>

ይድረስ ለአቶ በቀለ ገርባ!!! (ብሩክ አበጋዝ)

ይድረስ ለአቶ በቀለ ገርባ!!!
ብሩክ አበጋዝ
ለጤናዎት እንደምን አሉ? ዛሬም ትህነግን አምነው የትህነግ ፕሮፖጋንዳ መጫወቻና መሳሪያ በመሆንዎ እጅጉን አሳዘኑኝ። የትግራይ ሕዝብ ወደ መሀል አገር በወሎ አድርጎ መሄድ ካቆመ 1 ዓመት አለፈው በማለት ሌባ ጣትዎን ደጋግመው በማሳየት ሲናገሩ ሳይ ልቤ አዘነልዎት፤ አዘንኩብዎት አላልኩም አዘነለወት ነው ያልኩት። ለመሆኑ የትግራይ ሰወች የወሎን ምድር ሳይረግጡ ወደ መሀል አገር እንዴት መሄድ ይቻላቸዋልን ነው ወይስ ወሎ ድንበር ሲደርስ ተሽከርካሪው በአየር ላይ ተንሳፎ ትግራይ ድንበር ያርፋል?
ለማንኛውም የትህነግ ሰወች እንደሸወዱዎት እኔ አልሸውደዎትም። ምናልባት እርስዎ የተሸወዱት አማራን የሚያጥላላ ነገር እስከሆነ ድረስ ትርፍ አገኝበታለሁ ብለው ወደውና ፈቅደው ይሆናል። እስከማውቀው ድረስ ከመሀል አገር ወደ ትግራይ ለመሄድ 3 አማራጭ አለ። አንደኛው በአየር ላይ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በየብስ ነው። ሁለቱም ከመሀል አገር ወደ ትግራይ የሚያስገቡ መንገዶች ወሎን የሚረግጡ መሆናቸውን ሊያውቁት ይገባል።
አንደኛው መንገድ በደብረ ብርሃን፣ ከሚሴ፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ቆቦ አላማጣ ብሎ መሆኒን አልፎ ትግራይ የሚገባው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከመሀል አገር በአፋር በኩል አድርጎ አፋርን ካቋረጠ በኋላ ወደ ሰሜን ወሎዋ ሀራ ይገባና፣ ዶሮ ግብር፣ ጎብየ፣ ሮቢት፣ ቆቦ፣ አላማጣ፣ መሆኒ ብሎ ትግራይ ይገባል። እንግዲህ ከሀራ ጀምሮ ትግራይ እስኪደርሰ ድረስ ያለው አካባቢ የወሎ ግዛት እንደሆነ ልብ ይበሉ። በእርግጥ ረዝም ከመሆኑ የተነሳ አይጓዙበትም እንጂ ለክፉ ቀን ብለው የሰሩት በገዋኔ በኩል የሚያሰኬድ መንገድም አለ።
ወደ ትግራይ ለመሄድ ቅርቡ መንገድ በደሴ በኩል ያለው ቢሆንም ከሸዋ ሮቢት እስከ ኮምቦልቻ ያለው መንገድ እጅግ አስጠሊታ የሆነ ተደጋጋሚ የፍጥነት መቀነሻ ብሬከር ስላለው አሰልቺና ጊዜ ስለሚገድል ሰላም ባስን ጨምሮ ብዙ መኪኖች ከአምና በፊት ጀምሮ ቢርቅም በአፋር በኩል አድርገው እንደገና ወሎን ረግጠው ትግራይ ይገባሉ። ሌላው ደግሞ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከደሴ እንዲሁም ከመሀል አገርም በተለመደው መንገድ መኪና ሳይቆም እየሄደ ቆይቷል።
ባለፈው ጥር ወር እኔ ራሴ መቀለ በሚሄደው አውቶብስ ትኬት ቆርጨ ወልዲያ ድረስ ሄጃለሁ፤ የዚያኑ ሰሞን ከሀራ በኩል በዶሮግብር አድርጎ ሰላም ባስ ሲሄድ በዓይኔ አይቻለሁ፤ ነጋዴ ዘመዶቻችን በየጊዜው እየተመላለሱ ነው። ታዲያ እርስዎ የሚናገሩት ነገር ከየት የመጣ ነው? እርስዎ የተናገሩት የመንገድ መዘጋት ያለው በነገሩዎት ሰወች ጭንቅላት እንጂ መሬት ላይ ያለ አይደለም።
አቶ በቀለ ገርባ ትህነግ ሁለት ጊዜ ነው የበደለዎት ድሮ ባለጉልበት በነበሩ ጊዜ መብትዎትን ገፎ ወኅኒ ቤት ያሻቸውን አድርጎዎታል፤ አሁን ደግሞ በብልጠት አታለው የእነሱን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በእርስዎ አፍ በማስነገር ውሸታምና ቂል ተደርገው እንዲቆጠሩ አደረጉዎት። እርሰዎ 27 ዓመታት ሲዋሽና ሲያታልልዎት የነበረውን አካል ባህሪ መገንዘብ አቅቶዎት ዳግም ሲታለሉና የእነሱ መሳሪያ ሲሆኑ ኢትዮጵያን የማያውቃት ኤርትራዊ ግን የእነሱን በወሎ አትሂድ ይገድሉሀል የሚል የውሸት ማስፈራሪያ ባለመስማት እንዴት ውድቅ አድርጎ በወሎ በኩል ተጉዞ እነሱንም እንደታዘባቸው ከሚከተለው ጥሁፍ እንዲያነቡና ሳያረጋግጡ የተናገሩት ነገር ስህተት እንደሆነ አውቀው ይቅርታ ቢሉ ትልቅ ሰው ያስብለዎታል።
የትህነግእኩይ ፕሮፖጋንዳ ያከሸፈው የወሎ ሕዝብ አኩርቶኛል
ነገሩ እንዲህ ነው፦ ለደህንነቱ ሲባል ስሙን የማልገልፀው ኤርትራዊ የኤርትራ ታርጋ ያላትን መኪና ይዞ በመጥፋት ድንበር አቋርጦ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል። በተለያዪ የትግራይ ከተሞችም ቆይታ አድርጓል። ግለሰቡ በፖሊስ መኮነንነት ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ እና በኤርትራ መንግስት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ የነበረው በመሆኑ ነበር የመንግስት ንብረት የሆነች መኪናን ይዞ ከኤርትራ የተሰወረው። ይሁንና ይህ ግለሰብ ትግራይ ውስጥ በቆይታው ወደ አዲስ አበባ በቀጣይ ስለሚያደርገው ጉዞ የፀጥታና ደህንነት መረጃወችን ከሰበሰበ በኋላ ጉዞውን ወደ መሀል አገር ለማድረግ ወሰነ።
.
ስለ ጉዞው ትግራይ ውስጥ መረጃ የሰጡት ሰወች በሙሉ በአማራ ክልል አቋርጠህ እንዳትሄድ፣ መሄድ ያለብህ በአፋር በኩል በሚወስደው መንገድ ነው ይሉታል። ለዚህ ምክንያታቸውም “አንተ አማርኛ ስለማትችል እና ትግርኛ ብቻ ስለምትናገር ትግሬ ነው ብለው ይገድሉሀል፤ ነፍስህን ይዘህ አዲስ አበባ ለመድረስ ከፈለግ በደሴ በኩል አቋርጠህ እንዳትሄድ። አሁን ሁሉም የትግራይ ሰው የሚጓዘው በአፋር በኩል ነው። በደሴ በኩል የሚሄዱት ትግሬወች ይደበደባሉ፣ ንብረታቸው ይዘረፋል፣ ይገደላሉ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በደሴ አድርጎ ወደ አዲስ አበባ የሚሄድ ትግራውይ የለም……” ወዘተ ብለው ምክር ይለግሱታል።
.
ይኼ ኤርትራዊይም መኪናውን አስነስቶ በመጓዝ የትግራይን መሬት አቋርጦ አላማጣ በማደር እንደገና በጧት ተነስቶ በመጓዝ ዶሮ ግብር ይደርሳል። ዶሮ ግብር እንደ ደረሰ ወደ አፋር የሚወስደውን እንዲሁም ደግሞ ወደ ወልዲያ ደሴ የሚወስደውን መንገድ ሲያይ የአካባቢውን ሰወች ስለ መንገዶቹን መረጃ ይጠይቅና ይነግሩታል። አማርኛ ስለማይችል ብዙ መነጋገር አይችልም፤ አቅጣጫውን በምልክትና በጥቂት ቃላት ከመረዳት ውጭ ከአካባቢው ሰወች ጋር ስለ ጸጥታውም ሆነ ስለ ጉዞው ደህንነት መነጋገር አልቻለም።
.
ብቻ የትግራይ ሰወች ከመከሩት በተቃራኒ የአፋር መገንጠያውን መንገድ ትቶ የወልዲያውን መስመር ይዞ ወደ ወልዲያ ይጓዛል። የከፋ ችግርም የሚገጥመኝ ከሆነም ቅርብ ስለሆነ ከወልዲያ በመመለስ በአፋር መንገድ መቀጠል እችላለሁ፤ እንደተባለው አስጊ ነገር ከመጣም ይምጣ በማለት ነበር ወደ ወልዲያ አቅጣጫ የተጓዘው። ወልዲያ እንደ ደረሰም ጧት ስለነበር መኪናውን አቁሞ ቁርስ ለመብላት አንድ ሆቴል ገባ። ቁርሱን በልቶ እስኪጨርስ ትግራይ ላይ በተነገረው ልክ ያጋጠመው አንዳች ትንኮሳም ሆነ ክፉ ፊት አላስተዋለም። እንዲያውም መኪናውን የተመለከቱ ሰወች በሙሉ በፍቅር ስሜት በፈገግታ ነበር ሲመለከቱት የነበረው።
.
ቁርሱን በልቶ ጨርሶ ሂሳብ ለመክፈል ገንዘብ ሲያወጣ አስተናጋጅ የቁርሱም ሆነ የሌሎቹ ነገሮች ሂሳብ እንደተከፈለለት ይነግረዋል። የሚያውቀኝ ሰው ሳይኖር ማነው የከፈለልኝ ብሎ ሲጠይቅ “አንተ እንግዳችን ነህ እኛ ነን የከፈልነው እንኳን ወደዚችኛዋ አገርህ በሰላም መጣህ” የሚል ምላሽ ያገኛል። ትግራይ ላይ ከተነገረው አንጻር እጅግ የማይጠበቅ ምላሽ ከወልዲያ ነዋሪወች በማግኘቱ ሁኔታወች ሁሉ ድብልቅልቅ አሉበት። የደስታው ስሜት እንዳለ ሆኖ ትግራይ ውስጥ የሰማው ነገር በሙሉ መሰረተ ቢስ ወሬ መሆኑ ለምን እንዲል አስገድዶታል። የሆኖ ሆኖ ሁኔታውን ለማጥናት ወልዲያ ድረስ የመጣውና እንደተባለው አስጊ ነገር ካለም ተመልሶ በአፋር በኩል ለማለፍ ያቀደው ተጓዥ ሀሳቡን አንድ አድርጎ በደሴ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ጉዞውን ቀጠለ።
.
ደሴ እስኪደርስ በየመንገዱ ቡና ለመጠጣት በሚወርድባቸው ከተሞች ሰው ሁሉ በፈገግታ ነበር የሚቀበለው፤ የሚጠጣውን ቡና ሁሉ የሚከፍልለት የአገሬው ሰው ነበር። ሂሳብ ለመክፈል ሲጠይቅም “ተከፍሏል እንግዳችን ነህ፤ እንኳን ደህና መጣህ” የሚል ምላሽ ነበር የሚያገኘው። በዚህ መልኩ ተጉዞ ለምሳ ደሴ ይደርስና አንድ ምግብ ቤት በር ላይ መኪናውን አቁሞ ምሳ ለመብላት ይወርዳል። ደሴ ላይም በመንገድ ላይ እንደሆነው ሰው ሁሉ የተመለከተው በፍቅር ስሜት ነበር። ምሳ በልቶ ሲጨርስ አሁንም “እንኳን ሰላም ገባህ እንግዳ ነህ ሂሳብ ተከፍሏል” የሚል ምላሽ ያገኛል።
ከዚያም ወደ መኪናው ገብቶ ሞተር ሲያስነሳ መኪናዋ ስትንተፋተፍ ያስተዋለ እና ሆቴሉ ውስጥ ሲመገብ የነበረ መካኒክ “መኪናዋ በዚህ ሁኔታ አዲስ አበባ አታደርስህም ውረድና ማስተካከያ ጥገና አድርጌልህ ትሄዳለህ” በማለት መኪናዋን ጥገና አድርጎ ሞክሮ አስተካክሎ ሰጠው። አሁንም ለጥገናው ሂሳብ ሊከፍል ሲል መካኒኩ በጭራሽ አልቀበልህም በማለት መልካም መንገድ ይሁንልህ ብሎ ተመኝቶ ይሸኘዋል። የተነገረው እና ያጋጠመው ነገር እየቅል ሆኖበት እየተገረመ ጉዞውን ይቀጥልና ከሚሴ ይደርሳል።
.
ከሚሴ ላይ ደግሞ የተፈጠረ ችግር ነበርና የታጠቁ የአካባቢው ሰወች በርካታ መኪና አስቁመው ሁሉንም እየፈተሹ ስለነበር በርካታ መኪና ሰልፍ ይዞ ተሰልፎ  እየተጉላላ ነበር። እሱም አሁን የተባለውና የፈራሁት ነገር ደረሰ ብሎ አሰበ። ወዲያው ይዞት የነበረውን የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ አውጥቶ ከመኪናው ላይ ሲያውለበልብ ታጣቂወቹ ወደ እሱ በመቅረብ መታወቂያውን ጠይቀው ካረጋገጡ በኋላ በፈገግታና በፍቅር ስሜት ከሁሉም አስቀድመው ይሸኙታል። አዲስ አበባ እስኪደርስ ድረስም ተመሳሳይ መልካም ነገር ነበር ያጋጠመው።
የትግራይ ሰወች የነገሩት እና የነዙት የጥላቻ ወሬ ውሸት መሆኑ ስላስገረመው ጉዳዩን አዲስ አበባ ላገኘው ወንድሙ በሚችለው ቋንቋ በደስታ ሲቃ በግርምት ይነግረዋል። የእሱ ወንድም ደግሞ ለእኔ ወዳጅ ሁኔታውን በዝርዝር ያስረዳዋል። የእኔ ወዳጅ ደግሞ ይህ ነገር አስተማሪ በመሆኑ ፌስቡክ ላይ እንድጽፈው የተጓዡ ወንድም ጋር በስልክ አገናኝቶኝ ሁኔታውን በዝርዝር ነገረኝና አማርኛ የማይችለውን ተጓዥ ወንድሙን በስልክ እዚያው ያገናኘኛል። ተጓዡም አማርኛ ስለማይችል አማርኛና ትግርኛ እየቀላቀለ የደስታውን እና የግርምቱን ሁኔታ ለደቂቃ አወራኝ።
 .
ሁኔታው ትህነግ/ህወሓት ባሰማራቸው ወኪሎቹ የሚያሰራጨውን የጥላቻ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚገልጽና በተቃራኒው የወሎን ሕዝብ የተለመደ እንግዳ ተቀባይነት የሚያሳይ በመሆኑ አስተማሪ ነው በማለት ነው እኔም የጻፍኩት። ይህ ዓይነቱ የትህነግ/ህወሓት ወኪሎች የውሸት መሰሪ ፕሮፖጋንዳም በዋናው መንገድ ያሉ ከተሞችን ኢኮኖሚ እጅጉን የሚጎዳ መሆኑን መገንዘብም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ተጓዥ ግብዣ እና መልካም መስተንግዶ ላደረጉ ስማቸውን ለማላውቃቸው ሰወች ምስጋናየ ይድረስልኝ፤ መልካም ምግባራቸው የሁላችንም ኩራት ሆኗል ክፉወችንም አጋልጧል።
Filed in: Amharic