>

ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ!!! (ከሸንቁጥ አየለ)

ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ!!!
ከሸንቁጥ አየለ
ከሁሉም  የሚበልጠዉን ኢትዮጵያዊ  ማንነት በምልዓት መላበሱ ቢኖር እንዲህ  የተምታታ የማንነት ጥያቄ ዉስጥ ባልተገባ ነበር!
1. “የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙም እርስ በርሱ አልተቀላቀለም::አልፎ አልፎ መቀላቀል ያለዉ በከተሞች ነዉ:: በመሆኑም ከአማራ እና ከሌላ ብሄር በከተማ የተወለዱ እና አማርኛ ቋንቋ የሚችሉ ሰዎች ሁሉ አማራ ይሁኑ::አማራ ብሄረተኝነቱን ማምጣት የሚችለዉ ኢትዮጵያ ከሚባለዉ ሀገር ማዕቀፍ እራሱን ሲያወጣ ነዉ::ኢትዮጵያ በወረራ እና በቅኝ ግዛት የተፈጠረ ሀገር ነዉ::አማራዉ ሌሎች ነገዶችን ወሮ ኢትዮጵያ የሚባል ሀገር በመፍጠሩ ስህተት ሰርቷል::የአማራ ብሄርተኝነትን ያኮላሸዉ የኢትዮጵያ መፈጠር ነዉ::ኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ያለዉ ሀገር ስለሆነ ቢፈርስ ሁሉም ነገድ የየራሱን ክልል ይዞ መሄድ ይችላል::
አማራም የራሱን ክልል ይዞ ቢሄድ የአማራ ብሄረተኝነት በደንብ ያብባል::እኔም አማራ ነኝ እና የአማራዉ ህልዉና ስለሚያሳስበኝ አማራ ከዬት ወዴት የሚለዉን መጽሃፍ ለመጻፍ ተነሳሁ::” አቶ አንዳርጋቸዉ አማራ ከዬት ወዴት በሚለዉ መጽሃፉ የተረተዉ ነዉ::አቶ አንዳርጋቸዉ ይሄን መጽሃፉን የጻፈዉ የወያኔ/ኢህአዴግ የአዲስ ከተማ ጽ/ቤት አፈ ጉባኤ በነበረበት ጊዜ ከስልጣኑ ተባሮ ባሉት ጥቂት ወራት ዉስጥ ነዉ::የዚህ ጽሁፍ ዋና ፍሬ ሀሳብም የወያኔ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ ከሆነዉ ከአንዳርጋቸዉ አ ዕምሮ የፈለቀ የተኮረጀ ሀሳብ መሆኑን መጽሃፉን እንደዋጣ በግል ጋዜጦች ላይ መጽሃፉን ተችቼ ሀሳቤን ሰንዝሬ ነበር:: አንዳንድ ሰዎች ግን አማራ የሚባለዉ ቃል ስለተጠራላቸዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ የአማራ ጠበቃ ነዉ እያሉ እንብር እንብር ሲሉ እንደነበረም አስታዉሳለሁ::እረ አሁን ድረስ የሚሉም ነበሩ::
2. የአንዳርጋቸዉ ጽጌ ሁለተኛ መጽሃፉ “ነጻነት እማያዉቅ ነጻ አዉጭ የሚል ነዉ::በዚህኛዉ መጽሃፉ ከአማራ እና ኦሮሞ ነገድ እንደሚወለድ አብራርቶ ጽፏል:: ይሄ መጽሃፉ ከወያኔ ተጽኖ በተወሰነ ደረጃ የተላቀቀበት ወቅት እና ወደ ቅንጅት አስተሳሰብ ያዘነበለበት ወቅት ላይ ስለነበረ መላክም ሀሳቦችን ይዟል ማለት ይቻላል::አንዳንድ ትንታኔዎቹም ጠንካራ የሚባሉ ናቸዉ::የሚያሳዝነዉ ግን የዚህ መጽሃፍ መቋጫም የሚደመደመዉ የተዋህዶን ሀይማኖት በመሳደብ እና ተዋህዶን ደናቁርት አቢዮተኞች ላጠፉት ጥፋት ሁሉ ተጠያቂ በማድረግ ነዉ::ይሄ የድንዛዜ አካሄድ በአብዛኞቹ የዚያ ትዉልድ ፖለቲከኞች እራሳቸዉን እንዳዋቂ ለማሳያነት የሚተቀሙበት ስልት ነው::
የእግዚአብሄርን ቤት በመሳደብ እራስን አዋቂ ማድረግ ትልቁ ስልታቸዉ ነዉ::እናም አንዳርጋቸዉም ነጻነት የማያዉቅ ነጻዉጭ በሚለዉ መጽሃፉም ተዋህዶን አርክሶ እና ኮንኑ የትንታኔዉ መቋጫ አድርጓታል:: በእሱ ትንታኔ መሰረትም ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ እንዳያብብ ትልቅ እንቅፋት የሆነዉ የቤተክህነት ባህል እና ስነልቦና ነዉ::ከአቢዮታዉያኑ ኢ አማኞች ጋር ቤተክህነትን በምን ገመድ ጎትቶ እንዳገናኛት ግን ሳይገልጽልን አልፎታል::
አስቂኙ ነገር ታዲያ አንድ የተዋህዶ ሰባኪ ነኝ የሚል ወዳጄ የአንዳርጋቸዉን መጽሃፍ አነበብኩት ብሎ ማብራሪያ ሰጠኝ::ተዋህዶ ላይ ያለዉን እይታ እንዴት አገኘህዉ ብለዉ “መቼም ግሩም ገልጾታል” ብሎኝ ቁጭ::ይሄ ሰባኪ ነኝ ባይ መጽሃፉን እንዳላነበበዉ ወይም መጽሃፍ አንብቦ እንደማይረዳ ሲገባኝ ከትከት ብዬ ስቄቤት እንደነበረ ትዝ ይለኛል::ለምን ትስቃለህ ቢለኝ “መቼም እናንተ ዲያቢሎስ ቢሰድባችሁ አትቆጡም::የክርስቶስን ቤት የሚሳደብን ሁሉ ታደንቃላችሁ አይደል?” ብዬ ብለዉ የመለሰለኝ መልስ እስካሁን ያስቀኛል::”እንዴ ? አንዳርጋቸዉ ተዋህዶን ሰደበ እንዴ?” ብሎኝ ቁጭ::በቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰዉ እንዲህ ይመስለኛል::ነገር ከመመርመር ጩህት እደመቀበት እሚረግሙት ዳስ ዉስጥ ገብቶ ከበሮ የሚደልቅ::
3. አንዳርጋቸዉ አሁንም ሶስተኛ መጽሃፉን አሳትሟል:: ይሄ መጽሃፉ ደግሞ በተለዬ ሁኔታ ዉስጥ ሆኖ የጻፈዉ ይመስላል::በአንድ መልኩ እስር ቤት እያለ የጻፈዉ ታሪክ እና ከ እስር ቤት ከወጣም ብኋላ አሁን በኦነጋዉያን ተጽዕኖ ዉስጥ ወድቆ የጻፈዉ መጽሃፍ የቀደሙትን የራሱን ትርክቶች ደምስሷቸዋል:: ዋናዉ ማንነቴ ነዉ ሲል አማራ ከዬት ወዴት በሚለዉ መጽሃፉ ያተተዉንም ፍልስፍናዉን እና ማንነቱንም ፍቆ በመጣል አማራ የሚባል ህዝብ የለም::እኔም ኦሮሞ ነኝ ብሎ ቁጭ ብሏል::እኔ ኦሮሞ ነኝ ማለቱ አንዳች ክፋት የለዉም::አስገራሚዉ ነገር ከኔ በላይ አማራ የለም ሲል አማራ ከዬት ወዴት በሚለዉ መጽሃፉ የተረከዉን ማንነቱን በመፋቅ እንዴዉም አማራ የሚባል ህዝብ የለም ማለቱ ነዉ ነዉ::
ከላይ የተነሱ ሶስት የሰነልቦና ቀዉሶችን እንዉሰድ እና አላማቸዉ ምን እንደሆነ እንይ
1.አማራ ከዬት ወዴት የሚለዉ መጽሃፍ የተጻፈዉ እኔም አማራ ነኝ::አማራን ወክዬ ስልጣን እይዛለሁ የሚል ትልምን ተንተርሶ ነዉ::ይሄ ሀሳብ አይከፋም ነበር::ክፋቱ ግን አማራ ያልሆኑ የከተማ ሰዎችን ሁሉ አማርኛ ስለሚናገሩ ብቻ አማራ ይሁኑ::ኢትዮጵያም ትፍረስ::ኢትዮጵያ ስትፈርስ የአማራ ብሄረተኝነት ይቀጣጠላ የሚለዉ ሸዉራራ ሀገር አፍራሽ ህሳቤ ነበር::የዚህ ሸዉራራ ህሳቤ መነሻዉም ከአማራ በላይ አማራ ሆኖ ለመገኘት የታቀደ መሰረት የሌለዉ ስሁት ስነልቦናዊ ቀመር ነበር::
2. በሁለተኛዉ መጽሃፉ ደግሞ ኦሮሞነቱን እና አማራነቱን ለማሳዬት ከሁለቱ ነገዶች መወለዱን ለማታቀስ የተገደደበት ሁኔታ ነበር::ይሄዉም ቅንጅት ህብረ ብሄራዊነትን እያገነነዉ ስለመጣ ነበር::በዚህ ህብረ ብሄራዊነት ምህዳር ዉስጥ በሁለቱ ትልልቅ ነገዶች ተወክሎ መሪነቱን ለመጨበት እና ከኔ በላይ ወካይ የለም የሚል ታሳቢን ያነገበ ነዉ::
3. አሁን ነገሮች ሲገለባበጡ እና የኦሮሞ ብሄረተኝነት ጉልበት ሲያገኝ ደግሞ ሌላ የስልታን ጎዳና ስልጥ መቀዬስ አስፈላጊ ሆነ::እኔ ኦሮሞ ነኝ::አማራ የሚባል ነገድ የለም ብሎ ቁጭ::ይሄንንም በማለት አሁንም በስልጣን ወንበር ስር የማድፈጥ ስትራቴጅ ስልት እንጅ የኦሮሞን ህዝብ በተለዬ የመዉደድ ባህሪ ኖሮት አይደለም::የስልታን መንገዱ እጅግ ዘወርዋራ እና ብዙ መሆኑን አልሞ የተነሳዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ሁሉንም ስልቶች እየቀያዬር  እየሞከራቸዉ ይመስላል:: ሁሉም የከተማ ሰዎች እና የአማራ ክልል ህዝብ አማራ ይሁን ሲል አማራ ከዬት ወዴት በሚለዉ መጽሃፉ ያወጀዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ አሁን ደግሞ አማራ የሚባል ህዝብ የለም ብሎ እርፍ::
አንዳርጋቸዉ ጽጌ እና ግንቦት ሰባት በዚሁ አጋጣሚ የከረረ ጸብ ዉስጥ የገቡትን የአማራ ብሄረተኛ ሀይል የመበቀያ ስልትም ያገኙ መስሏቸዉ ሊሆን ይችላል አማራ የለም የሚለዉን ትርክት ይዘዉ የመጡት::አማራ የለም ካልን የአማራ ብሄረተኝነት ይዳከማ ብለዉ አስበዉ መሆኑ ነዉ::
የሽህ እና ህሽ አመታት የአማራ ታሪክን ካለማወቅ የሚመነጭ ሸዉራራ ህሳቤ እና ፈጥኖ ደራሽ ሀሳብ ሁሌም ስሁት ነዉ::የአማራ ህዝብ እንዲህ በቀላሉ የሚፈረካክሰስ ህዝብ አይደለም::የአማራ ህዝብ ሰላም እና እረፍት እስካላገኘ ድረስም የአማራ ወጣቶች እንደ አማራ ብሄረተኛ ወይም እንደ ኢትዮጵያ ብሄረተኛ ወይም በሌላ መልክ ሆነዉ ትግል ከማድረግ አይቆሙም::ስለዚህ መፍትሄዉ የችግሩን ስር ማድረቅ እንጅ ሀሰተኛ ትርክ መፍጠር አልነበረም::
———————
የመደምደሚያ ምክር ለአንዳርጋቸዉ ጽጌ
—————–
ከሁሉም  የሚበልጠዉን ኢትዮጵያዊ  ማንነት በምልዓት ብትለብሰዉ እንዲህ የስነልቦና ቀዉስ ዉስጥ አትገባም ነበር::የኢትዮጵያም ስልጣን እግዚአብሄር ከፈቀደልህ ያንተ ይሆን ነበር::ስልጣን ከእግዚአብሄር እንጂ ከዘርህ ወይም ከፓርቲህ አይመነጭም::ሃሃሃሃ…ለኮሚኒስቶች የሚያስቅ የካህን-ንጉስ ፍልስፍና ነገርኩህ አይደለም?
ለማንኛዉም ኢትዮጵያዊነት ከሁሉም ማንነቶች በላይ መሆኑን ብታዉቅ: አንተም ከሁለቱ ነገዶችም ተወልደህ ቢሆን: ወይም ከኦሮሞ ብሄር ብቻ ተወልደህ ቢሆን: ወይም ቀድሞ አማራ ነኝ እንዳልከዉ ከአማራ ብሄርም ተወልደህ ቢሆን ከንኡስ ማንነትህ የሚበልጠዉ አምንነት ኢትዮጵያዊ ማንነት ነዉ ነዉ::ከአማራነትም: ከኦሮሞነትም የሚበልጠዉን ኢትዮጵያዊ ማንነት በእምነት ብትለብሰዉ ከሁሉም በላይ ትከብር ነበር::
እንዲህ አንዴ አንዱ የነገድ ማንነትህ ትዝ ሲልህ ሌላ ጊዜ እንደሌለ ሲጠፋብህ: ሌላ ጊዜ ከሁለት መወለድህ ሲታሰብህ ባትተህ እና ዋትተህ መመላለስህ ያሳዝናል::እንደ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ የአዳም ልጅ ወንድሜ የማንነትህ ነገር እንዲህ እስከ አንጥንትህ ድረስ ለምን እንደ በላህ ሳስበዉ አሳዘንከኝ::
የሆኖ ሆኖ ተለይቶ የዘር ማጥፋት እየተደረገበት ያለበትን የአማራ ነገድ የለም ስላልክ የምታተርፈዉ የፖለቲካ ትርፍህን አንተዉ ታጭደዋለህ::የአማራ ነገድ በዚህ ወቅት የለም የሚለዉ ሰዉ ሳይሆን የሚፈልገዉ አማራን ለይታችሁ አታጥቁ:ፍትህ አድርጉ:ሁሉንም ኢትዮጵያዉያን እኩል የሚያደርግ ሀገር ፍጠሩ:ሁሉንም ነገዶች እኩል የሚያስተናግድ ፍጠሩ የሚል ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ ነበር የሚፈልገዉ::
ለማኛዉም ኢትዮጵያዊነትን መቶ አመት ነዉ እድሜዉ ብለህ በቅኝ ግዛት የተፈጠረ ሀገር ነዉ ብለህ ብትክደዉም መጽሃፍ ቅዱስ ግን የሚተርክልን ኢትዮጵያዊ ማንነት ከማንኛዉም የነገድ ማንነት በላይ መሆኑን ነዉ::በመጽሃፍ ቅዱስ እግዚአብሄር እራሱ ኢትዮጵያዊ ልጄ ነዉ ብሎ መስክሯል እና::
ኢትዮጵያዊነትን ለኢትዮጵያዊ ሁሉ የሰጠዉ እራሱ እግዚአብሄር ነዉና::የሚቀበለዉ ኢትዮጵያዊ መልካም አደረግ::የማይቀበለዉም ኢትዮጵያዊ መብቱ ነዉ:: ከእዉነቱ ስትቆረጥ ይዘህዉ የምትመጣዉ ትንታኔ ሁሉ ሀስት እና እርስ በርሱ የሚምታት ነዉ::አንዴ አማራ ነኝ: አንዴ አማራ እና ኦሮሞ ነኝ: አንዴ አማራ የሚባል ህዝብ የለም እያልክ መከራህን ታያለህ::አንዴ በስልታን ጥም: አንዴ በበቀል: አንዴም በግል ተራ ፍልስፍና ስትዋልል ትዉላለህ::
ኢትዮጵያዊነት ተፈልጎም የማይገኝ ማንነት ነዉ::ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለዉ ህዝብ እንኳን ቢጥለዉ ሌላ ወገን ያነሳዋል::ጥቁሩ አለም የነጻነት: የእኩልነት: በእግዚአብሄር መንፈስ መወደድን እና በ እግዚአብሄር አይን የታወቀ ህዝብ መሆኑን ማረጋገጫ ቢፈልግ የሚያገኘዉ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ነዉ::
ስለዚህ ዛሬ ኢትዮጵያ የተባለዉ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን አዉልቆ ቢጥለዉ ሌላዉ ወገን አንስቶ ይልብሰዋል::
ኢትዮጵያ ጥሎባት እናንተ ከወያኔ ጋር ሆናችሁ በቀየሳችሁት የነገድ ፖለቲካ ስር ገብታለች እና ገና ብዙ በርካታ ዉጥንቅጦች እና የማምንነት ቀዉሶችን የተሸከሙ ዜጎች ታስተናግዳለች:: አንዴ ይሄኛዉን ነኝ::ሌላ ጊዜ ያኛዉን ነኝ የሚሉ የማንነት ቀዉስ ዉስጥ የሚዳክሩ በርካታ ዜጎች የሚተራመሱባት ሀገር::
በነገራችን ላይ ኢሳያስ አፈወርቂ በአንድ ወገን ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ጥሎ ነዉ ኤርትራዉያንን ከወንድሞቻቸዉ ኢትዮጵያዉያንን የነጣጠላቸዉ::መለስ ዜናዊም በአንድ ወገን ኤርትራዊ ማንነቱን ክዶ ነዉ ኢትዮጵያዉያንን ከወንድሞቻቸዉ ኤርትራዉያንን የነጣጠሏቸዉ::ይሄም ሁሉ የክፋት እና ስልጣን መያዝን እንደ ግብ የመዉሰድ የተሳሳተ ፍልስፍና ነዉ::
የሆነ ሆኖ እግዚአብሄር የታመነ ነዉና  ህዝቤ ያለዉን እና የተወደደ ኢትዮጵያዊነት የተላበሰዉን ህዝቡን ያድናል::
Filed in: Amharic