>

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በዶ/ር አብይ አስተዳደር መካከል ውዝግብ ተፈጠረ!!! (ኢትዮ 360 )

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በዶ/ር አብይ አስተዳደር መካከል ውዝግብ ተፈጠረ!!!
ኢትዮ 360 — ነሐሴ 3/2011) 
 
በኢትዮጵያ በቀጣዩ አመት የሚካሄደው ምርጫ በምርጫ ቦርድና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር መካከል ውዝግብ ማስነሳቱን ከታማኝ ምንጮች ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮ 360 ምንጮች እንደገለጹት ውዝግቡ የተነሳው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አስተዳደር ምርጫው ለሁለት አመት ይራዘም በሚል ያቀረበው ሃሳብ በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲነገርልት በመፈለጉ ነው።
ምርጫ ቦርድ በኔ በኩል በቀረኝ ጊዜ ዝግጅቴን አጠናቅቄ ምርጫውን ማካሄድ እችላለሁ፤ ምርጫ ለማካሄድ አልችልም ያለው መንግስት ስለሆነ መንግስት እራሱ ይህን ሃሳቡን ለህዝብ ይፋ ያድርግ የሚል ምላሽ በመስጠቱ ውዝግቡ መካረሩን ነው ምንጮቹ የገለጹት።
የምርጫ ቦርድ አቋም አላንቀሳቅስ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተሰሚነት አላቸው ብለው የሚያስቧቸውን አምስት ፓርቲዎችን ቢሯቸው ድረስ ጠርተው ማነጋገራቸውም ታውቋል።
ለዚሁ ጉዳይ የተፈለጉት የኢዜማ የፖለቲካ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ የሽዋስ አሰፋም ለቅስቀሳ ከመጡበት አሜሪካ በአስቸኳይ እንዲመለሱ መደረጋቸውንም ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማስፈፀም ስለማልችል ይራዘም የሚል መግለጫ ሰጥቶ ሃላፊነት እንዲወስድ ያደረጉት ሙከራ በምርጫ ቦርድ እንቢተኛነት ሊሳካላቸው ባለመቻሉ፤ ከአምስቱ ፓርቲዎች ጋር ተወያይተው ፓርቲዎቹ ምርጫው ለሁለት አመት እንዲራዘም እንዲጠይቁና ይህንንም ለህዝብ ይፋ እንዲያደርጉ ከስምምነት መድረሳቸው ታውቋል።
ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት በራሱ የኢዜማ አመራሮችን በሁለት ተከፍለው እንዲወዛገቡ ማድረጉ ነው የተሰማው።
አንዱ አካል ሁለት አመት የሚራዘም ከሆነ ህገ መንግስቱ ሊሻሻል ይገባል ፣ያ ካልሆነ ግን ለምንድን ነው መንግስት ሊወስድ ያልፈለገውን ሃላፊነት እኛ እንድንወስድ የሚደረገው በሚለው አቋሙ መጽናቱን ምንጮቹ ይናገራሉ።
ሌሎቹ አመራሮች በአንፃሩ ችግር የለውም ሃገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ጥሩ ስላልሆነ የመንግስትን አቋም ብንደግፍ ይሻላል በሚል አቋም ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ይህ አቋም በፓርቲው ውስጥ ትልቅ መከፋፈልንና ውጥረትን ማንገሱ ተሰምቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈራረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ በምርጫ ቦርድና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል ሌላ የውዝግብ መንስኤ መሆኑን ነው የኢትዮ 360 የመረጃ ምንጮች የሚናገሩት።
 የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈራረምነው የቃል ኪዳን ሰነድ እየተከበረ አይደለም፣አባላቶቼ እየታሰሩ ነው፣ እስሩ ደግሞ ፖለቲካዊ ነው ሲል ያቀረበው ቅሬታ ዋና የውዝግቡ አጀንዳ መሆኑም ታውቋል።
ምርጫ ቦርድ የቃል ኪዳን ሰነዱ ስምምነት መከበር አለበት፣ ስምምነቱ የወጣው ለሚዲያ ፍጆታ ሳይሆን ህግን ልናስከብርበት ነው፣ አብን ያነሳው ጥያቄም ቢሆን በስምምነቱ መሰረት ሊስተናገድ ይገባል የሚል አቋሙን እንደያዘ ቀጥሏል።
ስምምነቱ ተደባብሶ እንዲያልፍ የሚፈልገው የዶክተር አብይ አስተዳደር በበኩሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ስምምነት የሚለውን አደባብሶ ለማለፍና ምርጫ ቦርድም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ምላሽ እንዳይሰጥ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጫና እየፈጠሩ ነው ይላሉ የመረጃ ምንጮቹ ።
በምርጫ ቦርድና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መካከል የተነሱት ውዝግቦች ነገሮችን ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ ሊመራቸው ይችላል የሚል ስጋትንም አጭሯል።
በዚሁ ውጥረት ምክንያት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተነሳው ውዝግብ የከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ውይይት ይደረግበት በሚል ቀነ ቀጠሮ መያዙንም ነው ምንጮቹ ለኢትዮ 360 ጨምረው የገለጹት።
Filed in: Amharic