>

ሀገር ታመሰግናለች - እኔም አመሰግናለሁ!!! (ጠ/ ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ)

ሀገር ታመሰግናለች – እኔም አመሰግናለሁ!!!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ
ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ፡-
• ስለማይበገረው ጽናታችሁ እና ሁሉን ማድረግ ስለሚችለው አስደናቂ አቅማችን በተለየ አክብሮት እና ፍቅር እጅ እነሳለሁ፡፡
• በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን እንኳን ሀገራችንን የሚመለከቱ አበይት ጉዳዮች ሲገጥሙን ከመቅጽበተ አይን ለሚያጋምደን- ያለምንም ልዩነት እንደ አንድ እናትና ልጅ ለሚያዛምደን እና ያለመለያየት ለሚያዋህደን ዘመን አይሽሬ ኢትዮጵያዊ መንፈሳችን ያለኝን የማይናወጥ ፍቅር በክብራችሁ ጥላ ስር ሆኜ በክብር እገልጻለሁ፡፡
• መቼም- ማንም የትኛውንም የክፋት ሴራ የሚሰራ የጥፋት አበጋዝ አብሮነታችንን ሊያጠለሽ ቢጥር እንኳን አብሮነታችን ከነፍሳችን ውስጥ የተሸመነ እንጂ ከስጋችን ላይ የተጎነጎነ አይደለምና አብሮነታችንን ላጸደለው የአረንጓዴ አሻራ ድላችሁ የተለየ ምስጋናዬን በፍቅሬ ሙዳይ ሞሽሬ እነሆ ልኬያለሁ፡፡
ሀገር ታመሰግናለች- እኔም አመሰግናለሁ!
የኢትዮጵያን አረንጓዴ ጸጋ በመመለስ አረንጓዴ አሻራ እንድናሳርፍ ያቀረብኩትን ጥሪ በመቀበል ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓም የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ለችግኝ ተከላ ወጥቷል፡፡
ከጨቅላ ሕጻናት እስከ ዘጠና ዓመት አዛውንት፣ ከጎዳና ተዳዳሪዎች እስከ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ፣ ከታክሲ ተራ አስከባሪዎች እስከ ጸጥታ አስከባሪዎች፣ ከገበሬዎች እስከ ግብርና ባለሞያዎች፣ ከልማት ጣቢያ ሠራተኞች እስከ ከፍተኛ ኤክስፐርቶች፣ ከተማሪዎች እስከ መንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከሀገር ቤት እስከ ዳያስፖራ፣ ከድምጻውያን አስከ ተዋንያን፣ ከአትሌቶች እስከ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች፣ ከጋዜጠኞች እስከ ፊልም ባለሞያዎች፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ – ያልተሳተፈ የኅብረተሰብ ክፍል አልነበረም፡፡
ይህ የተሳትፎ ማእበል እና የእምቢ ለሀገሬ ሆታም በታሪክ ማህደር ላይ መቼም አይረሳም፡፡ሕዝቡ አረንጓዴ አሻራውን ለማኖር የነበረውን ትጋትና ቆራጥነት የሚያሳዩ አስደናቂ ክንዋኔዎችን አይተናል፡፡
የአረንጓዴው አሻራ አርበኛ ከማለዳው 12 ሰዓት አስቀድሞ ወጥቷል፡፡ 
አያሌ ባለሀብቶች መኪኖቻቸውን በራስ ተነሣሽነት አንቀሳቅሰዋል፤ ዳያስፖራዎች በገንዘባቸው አግዘዋል፤ ኮርፖሬሽኖች ኃላፊዎቻቸውንና ሠራተኞቻቸውን አሠማርተዋል፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች ራሳቸውን አደራጅተው አሻራቸውን ለማኖር ወጥተዋል፤ ሙሽሮች በሠርጋቸው ዕለት ሱፍ- ቬሏቸውን ልብሰው ተገኝተዋል፤ ችግኝ ተካዮችን ለማበረታታት ቀረርቶ፣ ሽለላ፣ ፉከራ፣ ባሕላዊ ዘፈን እና እልፍ አእላፍ የህብር ሆታ በመላ ኢትዮጵያ- በመላ ኢትዮጵያውያን ቋንቋ እና ባህል ከጫፍ እስከ ጫፍ ተስተጋብቷል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶች ተከላውን በጸሎት አስጀምረዋል፤ እናቶች ምግብና መጠጥ አዘጋጅተው ለተካዮች አቅርበዋል፤ ወደ ውጭ የሚጓዙ ሰዎች የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት በዋዜማው ተክለዋል፤ ሚዲያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ዜናውን ለመሸፈን ተቀናጅተው ሠርተዋል፤ ዓይነ ሥውራን በኬን፣ አካል ጉዳተኞች በዊል ቸር፣ ወላጆች አራስ ልጆቻቸውን አዝለው ለተከላው ተሠማርተዋል።
ልጆች በእናታቸው እቅፍ፣ አረጋውያን በከዘራ ወደ ተራሮች ተምመዋል፡፡ ችግኝ ባጠረባቸው ቦታዎች ዜጎች በገዛ ገንዘባቸው እየገዙ ሀገራዊ ተልዕኳቸውን ተወጥተዋል፡፡
ሀምሌ 22 ማለዳ ከኢትዮጵያ ሰማይ ስር የነገሰው ትጋት፣ አብሮነት፣ ፍቅር፣ ተነሳስኦት፣ ጽናት እና የእናሳካዋለን ስሜት ችግኝ ከመትከልም በላይ የሚገለጽ ድንቅ ድል አጎናጽፎን በድል ተጠናቋል።
የሐምሌ 22ቱ ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ሕዝቡ በአንድነት ወጥቶ ችግኝ የተከለበት ብቻ ሳይሆን ሐሳቡን የገለጠበትም አጋጣሚ ነበር፡፡ ሀገሩን የሚወድ፣ ለሀገሩ የሚጠበቅትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ የሆነ፣ ለትክክለኛ ዓላማ የሚያሠማራው ሲያገኝም አንድ ሆኖ የሚነሣ ሕዝብ እንዳለን አይተናል።
ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት፣ ከግላዊነት ይልቅ ሕዝባዊነት፣ ከራሱ ይልቅ ለሀገሩ፣ ከሆዱ ይልቅ ለክብሩ የሚሞት ሕዝብ እንዳለንም ነግሮናል፡፡ ከትናንሽ አጀንዳዎች ይልቅ ታላላቅ ሀገራዊ ግዳጆች የሚማርኩት ሕዝብ መሆኑን ገልጦልናል።
ከአቧራ ይልቅ ለአሻራ ቦታ የሚሰጥ ሕዝብ መሆኑን በማያወላዳ መልኩ አስረግጦ- አስረድቶናል፡፡ ታላቅ ሐሳብ የሚማርከው ታላቅ ሕዝብ መኖሩን አመላክቶናል፡፡ ችግር ነቅሎ ችግኝ የሚተክል ሕዝብ እንዳለንምበውል ተረድተናል።
ይህ ታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ እንዲሳካ የበኩሉን ያልተወጣ የኅብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ ነገር ግን ከጣት ጣትይበልጣል እንደሚባለው የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ወገኖች አሉ፡፡
ሂደቱን የመራው ብሔራዊ ኮሚቴአባላት፣ ሂደቱን ያስፈጸሙት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት፣ መረጃው የተሰባሰበበትን መንገድና ሶፍት ዌር ያዘጋጁ ባለሞያዎች፣ ከክልል እስ ወረዳ ያሉ አመራሮች፣ እስከ ችግኝ መትከያ ጣቢያ ድረስ በተዘረጋው መረብ ተሠማርተው መረጃውን እያጣሩ ሲያሰባስቡ የነበሩ የመረጃ ወኪሎች፣ የተስተካከለ መረጃ ብቻ እንዲመዘገብ ሲከታተሉ የነበሩ የመረጃ አጣሪዎች፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀናጅተው ሲሠሩ የነበሩ መላው የሀገራችን ሚዲያዎች፣ ለኅብረተሰቡ ትምህርት ሲሰጡና ሲያቀናጁ የነበሩ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች፣ የየመሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፤ ላከናወናችሁት የላቀ የመሪነት ተግባር በራሴና በኢፌዲሪ መንግሥት ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ይህ ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ ቀን ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከተነሡ፣ ያሰቡትን ሳያሳኩ እንደማይመለሱ ለሺኛ ጊዜ መልሰው ያረጋገጡበት ነው፡፡ 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዐቅደን ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለናል።
የችግኝ እጥረት ባይገጥመንና ቀኑ ባይመሽ ኖሮ እንደ ሕዝቡ አወጣጥ ከዚህም በላይ የመሥራት ዐቅም ነበረን፡፡ ከዚህ ሥራችን በበጎው እንደተደሰትን ሁሉ ከስሕተቶቻችንም እንማራለን፡፡ ይህ ተግባር የአንድ ቀን ዘመቻ ብቻ አይደለም፤ ክረምቱን ሙሉ የምንሠራው ነው፡፡ ሀገራችን እንደ ስሟ ለምለም እስክትሆን ድረስ በየዓመቱ እንቀጥልበታለን።
ያገኘናቸውን በጎ ነገሮች አጠንክረን፣ ድክመቶቻችንን አርመን ቀጣዩን የተሻለ እናደርገዋለን፡፡ ከሀገራችን ጥቁር ሰማይ ስር በጥቁር መዳፍ የተሸመነ አረንጓዴ ሸማ ጥቁር አፈራችን ላይ እንዘረጋለን፡፡ የታላቅነታችን ሚስጥር የተሰቀለችበትን ክር ጠንቅቀን የምናውቅ ህዝቦች ነንና ከአዝማናት ታላቅነታችን ጋር እንደገና እንገናኛለን።
መውለድ ብቻ ልጅን እንደማያሳድገው ሁሉ መትከል ብቻ ዛፍን አያጸድቀውም። የወለድናቸውን ማሳደግ፣ የተከልናቸውንም መንከባከብ አለብን። ሕዝቡ በተከላው ቀን ቃል በገባው መሠረት የእገሌ ሥራ ነው ሳይል የተከላቸውን ዞሮ ማየት፣ መንከባከብና ከጥቃት መከላከል አለበት፡፡ ባለ ሀብቶች ባለሞያ መድበው የተከሏቸውን ችግኞች እንደሚያሳድጉ አምናለሁ፤ ወጣቶች የተከሏቸውን ችግኞች ለማየት ወደ ተራሮች ስፖርት እየሠሩ እንደሚወጡ ተስፋ አደርጋለሁ፤ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞችም ተራ ገብተው ችግኞቻቸው የት እንደደረሱ እንደሚጠይቁ እርግጠኛ ነኝ። የተከልናቸውን ችግኞች የማሳደግ ሀገራዊ ዐቅማችን ከ50 በመቶ በታች ነው።
 ይህን ውሱንነት በመቅረፍ ቢያንስ በቀጣዮቹ ዓመታት ወደ 70 በመቶ ማሳደግ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ወልዶ ማሳደግ የሚያውቅበት የሀገሬ ሕዝብ ተክሎ በመንከባከብ ታሪክ እንደሚሠራ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡
ለአረንጓዴ አሻራ ቀን ስኬት የሚጠበቅባችሁን ሁሉ ያደረጋችሁ ሁሉ ታሪክን በደማቅ ቀለም ጽፋችኋልና በድጋሚ አመሰግናችኋለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ ሠሪ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም
Filed in: Amharic