>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8626

የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ድምፅ!!!  (ታዲዮስ ታንቱ)

የሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ድምፅ!!!
 ታዲዮስ ታንቱ
~  “የኢትዮጵያ ነፃነት አይገሰስም! 
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖትም አይረክስም!” 
     ( ኢትዮጵያዊው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ) 
★ የኢትዮጵያውያኑን ሰማእታት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስንና የጎሬውን ሰማእት ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን አስታውሳችሁ  ወደ ዘንድሮ ሊቃነ ጳጳሳት ህይወት መለስ ብላችሁ ትገቡበት ቀዳዳ፣ ትሸሸጉበት ጥግ እንዳታጡ ተጠንቀቁ።
የሰማዕቱ አርበኛና ሐዋርያው ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነት ውሏቸው።
   …ትኩሱን ደማቸውን ውሾች ልሰዋል። አሁን ቀዝቅዟል። ከአፈር ተዋህዷል። ጉንዳኖች ደግሞ ሰፍረውበታል። በተራቸው የቅዱሱን ደም ይዋኙበታል። መስቀላቸው ከቀኝ እጃቸው አጠገብ ወድቋል። ግራ እጃቸው ከአምባር መዋያ መልስ በጭቃ ተለውጧል። ጥፍሮቹ እንኳን አይታዩም። ልብሳቸውም በጭቃ ተለውሷል። ራሳቸው በጥይት ተፈረካክሷል። አንድ አሞራ እየበረረ መጥቶ በሬሳቸው ላይ ሊያርፍ ሲል በሰዎች ተባርሯል። መላ አካላቸው ደቅቋል። ዓይኖቻቸው ወደ አረንጓዴነት ተቀይረዋል። አፋቸው በመጠኑ ተከፍቷል። ሕዝበ ክርስትያን በውስጡ ለውስጡ ያለቅሳል። ሬሳቸውን ደፍሮ የሚያነሳ ግን ማንም አልነበረም። ምክንያቱም የፋሽስቶች ውሳኔ በቅፅበት ተፈፃሚ ይሆንበታልና ነው።
•••
በዚህ ሁኔታ ሬሳቸው ለብዙ ሰዓታት ተዘርሮ ውሏል። የጨው ተራ አፈር በሐምሌ ዝናብ ቦክቷል። ሰዎች የጀግናውን ሐዋሪያ ሬሳ ላለመርገጥ ሲጠነቀቁ ይስተዋላል። አንዳንዶች ግን በጉዳያቸው የህሊና ስሌት ተመስጠው ሲገሰግሱ ጭቃ በእጅጉ ያፈናጥሩበታል። ከመንገድ ዞር ለማድረግ እንኳን የፋሽስቶች ፈቃድ ሊወርድ ይገባል። ይህ ሳይደረግ ማን ይደፍራል? በገዛ ስሜቱ ስሜቱን ያስተናገደ ይገደላል። ሬሳው ቢያድርም በዚያው ይቀጥላል። በድንገት ግን ለውጥ ተስተውሏል። የጀግናው ሐዋሪያ ሬሳ ተነስቷል። በቦታው አልነበረም። ማን ወሰደው? ሲያልፉ ያዩት ሲመለሱ አጥተውታል። ወስዶ የደበቀው ይታወቅ።የሁሉም ጥያቄ ሆኗል። የፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ ደግሞ በጣም ተናድዷል። የሚቀበርበትን ቦታ መወሰን ፈልጓል። ምን ጉድ ነው እናንተዬ? ዳኛው ከመኻል ወንበር ተቀምጦ ቅጣቱን አፅድቋል። አገዳደሉም በትዕዛዙ ተፈፅሟል። አሁን ደግሞ የቀብር ቦታ ምርጫ እንዴት የዳኛ ኃላፊነት ሊሆን ይችላል? የእኝህ ሐዋሪያ ግፍ አልበዛም ትላላችሁ? ሬሳቸው ከተቀበረበት ከጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ቅጥር ግቢ ተቆፍሮ እንዲወጣ ተደርጓል። የዳኛውን ትዕዛዝ ዳኛው ራሱ ካልቀለበሰው ማን ይቀለብሰዋል? ከከተማ ዳር ተወስዶ በሚስጥር ስፍራ እንዲቀበር ለለማዳ አገልጋይ ባንዳዎች ትዕዛዝ ወርዷል። በምክንያቱ ምክንያት በሚስጥር ተወስዶ በድብቅ ከአፈር ውስጥ ገብቷል። አቡኑ በአደባባይ ተገድለዋል። ነፍስ አልባ አካላቸው በበድን ይዘቱ ተሰውሯል።
•••
አርበኛውና ሐዋሪያው ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ በፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል መገደላቸው በታሪክ ዓይን በቦግታ ይስተዋላል። ጥያቄ አይታሰብም! የባንዳዎች ሎሌያዊ ሚና ግን በደረጃው ዘወትር አለመታሰቡ ለምንድን ነው? ተገቢም አስፈላጊም ጥያቄ መሆኑን አንጣ!! በታሪክ ሐቅ ላይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ወግ የለም። እውነት እንደ ወረደ ለትውልድ ይውረድ። ባንዳ ከባዕዳን ወራሪ ባላነሰ ደረጃ ኢትዮጵያን ጎድቷታል። ታሪካችን ደግሞ ከባንዳና ከከሐዲ ነፃ ሆኖ አያውቅም። ይህ ትውልድ የታሪካችንን ታሪካዊ ፍሰት አይጣ!! ጀግኖች አገራችንን ጠብቀው ያቆዩት በየዘመኑ የተነሱ ወራሪዎችንና ባንዳዎችን ከትቢያ ጋር በማዋሐድ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህ እውነት ነው። እውነትም ይህ ነው። ሌላ እውነት የለም!!
•••
በአሁኑ ሰዓት ዳኞች ከአንዲት ጥቁር አውቶሞቢል ወርደዋል። ከችሎት አዳራሽ አጠገብ ደርሰዋል። የመሐል ዳኛው ኢጣሊያዊው ኮንቴ ዴላ ፖርቶ ከፊት ሆኖ ሁለት ለማዳ አገልጋይ ባንዳ ኢትዮጵያዊያንን ተከትለውታል። ወደ አዳራሽ እየገቡ ነው። አሁን ሦስቱም ዳኞች ገብተዋል። ህዝቡ ለክብራቸው ከመቀመጫው ተነስቷል። አዳራሹ በጆሮ ጠቢዎች ተሞልቷል። ጆሮ ጠቢዎቹ ለማዳ አገልጋይ ወዶ ገባ ሆድ አደር ኢትዮጵያዊያን እንደነበሩ ታውቋል። ጥቂት የውስጥ አርበኛ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በአሳማኝ የቋንቋ ቃና አቡነ ጴጥሮስን እያወገዙ ተሰምተዋል። ከጆሮ ጠቢዎች መካከል ኢጣሊያንኛ የሚናገሩ ከሁለት እንደማይበልጡ ለማወቅ ተችሏል። በችሎቱ ላይ ከፍተኛ የሐዘን ድባብ ይነበባል።
•••
ኢጣሊያዊው የመሐል ዳኛ ፈገግ በማለት ህዝቡ እንዲቀመጥ ለወለሉ ትዕዛዝ አወረደ። ወዲያው እሱም ተቀመጠ። ቀጥሎ የግራ ዳኛ ወንበር ይዟል። ነጋድራስ ወዳጆ ዓሊ ይባላል። ነጋድራስ ወዳጆ ዓሊ የክፍሌ ወዳጆ አባት መሆኑ ይታወቃል። ክፍሌ ወዳጆ ደግሞ የትግሬ ተወላጅ ለሆኑ ባንዳዎች ታማኝ ሎሌ እንደነበረ ይታወቃል። የቀኝ ዳኛው በቀኝ ተቀምጠዋል። ብላታ አየለ ገብሬ ይባላል። የመኻል ዳኛውን ስሜት ይከታተላል። ባንዳ በጌታው ሳንባ ይተነፍሳል። ሕሊናውን በሊሬ የሸጠ ምን ሊሆን ይችላል? ነጋድራስ ወዳጆ ዓሊ በተፈጥሯዊ ሞት ከዚህ ዓለም ተለይቷል። ብላታ አየለ ገብሬን ግን ታህሳስ 7 ቀን 1953 ዓ.ም ብርጋዴየር ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ገድሎታል። እርግጥ ነው በዕለቱ አርበኞችም ተገድለዋል። ለኃጥአን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል። የንዋይ ወንድማማቾች የግድያ የሒሳብ ስለት ግን በዚህ ምሳሌያዊ አነጋገር አይስማማም። አንዳንድ የአምስት ዓመት አርበኞች የሃያ አመት ቀማኞች እንደ ነበሩ በሰንጠረዥ አስቀምጧል። ገዳዮቹ በግልፅ ናቡቴ መኳንንትን ከህዝብ ጫንቃ ላይ ማውረድ የሀገር ባለውለታ ጀግና አርበኞችን መፃረር እንዳልነበረ ተናግረዋል። አንድ! ሁለት! አንድ! ሁለት! ይህ የነዋይ ወንድማማቾች ድምፅ ነው። ከአረንጓዴው ሳሎን!!
•••
አቡነ ጴጥሮስ ከወንበዴዎች ጋር በማበር ወንጀል ተከስሰዋል። ፍርዱ ምን ሊሆን ይችላል? አቡኑ ውጭ ተቀምጠዋል። እጆቻቸውን በረጅም ሰንሰለት ታስረዋል። ሁለት ለማዳ ባንዳ አገልጋዮች ባጠገባቸው ቆመዋል። አንዱ ባንዳ ኢጣሊያንኛ ይናገራል። ሁለተኛው ጆሮውን ቢቆርጡት አይሰማም። ዳኞቹ ለጥቂት ደቂቃዎች ሲወያዩ ቆይተዋል። የመኻል ዳኛው ሰዓቱን ተመለከተ። በመቀጠል ወደ ተቀመጠው ሕዝብ አየ። ብዙም አልቆየም። ከቆሙት ኢጣሊያዊያን ወታደሮች አንዱን ጠራው። ወታደሩ ቀረብ በማለት ወታደራዊ ሰላምታ ሰጠው። አንቡነ ጴጥሮሥ እንዲገቡ እንዲያደርግ ታዘዘ። ወታደሩ በታዛዥነት አቋም ለሁለተኛ ጊዜ ለዳኛ ሰላምታ አበረከተ። ትዕዛዙ ለአቡኑ ጠባቂዎች ከመቅፅበት ደርሷል። ጠባቂዎቹ አቡነ ጴጥሮስን ይዘው ተንቀሳቅሰዋል።
•••
ትርጁማኖች ተነስተው ቦታ ይዘዋል። ሁለት ናቸው። አንደኛው ደጃዝማች አርአያ ዋሴ የተባለ ሰው እንደነበር መረጃ ይዘናል። ሁለተኛው ደግሞ ፊታውራሪ ሮዛሪዮ ተብሎ ይታወቃል። ሁለቱም ከማስተርጎም የዘለለ ሚና አልነበራቸውም። አሁን አቡነ ጴጥሮስ ከችሎት አዳራሽ ገብተዋል። ታዳሚው ሕዝብ ከንፈሩን ይመጥጣል። የመኻል ዳኛው በኢጣሊያንኛ የተደራጀውን የክስ ዝርዝር በደጃዝማች አርአያ ዋሴ አማካኝነት ለአቡነ ጴጥሮስ አሳውቋል። አቡነ ጴጥሮስ በደንብ ሰምተዋል። አቡኑ ምንም ነገር ቢመጣ በፀጋ ለመቀበል ወስነዋል። ለሀገራቸው ነፃነት፣ አንድነትና ሉአላዊነት እንደማያቅማሙ ፍርጥም ባለ ቋንቋ መልስ ሰጥተዋል። ይህም በአስተርጓሚው ተተርጉሟል። በዚህ የድፍረት መልስ የመኻል ዳኛው ተናድዷል። ወዲያው ሶስቱም ዳኞች አቡነ ጴጥሮስ በአደባባይ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ በመወሰን መዝገቡን ተመላሽ አድርገዋል። በፈጣን ችሎት አስቸኳይ ውሳኔ ተሰጥቷል። አለቀ።
•••
ሐምሌ 22 ቀን 1928ዓ.ም አቡነ ጴጥሮስ በጥይት ይደበደባሉ። ወሬው በመላው አዲስ አበባ ተሰምቷል። ቁርጥ ቀን ሆኗል። በዚያን ጊዜ ጨው ተራ ተብሎ ይታወቃል። ዛሬ ከማስታወቂያ ሚንኒስቴር ሕንፃ ዝቅ ብሎ የሚገኝ ስፍራ መሆኑን እንወቅ። ከጧቱ ሦሥት ሰዓት አንስቶ ጨው ተራ በሰው ተጨናንቋል። ጆሮ ጠቢው በበኩሉ ይርመሰመሳል። አራት ሰዓት ሲሆን አቡነ ጴጥሮስ በበርካታ ለማዳ አገልጋይ ባንዳዎችና በጥቂት ኢጣሊያዊያን ወታደሮች ተከብበው ከጨው ተራ ደረሱ። ከፊታቸው ድፍረት ይነበባል። ዘለዓለማዊ መንፈሳቸውን ለሟች ስጋ ላለማስገዛት ፀንተዋል። እንደ አብርሃም በግ ተነድተዋል። አሁን ለመገደል ከተረመረጠው ስፍራ ደርሰዋል። ጥያቄ አልተነፈጉም። ዓይንዎት በጨርቅ እንዲሸፈን ይፈቅዳሉ? መልሥ ለመስጠት አላቅማሙም። ፊታቸው ባይሸፈን ደስተኛ መሆናቸውን አረጋገጡ። ተኳሽ ጓድ ተዘጋጅቷል። አቡነ ጴጥሮስ ፊታቸውን ወደ መርካቶ አቅጣጫ እንዲያዞሩ ተደረጉ። ዓይኖቻቸው እንዳልተሸፈኑ ልብ በሉ። ስምንት ተኳሾች አንድ ላይ አነጣጠሩባቸው። አዛዡ ከጥቂት ጊዜአት በኃላ ትዕዛዝ ይሰጣል። አቡነ ጴጥሮስ በልባቸው ፀሎት ላይ ናቸው። አምላኬ ሆይ ግፈኞች እኔን ባሪያህን ሊገድሉኝ ተዘጋጅተዋል። ለሀገሬና ለሐይማኖቴ እሞታለሁ። ወዳንተ እመጣለሁ። ነፍሴን ተቀበላት። ሀገራችንን ጠብቃት።
•••
አዛዡ አሁን ጮኽ ባለ ድምፅ ትዕዛዝ ሰጠ። ስምንቱም ነፍሰ ገዳዮች ተኮሱባቸው።አቡነ ጴጥሮስ ወደቁ። የሕክምና ክፍል አዛዥ በወደቁበት ገልብጦ ተመለከታቸው ነፍሳቸው ገና ከሥጋቸው እንዳልተለየች አስተዋለ። ወዲያው ሽጉጡን መዝዞ በሶስት ጥይት ጭንቅላታቸውን አከታትሎ በመምታት ጨረሳቸው።
•••
አርበኛውና ሐዋሪያው ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ የኢጣሊያን ገናናነት አምነው እንዲቀበሉ ብዙ ተለምነዋል። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪቃ የኢጣሊያ ቅኝ ግዛት መሆኗን አምነው ከተቀበሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን መሪ እንደሚሆኑ ተነግሯቸዋል። ግን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም። ባንዳ መነኩሴ። ከመባል በላይ ምን ሞት አለ? የቪክቶሪያ አማኑኤልን ንጉስነትና የቤኒቶ ሙሶሎኒን ቻንስለርነት ከዕውቅና እርከን አላሳደጉም። ከሮማ ውድ ዋጋ ያለው ሽልማት እንደሚጠብቃቸው ተገልፆላቸዋል። አቡኑ ግን በንቀት መልሥ አልፈዋል። ውብ አውቶሞቢል በትዕዛዝ ከኢጣሊያ ሀገር እንደሚመጣላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል። መልሳቸው ግን የተለመደ እምቢታ ሆነ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሊሬ እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸዋል። አቡነ ጴጥሮስ ግን ምንም ዓይነት ቁሳዊ ሀብት አልለወጣቸውም። በአማላጅ ጋጋታ አልተበገሩም። ይልቁንም ምድሪቱም ጭምር ለኢጣሊያን እንዳትገዛ አወገዟት። “የኢትዮጵያ ነፃነት አይገሰስም! የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐይማኖት አይረክስም!” ይህ የ አቡነ ጴጥሮስ ድምፅ ነው።
•••
ሰማዕትነትን በድፍረት የተቀበሉት አርበኛውና ሐዋሪያው ብፁዕ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ በመስከረም ወር 1868ዓ.ም በሰላሌ ዋና ከተማ በፍቼ ተወለዱ። በሕፃንነታቸው በጎሐ ፅዮን ማርያም ቤተክርስትያን ትምህርት መጀመራቸው ታውቋል። በመቀጠልም በደብረ ሊባኖስ ትምህርታቸውን በስፋት ተከታትለዋል። ከዋሸራ ጎጃም በቅኔ መምህርነት ተመርቀዋል።
•••
አርበኛውና ሐዋሪያው አቡነ ጴጥሮስ እስከ 1921ዓ.ም ድረስ በየቦታው እየተዘዋወሩ አስተምረዋል። የአድባራት አለቃም ሆነው አገልግለዋል። በ1921ዓ.ም ወደ ግብፅ ሔደው ተሹመው መመለሳቸውም በህይወት ታሪካቸው ውስጥ ተወስቷል። ከግብፅ ሲመለሱ የመንዝና ወሎ ጳጳስ ሆነው ሠርተዋል። በ1928ዓ.ም ደግሞ ማይጨው ዘምተዋል። የወገን ጦር ወደ ኃላ ሲመለስ እሳቸውም ተመልሰዋል። ነገር ግን ትግላቸውን አላቋረጡም። ይልቁንም በግንደ በረትና በሰላሌ የተጠናከረ የአርበኝነትን እንቅስቃሴ ያደርጉ ገቡ። በእርግጥ እሳቸው ራሳቸው ጠብመንጃ ይዘው ጥይት አጉርሰው በፋሽስቶች ላይ የተኮሱበት ወቅት አልነበረም። ነገር ግን ህዝቡን በማረጋጋትና አርበኞችን በማስተባበር በኩል ትልቅ ተግባር አከናውነዋል። መጠባበቂያ ጠብመንጃ ባለበት አካባቢ ደግሞ የመሳሪያ አጠባበቅ አመራር መስጠታቸው ታውቋል። አቡነ ጴጥሮስ የጀግናው የደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ የንስሐ አባት እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል።
•••
በእውነት ስለእውነት እንናገር! አርበኛውና ሐዋሪያው አቡነ ጴጥሮስ ንፁሕ የሃይማኖት አባት ነበሩ። የሕይወት ታሪካቸው ይመሰክራል። ተምረውና አገልግለው በታላቅ ሰማዕትነት ወድቀዋል። ወንጀል አልሠሩም። ከባለስልጣናት ተመሳጥረው ጳጳስ ገልብጠው በትዕዛዝ ጳጳስ አልተደረጉም። በውጭ አሀገር አልኖሩም። ሀብት ንብረት አልነበራቸውም። ለሆዳቸው ኖረው የሞቱ አድር ባዮችን እየመረጡ ፍትሐተ ጸሎት አላደረጉም። እንደዘመናችን ጳጳስ ተብዬዎች አራት ጥይት የማይበሳው መኪና አልነበራቸውም። መነኩሴ በቁሙ የሞተ መሆኑን አውቀዋል።
•••
ስሞት በመስተዋት ሳጥን ቅበሩኝ ብለው አልተናዘዙም። ለሟች ተክለ አካል መታሰቢያ በምዕመናን ገንዘብ የተሠራ ሐውልት አልነበራቸውም። ሞት ላይቀር ለበስባሽ ሥጋ ጓጉተው ሲታመሙ የሃምሳ ሽህ ብር መርፌ የሚወጉ ጳጳስ አልነበሩም። ሽጉጥ ታጥቀው የሚዞሩ አስመሳይ ጳጳስም አልነበሩም። በቤተክርስትያን ውስጥ መነኩሴ የሚያስረሽኑ ጳጳስ አልነበሩም። አንደበታቸው ሃይማኖታዊ ቃላትን ብቻ የሚያፈልቅ እውነተኛ የምዕመናት አባት ነበሩ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀኖናን በጥብቅ የሚያከብሩ ጳጳስ ነበሩ። እንደ ዘመናችን አንዳንድ ጳጳስ ተብየዎች ቅድስት ማርያም እንደማንኛይቱም ሴት ናት እያሉ በሃይማኖት የሚሳለቁ የቀበሮ ባህታዊ አልነበሩም። ማንም የፈለገውን ሃይማኖት መከተል እንደሚችል በመስበክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሐይማኖትን ምዕመናንን ሃይማኖታዊ ሞራል አልተፈታተኑትም። አቡነ ጴጥሮስ ለሃይማኖታቸው ኖሩ! ለሀገራችን ሰማዕት ሆኑ! አቡነ ጴጥሮስ ታላቅ ሐዋሪያ ነበሩ። ታላቅ ተግባር ፈጸሙ፣ በታላቅ ሰማዕትነት ወደቁ። እውነተኛ የሃይማኖት አባቶች በታላቁ ሐዋርያ በአቡነ ጴጥሮስ መንፈሳዊ ኩራት ይሰማችሁ ኢትዮጵያ እናታችንም ትኩራ!!
Filed in: Amharic