>

የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ፍ/ቤት ውሎ!!! (ዳንኤል ሺበሺ)

የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ፍ/ቤት ውሎ!!!
ዳንኤል ሺበሺ
ዛሬ!
የጋዜጠኛው እስር የህግ አግባብነት የለውም! ይላል የህግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ ፡፡ ስለሆነም  habeas corpus (በህገ ወጥ መንገድ የታሰረ እስረኛ ፍርድ የማግኘትና ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት) ወይም <አካልን ነፃ> የማውጣት ክስ መስርቷል ፡፡
ይህን ክስ ሲመለከት የቆየው የልደታ መጀመሪያ ደ/ፍ/ቤት ለዛሬ ዕሮብ ሐምሌ 17ቀን 2011 ጧት 4:30 ቀጠሮ  ይዞ ነበር ፡፡ ቢሆንም ፖሊስ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን ወደ ፍ/ቤት ለማቅረብ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ይህንን በተመለከተ የህግ ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ ከላይ ለተጠቀሰው ፍ/ቤቱ አቤቱታ አቅርቧል ፡፡
አበቱታው  በጥቅሉ ፦
– ፖሊስ የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ አለማክበሩ ለህግና ይህ የፖሊስ እርምጃ ለፍ/ቤቱ ያለውን ንቀት ያሳያል፤ ህግ ሊከበር፤ ፍ/ቤቶች ሊደመጡ ይገባል፡፡ ስለዚህ የአዲሳባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ታስሮ ከደንበኛዬ ጋር እንዲቀርቡ ይታዘዝልን በማለት ጠይቋል ፡፡
–  የአዲሳባ ፖሊስ ተወካይ  በበኩሉ ምርመራ የሚያጣራው የአአ ፖሊስ ሳይሆን የፌዴራሉ ፖሊስ ነው፤ እኛ በአደራ ነው የተቀበልነው ብሏል፡፡ ክብርት ዳኛ “እስረኛው በአአ ፖሊስ አለ ወይስ የለም?” ብላ ለጠየቀችው ጥያቄ መልስ ሰጭው የአአ ፖሊስ ባልደረባ “እኔ አላውቅም!” በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ዳኛዋ ቀጠለችና “ተከሳሽ እናንተጋ መኖር ወይም አለመኖሩን ሳታውቁ ምርመራው የሚያጣራው ፌዴራል ፖሊስ ነው፤ እኛ በአደራ ተቀብለናል የሚል ደብዳቤ እንደት ፃፋችሁ?” እንደት አወቃችሁ በማለት ሲትጠይቀው  “እሺ ሌላ ትዕዛዝ ይሰጠንና በተባለው ቀን እናቀርባለን” በማለት ተከሳሹ በአአ ፖሊስ እጅ እንደሚገኝ በግላጭ አመነ ፡፡
 – የተከሳሽ ጠበቃ አቶ ተመም በምላሻቸው “በመጀመሪያ  ደረጃ፤ በህጋችን መሠረት የሰው ልጅ በአደራ አይቀመጥም፤ በአደራ የሚቀመጠው ንብረት ወይም ቁስና ገንዘብ ሲሆን ነው፤ ክቡር የሆነ የሰው ልጅ በምንም ምክንያት፤ በማንም እጅ በአደራ ሊቀመጥ አይችልም፤ ይህ የህግ ጥሰት ነው፤ በህግና ክቡር በሆነው ሰው ልጅ ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው! በዜጎች መብት ላይ መቀለድ ነው” በማለት ተከራክሯል ፡፡ በሌላ በኩል እስረኛውን መመርመር በህግ ሥልጣን  የሌለው አካል/ፖሊስም ቢሆን ማሰር አይችልም ፡፡ ስለሆነም ፖሊስ ዛሬም ከድሮ አስተሳሰብ የተላቀቀ አይመስለኝም፤ እኔም ሆንኩ ደንበኛዬና ቤተሰቦቹ እየተሰቃየን ነንና ከእስር እንዲለቀቅ ይታዘዝልኝ በማለት በአጽንኦት ጠይቋል ፡፡
***
ከችሎት መልስ ፦
በሌላ በኩል ከችሎት እንደወጣን  <የአአ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር  ታስሮ ከደንበኛዬ ጋር እንዲቀርብ ይታዘዝልኝ> በማለት ጠበቃ ተማም አባቡልጉ በመጠየቁ የተናደደ የአአ  ፖሊስ ባልደረባ አቶ ተማምን ሲያመናጭቀውና በኃይል ሲያቧርቅበት በዓይኔ ተመልክቺያለሁ ፡፡ ምን ይፈጠር ይሆን? እያልኩ ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት አድርጊያለሁ ፡፡ ለዚህ ጉዳይ ተብሎ ኮሚሽነርን የሚያህል ሰውን ታስሮ ይቅረብ ስትል ምን አስበህ ነው? በማለት በቁጣ ለማስፈራራት ሞክሯል ፡፡ አቶ ተማም’ም በምላሹ  “ከህግ አግባብ ውጭ ነገ አንተ ብትታሰር ስለ አንተም የምለው ይንን ነው” አትደፋብኝ! እያወራን ያለነው ስለ ህግና አሰራር  እንጂ ስለ ግለሰብ ጉዳይ አይደለም በማለት መልሰውለታል ፡፡
በሰዓቱ የወታደሩ ስሜት  ከተለመደው ሰውአዊ ቁጣ ወጣ ያለ በመሆኑ እና ጋዜጠኛ ኤልያስን በሕግ ፍትም ሆነ በሰብአዊነቱ ከኮሚሽነሩ አሳንሶ ለማየት የሄደበት ርቀት ብዙም ምቾት የሚሰጥ አልነበረም ፡፡ ውስጤ በጣም አዝኗል፡፡
በመጨረሻም፦
ለብይን  ከሰዓት በኀላ 9:00 ሰዓት ተቀጥሯል ፡፡
ችሎቱ ከሰዓት በኀላው ብይን ፦
ነገ ሐሙስ ሐምሌ 18 2011 ዓም ከሰዓት 10:00 ሰዓት ልደታ መጀ/ደ/ፍ/ቤት 8ኛ ችሎት (4ኛ ፎቅ ቢሮ ቁ. 420  ተከሳሹን የአአ ፖሊስ እንዲቀርብ #ጥብቅ_ትዕዛዝ ተላልፏል ፡፡ የነገ ሰው ይበለን!
Filed in: Amharic