታት ናቸው፡፡ የሀገሬ መንግሰት እንዲህ እንዲሆን አልፈልግም፡፡ እንዲህ ዓይነት ግምት የሚሰጡ ሪፖርቶች ሲወጡ መንግትን ስለማልደግፍ ጮቤ አልረግጥም፡፡ ይልቁንም አዝናለሁ፡፡ በቅርቡ አንዲት ሴት መኖሪያ ቤቴ ድረስ መጥታ በከፍተኛ የመንግሰት ሹም ፆታዊ በደል እንደደረሰባት ነገረችኝ፡፡ ለነገሩ ጉዳዩ የግል ግንኙነት ከመሆኑ አንፃር ብዙም ፍርድ ቤት የሚያስኬድ ባሕሪ እንዳለው ባይገባኝም፤ የተነፈገ መብት አለኝ ካለች ፍርድ ቤት እንድትሄድ ነገርኳት፡፡ “ፍርድ ቤት ብሄድም ትርጉም የለውም፤ ይህን ማድረጌን ከሰሙ ያስገድሉኛል፤ አንተ በደንብ አታውቃቸውም አለቸኝ፡፡” ደነገጥኩ!! እውነት ነው ከሷ በላይ አላውቃቸውም፤ በግልፅ አንሶላ ተጋፋ ውስኪ ተራጭታ የሚያደርጉትን ታውቃለች፡፡ በመጨረሻም ከእኔ የምትፈልገው ነገር እኔ ላድርግላት እንደማልችል፤ እኔም ከመስመር አልፎዋል ያሉ ቀን ሊገድሉኝ፣ ሊያስገድሉኝ ካዘኑልኝ ደግሞ እስር ቤት ሊወረውሩኝ እንደሚችሉ አምኜ በድፍረት እንደምንቀሳቀስ ነገርኳት፡፡ ይህን ታሪክ ያነሳሁት መንግስት ከለላ የሚሰጠን ጠባቂያችን ሳይሆን ሊገድለን፣ አደጋ ሊያደርስብን የሚችል ነው ብለን ተዓማኒነት እንድንነፍገው ለምን ሆነ? ብዬ ለመጠየቅ ነው፡፡ የመንግሰት ተቃዋሚ ሆኖ አይደለም፤ መንግሰትን ከሚወክሉት ሹሞች ጋር ሲዳሩ መክረም እንደ ውለታ ተቆጥሮ ዋስትና አይሆንም፡፡ የፈለጉ ቀን ከህግ ሰርዓት ውጭ ማሰገደል የሚችሉ ናቸው፡፡ መንግሰትን የሚወክሉት ሹሞች፡፡ ግን ለምን አንዲህ ሆነ?
መንግሰት ለሚያደርጋቸው ነገሮች፣ ለሚወሰደው እርምጃ ተገማችነት አለመኖር ለተጠርጣሪነት እና ተዓማኒነት ጉድለት እንደሚያጋልጠው እርግጥ ነው፡፡ ይህን መከላከል ሲገባ ደግሞ ይህን የሚያጠናክሩ ድርጊቶችን በተደጋጋሚ ማየት መንግሰት ተዓማኒ አይደለም ብቻ አይደለም አንድ አንድ ሰዎች በድፍረት እንደሚሉት “መንግሰታዊ ውንብድና” ነው፡፡ ያሰገድሉናል የሚባል አቋም ሲያዝ ፍርድ ቤት አቅርበው አንዳለሆነ ግልፅ ነው፡፡ በአህአዴግ መንግሰት ከሁለት ሰዎች በላይ በህግ ውሳኔ በሞት የተቀጣ እንደሌለ እናውቃለን፡፡
ይህንን “የመንግሰትን ተዓማኒነት ጉድለት” የሚመለከት ፅሁፍ እያዘጋጀሁ ሳለ የግሌ አስተያየት እንዳይሆን የፌስ ቡክ ጓደኞቼ አስተያየት እንዲያዋጡ መጠየቅ ፈለጉህ፡፡ እንዲህም ብዬ በፌስ ቡክ ላይ ለጠፍኩ “እባካችሁ የመንግሰትን ተዓማኒነት ጉድለት የሚያሳይ አሳብ አዋጡ!! ከሌላችሁ በእውሽት ላይ የተመሰረተ ክስ ወይም ጠቅላላ አስተያየት ተቀባይነት የለውም፡፡ አመሰግናለሁ ……” የሚል ነበር፡፡ ተቀባይነት የሌላቸው አጠቃላይ አሰተያየቶችን ጨምሮ እጅግ ብዙ አስተያየት በአጭር ጊዜ ቀረበልኝ፡፡ በመሰረታዊነት ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግሰታዊ ሰርዓቱን እንዲያከብሩ የሚጠይቅ ሲሆን፤ በግልፅ ምሳሌ ተደርገው ከተጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግስት ባድመን አሰመልክቶ የተሰጠው መግለጫ፣ ዜጎች መንግሰት ላይ እምነት ቢኖራቸው በሚሊዮን ለምን ይሰደዳሉ?፣ ኢቲቪን ተመልከት፣ ፍርድ ቤቶች ምን እየሰሩ ነው፣ የደህንነት ተቋም ለማን ነው የሚሰራው? ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ነው ብለህ ታምናለህ? የሚሉና ከነአካቴው መንግሰት አለ ወይ? የሚሉት ይገኙበታል፡፡ አሰተያየቶቹ ሁሉንም የመንግስት አካላት የዳሰሱ ናቸው፡፡ መንግሰት ዜጎች በዚህ ደረጃ ተዓማኒነት እንዲነሱት ለምን ይተጋል ብለን መጠየቅ የለብንም ትላላችሁ?
ምኞቴ መንግሰታቸን ብለን የምናከብረው መንግሰት አንዲኖረ ነው፡፡ ግልፅ ነው በአሁኑ ስዓት የለንም እያልኩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚገለፀው መንግሰትን ወክለው በሚታዩት ሹማምንቶች ባህሪና ተግባር ነው፡፡ የሀገርን ገፅታ ለመግንባት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ኃላፊነት እንዳለብን እና ግዴታችን እንደሆነ ባምንም ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ግን ያለምንም ማወላወል በተግባር ሊያውል የሚገባው እና ሞዴል ሊሆነን የሚገባው መንግሰት ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ በኃላፊዎቹ ይወከላል፡፡ የእኛ ተግባር ትክክለኛ ስራ ሲሰሩ ሞዴሎቻችን አድርገን መውስድና ትክክለኛ ተግባራቸውን ማስፋት፤ ካልሆነ ደግሞ ያልሆኑትን ናቸው ብለን መቀለድ ሳይሆን አትመጥኑንም ብለን መንገር ነው፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ!!!!!

ቸር ይግጠመን

Filed in: Amharic