>
5:13 pm - Monday April 19, 7756

ታከለ ኡማ ምን እያሉ ነው ?  (ሙሉአለም ገ/መድህን)

ታከለ ኡማ ምን እያሉ ነው ? 
( ሙሉአለም ገ/መድህን)
‹‹ኦሳ ማዕከሉን በአዲስ አበባ እንዲከፍት ምክትል ከንቲባው ጠየቁ›› ይላል የቢቢቢ አማርኛ ዘገባ፤ ‹‹መልካም›› ብለናል፡፡ ኢትዮጵያዊ እስከሆኑ ድረስ መብታቸው ነው፡፡ የእኔ ጥያቄ ሌላ ነው፡፡
የኦሮሞ ጥናት ማዕከል (OSA) ከተሰረተ 33 ዓመት ሆኖታል፡፡
 በስደት ባሉ የኦሮሞ ምሁራን የተቋቋመው ይሄ የጥናት ማዕከል፣ የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት ምስረታ ፈጽሞ በማይቀበሉ ከቶም ‹‹ኢትዮጵያ በኦሮሞ ላይ  የቅኝ ግዛት ወረራ ፈጸመች›› የሚል የታሪክ ብያኔ ያላቸው አካላት ያቋቋሙት ማዕከል ነው፡፡ በዚህ ማዕከል ውስጥ ከሀገረ መንግስት አመሰራረት፣ ከታሪክ ውርስ ግንዛቤ፣ ከሀገር አወቃቀር ቅርጽ ጋር በተያያዘ ተሰሩ የተባሉ ጥናቶች ሁሉ ነባሩን የኢትዮጵያን ማህበራዊ ህሊናም ሆነ ሥነ-መንግሥታዊ ትሩፋቶች በአውዳሚነት የሚረዱ፣ የጋራ እሴቶችን ፈጽሞ የሚክዱ፤… በርካታ ጥናቶች ቀርበውበታል፦
 አማራ እንደ ወራሪ ተስሎ ቀርቧል!
የነጻነት እና የሥልጣኔ ባለቤት የነበሩት ዳግማዊ አጼ ምንልክ በአፍሪካዊ ‹‹ሂትለር›› አምሳያነት ቀርበዋል!
ከአገር ገንቢነት ሚናው ጋር በተያያዘ አማራ ከሌሎች የባህል ቡድኖች ጋር የፈጠረውን መስተጋብር ተከትሎ ሸዋን በመሳሰሉ አካባቢዎች የሚታየውን የባህል ተዋሃጅነት በጎደፈ ማንነት የሚያብጠለጥሉ የ‹‹ጥናት›› ወረቀቶች በኦሮሞ የጥናት ማዕከል ቀርበዋል፡፡
በአንጻሩ  ዘርን አመንምኖ እና አሳስቶ የሚያጠፋ፣ ባህልን፣ ቋንቋንና ማህበራዊ ማንነትን ጨፍልቆ እሳት እንደገባ ቅቤ አቅልጦ በአስደናቂ ፍጥነት ከምድረ ገጽ የሚያጠፋውን የገዳ ሥርዓት እና ሞጋሳን እጽብ ድንቅ የሆነ ‹‹የአፍሪቃ የዴሞክራሲ ተምሳሌት›› በሚል በ‹‹ጥናት›› ወረቀቶች ውዳሴ ቀርቧል- በማዕከሉ፡፡ ላለፉት ሠላሳ ሦስት ዓመታት በዚህ ማዕከል ሌላም ሌላም ተብሏል፡፡ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የጥናት ጉባኤውን አካሂዷል፡፡
የእኔ ጥያቄ ከላይ የተመለከቱ ነጥቦችን የተንተራሰ አይደለም፡፡ ጥያቄየ ወዲህ ነው፡- ምክትል ከንቲባው በኦሳ የጥናት ጉባኤ ማጠቃለያ ላያ  ‹‹ማህበሩ ከዚህ በፊት ያካሄዳቸውን ጥናቶች የፖሊሲና መመሪያዎች መሰረት መሆን ስላለባቸው በተቀናጀ መልክ በማዘጋጀት ሥራ ላይ እንዲውሉ መድረግ አለበት›› ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ጥናት ማዕከል (OSA) ለኦነግ ‹‹አይዶሎግ›› ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱም የሚረሳ አይደለም፡፡ እናስ ለኦነግ ሲያገለግሉ የነበሩ መመሪያዎችን ነው የአገር ፖሊስና መመሪያ እንዲሆኑ ምክትል ከንቲባው ማሰሰቢያ የሰጡት?
እስኪ የሚከተሉትን የ‹‹ጥናት›› ውጤቶች ከጥናት ማዕከሉ ድረ-ገጽ አውርዳችሁ አንብቧቸው፡፡
• ‹‹The Survival of Oromo Nationalism››  Hamdesa Tuso (1986)
• ‹‹Beyond the Oromo-Ethiopian Conflict››  Mekuria BuIcha (1993)
• ‹‹The Oromo, Change and Continuity in Ethiopian Colonial Politics›› Asafa Jalata (1993)
• ‹‹Arsi Oromo Political and Military Resistance Against the Shoan
Colonial Conquest (1881-6)›› Abbas Haji (1995)
• ‹‹A Short History of ‘Oromo Colonial Experience1870’s- 1990’s: Part One 1870’s  to 1935››  Mohammed Hassen (1999)
• ‹‹Looga Oromoo Walloo (Wallo Otomo Dialect)›› Tamane Bztzma  (2006)
 ” አቢሲኒያዊያን ኦሮሞን እንደገዙ
-የአማራ ጭቆና በኦሮሞ ፣ 
 -እንግሊዝ በሱዳን : ኢትዮጵያ በኦሮሞ ያደረሱት ቅኝ ግዛት ንጽጽር፣ 
አማራ ኦሮሞ ላይ የጫነበት ማንነት ፣
-ኢትዮጵያ ኦሮሞ ላይ ያደረሰችው ወረራ፣ 
-ኦሮሞ ሀገር ስትሆን ኦሮሞ ውስጥ ያሉ ወራሪና መጤ ነፍጠኞች እጣ ፋንታ፣ 
-ኦሮሞ ሀገር ስትሆን የዜግነት ጉዳይና ሌሎች የመብትና ግዴታ ሁኔታ፣ “
– ሚኒሊክ እና ሀይለስላሴ ኦሮምኛን እንዴት እንደከለከሉ
ባለፉት ሠላሳ ሦስት ዓመታት በኦሮሞ ጥናት ማዕከል ውስጥ ከታተሙ ‹‹ጥናቶች›› ውስጥ ወደር በሌላቸው የጥላቻ ምስባኮች የታጨቁ ወረቀቶች ቀርበዋል፡፡ እናስ ምክትል ከንቲባው እነዚህን የጥላቻ ሰነዶች ነው የአገር ፖሊሲ እና መመሪያ እንዲሆኑ ፍላጎታቸውን በአደባባይ የገለጹልን?
ለሁሉም በየዓመቱ በጥናት ጉባኤው ላይ ከሚቀርቡ ወረቀቶች አኳያ የኦሮሞ ጥናት ማዕከል ከቆመላቸው ዓለማዎች ውስጥ  በጥቂቱ፡-
የሀገሪቱን የረጅም እድሜ ሀገረ መንግስትነት ታሪክ መናድ፣
• የጋራ እሴቶችን እና አኩሪ የጥንታዊ ስልጣኔ ውርሶቻችንን በአዎንታዊ ጎን ሳይሆን በአሉታዊ ጎናቸው ለትውልድ ማስተማር፣
• የሀገሪቱ አመሰራረት እንደ አብዛኞቹ የአለም ሀገራት ሁሉ ዘመኑ በወለደው የአገዛዝ ስርአት የተዘወረ ሳይሆን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት የተመሰረተች ኢምፓየር እንደሆነች ቆምንለት ለሚሉት ትውልድ ማስተማር፣
• በሀገረ-መንግስት ምስረታ ሂደት ለተፈጠሩ ቅራኔዎች መፍትሄው  ‹‹መገንጠል›› ነው በሚል ሲሰብክ የኖረ ስለመሆኑ እኛም ሆነ እነሱ የሚክዱት ሃቅ አይደለም፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ላንሳ! ባለፉት ሰላሳ ሦስት ዓመታት የኦሮሞ ጥናት ማዕከል (OSA) የኦሮሞ ገበሬዎችን እና አርብቶ አደሮችን ህይወት ለመቀየር የሚያግዙ ስንት ጥናቶችን ሰራችሁ? የጥናቱ ውጤት ምን ይመስላል?…
 ምክትል ከንቲባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ … ማህበሩ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለመደገፍ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንግዲህ ጨዋታውን በግልጽ አደረጉት ማለትም አይደል ? ሀገረ-መንግሥቱን የማፍረስ እና በኦሮሞ አምሳያ የመቅረጹ ሂደት ከወረቀት ወደ መሬት ለማውረድ ሰፊ ርቀት እየተጓዙ ያሉትን ሰዎች በዝምታ ማየቱ ኢትዮጵያን እንደመክዳት ይቆጠራል፡፡ ታከለ ኡማ በአደባባይ ፍላጎታቸውን ስለገለጹልን ‹‹ምስጋና›› ይገባቸዋል፡፡
Filed in: Amharic