>

ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የሰዎች ማስፈራሪያ እንዲሆን ተሰርቷል!!! ( ኦቦንግ ሜቶ)

ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የሰዎች ማስፈራሪያ እንዲሆን ተሰርቷል!!!

በምህረትሞገስ

አዲስአበባ፡– ህፃንን በጅብ እንደሚያስፈራሩ ሁሉ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል የሰዎች ማስፈራሪያ ያሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦቦንግ ሜቶ ናቸው።

አቶ ኦቦንግ ሰዎች በብሔር እንዲያስቡ የተሰራውን ያህል በተገላቢጦሽ ሰብአዊነትን እንዲያውቁ በሚያስችል መልኩ መሰራት አለበት ካሉ በኋላ፤ ከብሔርተኝት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን መስበክ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አስጊ ነው። በዓለም በየትኛውም አገር ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክልል በብሔር ተዋቅሯል። የፖለቲካ ፓርቲ በብሔር ከመቋቋሙ አልፎ፤ ቤተዕምነት እና ባንክ ሳይቀር በብሔር ስም ተመስርተዋል። ይህ አደገኛ ነው። አንዱ ነዋሪ ሌላው ሰፋሪ እየተባለ የሚነገረውም ትክክል አይደለም። ሰው በብሔር መለካት የለበትም። ሥራ ማግኘት ያለበት በአቅም መሆን እያለበት በኮታ በብሔር መሆኑ ተገቢ አይደለም። ይህ በአጭሩ ካልተገታ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ብለዋል። ‹‹ህገመንግስት መቀየር ካለበት መቀየር አለበት።

የትምህርት ሥርዓታችን መቀየር አለበት፡›› የሚሉት አቶ ኦቦንግ፤ በየእምነት ተቋማት፣ በየትምህርት ቤትም ሆነ በየትኛውም ቦታ ስለኢትዮጵያዊነት መነገር እንዳለበት ተናግረዋል። በተረፈ አንድ ሰው ያለው የብሔር ማንነት ብቻ አይደለም። የፆታ (ወንድ፣ ሴት)፤ የሃይማኖት፣ የወላጅነት፣ የሙያ እና ሌሎች ማንነቶችም እንዳለው መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

ወደሩዋንዳ ሄደው እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን ሩዋንዳውያን ብሔር ሲጠየቁ የሰው ልጅ ነኝ እያሉ መሆናቸውን እና ኢትዮጵያውያንም የሰው ልጅ ነኝ ለማለት እንደነሱ አንድ ሚሊዮን ህዝብ እስኪያልቅ መጠበቅ እንደሌለበትም ነው ያመለከቱት፤ ከዚህ በኋላ ያለአግባብ ሰው መፈናቀል እና መሞት የለበትም። ሁሉም በሰላም እንዲኖር መሰራት አለበት። ስለብሔር እያሰቡ ከመናቆር ለሙን መሬት በአገር ፍቅር ስሜት ከተሰራበት ምስራቅ አፍሪካን መመገብ ይቻላል ብለዋል። ነገር ግን ህግም ሆነ ህገመንግስት አይሻሻልም ማለት ሆዳምነት ነው። ይልቅ ጉርሻን የመሳሰሉ የአገሪቷን የፍቅር እሴቶች በማጉላት እና በማሳደግ በዘመቻ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

Filed in: Amharic