>

የ“በለጠው” በለጠ ሞላ!!! (ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ)

የ“በለጠው” በለጠ ሞላ!!!
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
ሰሞኑን፣ የአንዳፍታ ዶትኮም አዘጋጅ ሥዩም ተሾመ፣ በአዲስ የአበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል መምህር ከኾነው በለጠ ሞላ ጋራ፣ ከአደረገው ቃለ መጠይቅ ውስጥ ተነሥቼ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ብቻ አስተያየቴን ለመሰንዘር እፈልጋለሁ፡፡
ጉዳዩ፣ የበለጠ ሞላን የምሁራዊ ልቅና ዕርከን ይመለከታል፡፡ በውይይቱ ላይ፣ የፕሮግራሙ አዘጋጅ፣ በለጠን፣ በውጤት የሚበልጡህ ኹለት ተማሪዎች እያሉ አንተ እንዴት ለትምህርት ክፍሉ መምህርነት ልትመረጥ በቃህ? በማለት ጠይቆታል፡፡ ጥያቄው በይዘቱ፣ የትምህርት ክፍሉ አመራረጥ አድሏዊነት እንደነበረው የመጠቆም አንድምታ እንዳለው ግልጽ ነው፡፡
እኔ፣ በለጠ ለመምህርነት ሲመረጥ በቦታው አልነበርሁም፡፡ ኾኖም፣ በለጠን በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር እንደ አስተማሪ፣ በተጨማሪም እንደ ትምህርት ክፍሉ የሥራ ባልደረባ በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው፣ በለጠን ለመምህርነት ማስቀረቱ ትክክለኛ ምርጫ እና በተለይም የትምህርት ክፍሉ በእጅጉ ተጠቃሚ እንደ ኾነ፣ የግል እማኝነቴን ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡
በለጠ እንደ ተማሪ፤
ትምህርት ክፍሉ ተማሪዎቹን መርጦ በሚቀጥርበት ጊዜ፣ ‘ሰቃይ’ በሚል ዘይቤ፣ የጠቅላላ ድምር ውጤት ላይ ብቻ ተመርኩዞ የአስተማሪነትን ብቃት ከመመዘን ጋራ ከግምት ሊወስዳቸው የሚገቡ መሳፈርት አሉ፡፡ እኒህም፥ የተወዳዳሪው ጠባይ፣ ሞራላዊ ይዞታና ግብረ ገባዊነት እንዲሁም ተግባቢነት ተያይዞ መታየት ይኖርበታል፤ እላለሁ፡፡
በመሠረቱ፣ የፍልስፍና ትምህርት ክፍሉ፣ መምህራንን ከተማሪዎች መርጦ ለመቅጠር በሚያወዳድርበት ጊዜ የሚከተለው አሠራር፤ ድምር ውጤትን በአጠቃላይ እና የፍልስፍና ኮርሶች ውጤቶችን በተለይ በማወዳደሪያነት ይጠቀማል፤ በተጨማሪም፣ ከተወዳዳሪዎቹ ጋራ በኹለንተናዊ እና ሞያዊ ጉዳዮች ቃለ ምልልስ አድርጎ ራሱን የቻለ መመዘኛ ይሰጠዋል፡፡
የበለጠ ሞላ ለመምህርነት መመረጥ፣ እነኚህን መመዘኛዎች ኹሉ ያለፈ እንደ ኾነ ከትምህርት ክፍሉ አመራር ጠይቄ አረጋግጫለሁ፡፡ በፍልስፍና ኮርሶች ውጤት እና በተካሔደው ቃለ ምልልስ ምዘና፣ ከተወዳዳሪዎቹ መካከል ከበለጠ ልቆ የተገኘ አልነበረም፡፡ ይህም የምዘናው አፈጻጸም ከአድልዎ የጸዳ እንደነበር ያሳያል፡፡
እኔ እና በለጠ ሞላ የተዋወቅነው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ሓላፊ ኾኜ ሳለሁ፣ ከአውሮፓ የማስተርስ ዲግሪውን ይዞ ከተመለሰ በኋላ ነው፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ሥር አራት ተማሪዎች ተልከው፣ “ፕራክቲካል ኤትክስ”(Practical Ethics) በሚል ርእስ የማስተርስ ዲግሪ ይዘው መጥተው ነበር፡፡ ውጭ ተምረው መምጣታቸው በራሱ በጎ ቢኾንም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍላችን፣ በዚያው መስክ የተሻለ የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ዝግጅት ነበረው፡፡
በመኾኑም፣ በወቅቱ እንደ ትምህርት ክፍል ሓላፊነቴ፣ ልጆቹ በአውሮፓው ዲግሪ ሳይወሰኑ፣ ዳግም በመርሐ ግብራችን ተመዝግበው የማስትሬት ዲግሪአቸውን ማግኘት እንዳለባቸው ነገርኋቸው፡፡ ጥቂቶቹ ቅር ቢላቸውም፣ ኹሉም እንደገና ተመዝግበው ትምህርቱን ቀጥለው ሲያጠናቅቁ የነበራቸው ስሜት ከቀድሞው በተለየ በጣም ደስተኛ ነበሩ፡፡
ከእነርሱ አንዱ የነበረው በለጠ፣ በራሱ ፍላጎትና ሙሉ ፈቃደኝነት፣ ትምህርቱን ተከታትሎ ከማጠናቀቁም በላይ፣ ለፕሮግራሙ የተመደቡትን ስምንቱንም ኮርሶች በሙሉ “ኤ” ግሬድ በማግኘት፣ በመመረቂያ ሥራውም “ኤክሰለንት” በማስመዝገብ፣ በሙሉ አራት ነጥብ በእጅግ ከፍተኛ ማዕርግ ተመርቋል፡፡ ምናልባት ይህን ልቅናውን፣ ራሱን በለጠን ሳላስፈቅደው በመግለጼ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
በለጠ እንደ አስተማሪ፤
በሥራ ባልደረባነት ከበለጠ ሞላ ጋራ ከስድስት ያላነሱ ዓመታት የቅርብ ዕውቅና አለን፡፡ እንደ መምህር፥ ታታሪ፣ ሞያው በሚጠይቀው ምሁራዊ ክሂል እና ዲስፕሊን የታነፀ ነው፡፡
በለጠ፣ በእምነቱም ላመነበት ጉዳይ ያለፍርሃት የሚቆምና ይህን ብናገር መጥፎ ይደርስብኛል በሚል ስሌት ከአቋሙ የሚያፈገፍግ እንዳልኾነ በሚገባ አውቃለሁ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚኾነኝ፣ እኔ በቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አድማሱና አበሮቹ ከተባረርሁ በኋላ እርሱ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ሓላፊ ኾነ፡፡ ጠርቶኝም፣ “የፖለቲካ ፍልስፍና የሚያስተምር ስለሌለና ቀደም ሲልም ኮርሱን ለማስተማር ተመድቤ ስለነበር፣ አስተምርልኝ፤” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ኮርሱን አስተማርሁ፡፡
ኾኖም ግን፣ በወቅቱ የኮሌጁ ዲን የነበረው ፕሮፌሰር ወልደ አምላክ በዕውቀት፣ ክፍያዬ እንዳይፈጸምልኝ በማስደረጉ ከትምህርት ክፍሉ ሓላፊ በለጠ ሞላ ጋራ በአካዳሚክ ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ፍጥጫ ተፈጠረ፡፡ በለጠ፣ ለሠራ ክፍያው ይገባዋል፤ በማለት ይህን ፍትሐዊ አለኝታነቱን ሲያሳይ፣ ዲኑ ከፕሬዝዳንት አድማሱ ጋራ ከነበረው ቅርበት አንጻር ራሱን ለአደጋ እያጋለጠ ነበር፡፡
በሌላ በኩል፣ ፕሮፌሰር ወልደ አምላክ በግብጽ ሀገር ለሚሠራው ፕሮጀክት ሰዎችን ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር፡፡ ይህን ማስታወቂያ ተከትሎ በለጠ ውድድሩን በአንደኛነት ቢያጠናቅቅም፣ በአካዳሚክ ኮሚሽን ላይ እኔን ወክሎ ከፕሮፌሰሩ ጋራ እሰጥ አገባ በመግባቱ ዕድሉን እንዳይጠቀምበት ኾኗል፡፡ እኔ እስከምረዳው ድረስ፣ ለእውነት እና ለፍትሕ በመቆም ዋጋ መክፈል ማለት ይኸው ነው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ብዙዎች ዘመኑን መስለው፣ በስጋት ከእኔ ጋራ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ላለመታየት በሚሸሹበት ወቅት፣ በለጠ በሓላፊነቱ የትምህርት ክፍሉን ወጣት መምህራንና ስታፎች አስተባብሮ በይፋ የስንብት የራት ግብዣ በአንድ የታወቀ ሆቴል አዘጋጅቶ፣ ያበረከተልኝን፣ የአገራችን የቆዳ ምርት ውጤት የኾነ ምርጥ ቦርሳ እና ቡልኮ ስጦታ ልዘነጋው አልችልም፡፡
እንደ መውጫ፡- በመግቢያዬ ለመግለጽ እንደሞከርሁት፣ ትምህርት ክፍላችን ለአስተማሪነት መርጦ ካስቀራቸው ወጣት መምህራን መካከል፣ በለጠ ሞላን በቀዳሚነት አስቀምጠዋለሁ፡፡
Filed in: Amharic