>

የእነ አብርሃም ወልዴ "የሰላም ፌስቲቫል" ና  የ"ብሄር ብሄረሰቦች" ጭፈራ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ!!! (ሳምሶን ጌታቸው)

የእነ አብርሃም ወልዴ “የሰላም ፌስቲቫል” ና  የ”ብሄር ብሄረሰቦች” ጭፈራ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ!!!
ሳምሶን ጌታቸው
እነ አርቲስት አብርሃም ወልዴ “የሰላም ፌስቲቫል” እናደርጋለን እያሉ ነው። ፌስቲቫል ማለት ባጭሩ አንድ የባህል ወይም የሐይማኖት ወይም የስፖርት ወይም የኪነጥበባት ክዋኔ ሆኖ በአብዛኛው ሰዎችን ለማዝናናትና ለማገናኘት ባለመ መልኩ የሚዘጋጅ (ዓመታዊ) ክብረበዓል ነው። መድረኩ ቢዝነስም ይቀላጠፍበታል። ታዲያ የሰላም ፌስቲቫል ምን ማለት ነው? አሁን ያለብን ችግር በአንድ ቀን ወይም ሰሞን የፌስቲቫል ግርግር የሚፈታ ነው?
የሀገራችን መሠረታዊ ችግር ምንጩ የብሔር ብሔረሰቦች ቅራቅንቦ ፖለቲካና አያያዙ ነው። የእነ አብርሃም ፌስቲቫል ደግሞ በመንግሥት ፊት ሞገስ ለማግኘት ያንን ዝባዝንኬ መዝለል አይችልም። ስለዚህ ስራቸው ቅራቅንቦውን የብሔር ብሔረሰቦች ነገር በኪነጥበብ መንገድ ሊያስታምሙ መጣር ይሆናል ማለት ነው። የአንድ ወገን ድምፅ ላለመባል። ያ ማለት ደግሞ ሁሉን አካታች ጭፈራና ሙዚቃ ይቀርባል። ያው በየመድረኩ እንደተለመደው “አንድ ነን፣ ፍቅር ያሸንፋል፣ ሰላም ለሁላችን” የሚሉ መፈክሮች በዲስኩር ታጅበው ይቀርባሉ። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ዝግጅቱ ኢሕአዴግ በየአመቱ ሰዎችን ለጭፈራ ከሚያሰማራበት የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከሚባለው “የፖለቲካ ፌስቲቫል” በምን ይለያል?
ላሉብን ሀገራዊ ችግሮች መፍትሔ እየተባሉ የሚቀርቡ ነገሮች በደንብ የታሰበባቸውና ዘላቂ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ መሆን አለባቸው። ለአጭር ጊዜ ሆይሆይታ፣ ለአጭር ጊዜ የሚዲያ ሽፋን፣ ምናልባትም እግረ-መንገድ የሚገኙ የስፖንሰርሺፕ ፈሰሶችን እንደ ግብ ቆጥሮ፤ ውጤት የለሽ ድርጊቶችን በሀገርና ሕዝብ ስም፣ መድረክና እድሉ ስለተገኘ ብቻ በተቸገረ ሀገርና ሕዝብ ላይ መተግበር ይቅር የማይባል አጉል ማላገጥ እንደሚሆን ማሰብ ተገቢ ነው።
በተመሳሳይ መንገድ በተተገበሩ ውጤት የለሽ ዝባዝንኬዎች የተነሳ መፍትሔ በሚባሉ ነገሮች ሁሉ ሕዝብም ተስፋ እየቆረጠ የመጣ ይመስላል። አብርሃም ጎበዝ አርቲስት መሆኑ የታወቀ ነው። ስለዚህ ይሄ “የሰላም ፌስቲቫል” ያለው ነገር ከአንድ ቀን የዜና ግብአትነትና ከተራ የግል ዝና ማማሟቂያነት የዘለለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እርግጠኛ መሆን አለበት።
አለበለዚያ ሌላ ዝና ወይም ጥቅም እጨምራለሁ ሲሉ፣ ያለና የነበረን ስምና ክብር እስከመጨረሻው ማጣትም ይመጣል። ሕዝብም ሆነ ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ የፖለቲከኞች አልበቃ ብሎ የግለሰቦች ቤተሙከራ እና የደፋሮች መነገጃ የመሆኗ ነገር ማብቃት አለበት። ስለዚህ አብርሃም ወልዴ አሰብኩት ስላለው ነገር በሚገባ እርግጠኛ መሆን አለበት። አለበለዚያ በሀገር እና ሕዝብ ስም ሳያፍሩ የሚያቆስሉንን ሰዎች እኛም ሳናፍር ራሳችንን መከላከል እንደምንችል ማስታወስ ያስፈልጋል። ይታሰብበት።
Filed in: Amharic