>
5:13 pm - Sunday April 19, 4082

ጂጂጋ ያችን ሰዓት!!! (ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ)

ጂጂጋ ያችን ሰዓት!!!
ሙክታሮቪች ኡስማኖቭ
(ይህ ፅሁፍ በአብዲሌ ሄጎ ጂጂጋ ያየችውን መከራ በአይን ምስክርነት አምና የፃፍኩት ነው። አሁን የምደግመው በደቡብ ኢትዮጵያ ሀዋሳ እየታየ እየተሰማ ካለው አሰቃቂ ኩነት ጋር በእጅጉ ተመሳሳይነት ስላልው እንዲሁም በዚያ ቀውጢ ሰዓት የመሰከርኩት እና ስለኢትዮጵያ የተረዳሁትን ሃቅ ዳግም ልገልፀው ነው!!! 
ቀኑ ቅዳሜ፣ እንደማነኛውም ቀን ነበረ። አራት ሰአት ላይ በአንድ ቅፅበት፣ በሁሉም የጂጂጋ አደባባይ፣ ገበያ፣ ሰርጥና ጥግ ዋይታ በረከተ። ጥይት ተንጣጣ፣ የተኩስ እሩምታ ጦዘ። የሴቶች የልጆች ዋይታ፣ የናቶች ጩኸት፣ የዘራፊዎች ጭፈራና “አቢይ ዳውን ” ሄጎ ሄጎ” የሚል ፉከራ በረከተ። በመኪና ጡርንባ የታጀበው ጭፈራ እና ማቅራራት፣ ፉከራና መፈክሩ ከስቴድየም ወሳኝ ድል በሃላ
እንደሚታይ የደጋፊ ድጋፍ ነው የሚመስለው። ነገሩ የታሰበበት መሆኑ በጣም ያሳውቃል። ምድር ቁና ሆነች።
የኔ ቤት 06 ቀበሌ የሀበሻው ሰፈር ነው። በግቢው አጥር አጮልቄ ሳይ ወጣቶች የዘረፉትን ሲያሸሹ፣ በቆመጥና በስለት ሰውን ሲያባሩ፣ ያገኙትን በፍልጥ፣ በፌሮ ሲመቱ፣ ግቢ እየሰበሩ ሲገቡ አየሁ። መሳሪያ የታጠቁት ሲቶክሱ አየሁ። ይህ የተለየ ነገር መሆኑ ገባኝ።
የግቢያችን ሰዎች ለማይቀረው ዘረፈና ድብደባ ባዶ እጃችን ከምንጋፈጥ ራስን መከላከያ መፈለግ ጀመርን። ስለት፣ ድንጋይ፣ መጥረቢያ ተከፋፈልን። ለኔ የሆነች ጣውላ ነገር ሰጡኝ። የተገኘው ነገር ነው እንግዲህ። ሁሉን ቤቶች ትተን በአንድ ክፍል ውስጥ ተሰባሰብን።
እኔ አላስቻለኝምና ለመጨረሻ ጊዜ ወጥቼ ሳጮልቅ ተመትቶ ክፉኛ እየደማ፣ አጥሩን ተደግፎ የሚያቃስት ወጣት አየሁ። የግቢውን በር ከፍቼ ደግፌ አስገባሁት። የግቢውበር በሀይል በድንጋይና በብረት ተደበደበብን። ወጣቱ የጉራጌ ተወላጅ፣ ሱቁን ዘርፈው እሱን ደብድበው፣ወደ ሌላ ሱቅ ሲያመሩ እንደምንም ከተኛበት ተነስቶ መምጣቱን ነገረን። አጥበነው፣ አበረታተን አይዞህ አልነው። ግቢውን ዞምቡዊች ከበውታል። ሄጎ ሄጎ ይላሉ።
ለምን የሆነው ሆነ? ማን ናቸው ሄጎዎች? ምን እየተካሄደ ነው? ስልክ መደዋውል ጀመርኩ። አመፁ ሁሉ ቦታ ነው። ህዝባዊ አመፅ አይደለም። ሄጎ የተባሉ፣ በክልሉ
የተደራጁ፣ ምንም ሳይሰሩ ለወራት በፌክ መዋቅር ሲከፈላቸው የነበረ፣ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ፣ በድጋፍ ስም ለሽብር ያኮበኮቡ ወጣቶች መሆናቸውን ሰማሁ። አብዲሌ በድብቅ ያሰለጠናቸው፣ ከየእስርቤቱ የተፈቱ፣ ስራየሌላቸው ዱርዬዎች፣ ከየዞንና ወረዳ የሰበሰባቸው ወጣቶች ናቸው።
በራችን ይደበደባል፣ ዘለው ለመግባት ሞከሩ። የውሾቹ ጩኸት አስፈርቷቸው ተመለሱ። ጎሮቤት ገቡ። የሲቃ ጩኸት፣ ድብደባ ይሰማናል።
ትንሽ እንደቆየን የጥይት እሩምታ ግቢያችን በር ላይ ሰማን። ከሞት ጋር ተፋጠጥን። ዉሾቹ በግቢው ቀዳዳ ሾልከው ወጡ። ከሞት ጋር አይን ለአይን ተፋጠጥን። ተስፋ በመቁረጥ ትካዜ ውስጥ “በቃ ለዚሁ ነበር” አልኩ።
★ – ★— ★
# እንዲህነበር 2
በጭንቅ ውስጥ ለሰዓታት አሳለፍን፡፡ ጂግጂጋ ወደ ዶግ አመድነት እየተለወጠች ነው፣ ሲቃ፣ ጩሐት፣ ለቅሶ ይሰማ፣ በጣም የሚረብሽ! ተጎድቶ ያስገባነው ልጅ ማስታወክ ጀመረ! በጣም ተጎድቷል። ስልክ ጠየቀኝና ሰጠሁት። ሚስቱ ጋ ደውሎ ደህና ነኝ አታስቢ አላት። ድምፁ ውስጥ የስንበት ድባብ አለ። ከጅጂጋ ውጪ ስለሆነች ሳቋ ና ቀልዷ ከሱ አልፎ ለኔም ተሰማኝ።
የኪዳነምህረት ቤ/ክ መቃጠሏን በስልክ ስሰማ ጉዳዩ የተለየ እንደሆነ እና ከዚህ ቀደም ከነበሩ ብጥብጦች የተለየ መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ …..
ሃላ እንደሰማሁት አርብ ድሬ ላይ ጸረ አብዲ ስብሰባ አድርገው የ8 ነጥብ አቋም ሲያወጡ፣ አብዲም ክልሉን የሚገነጥል የምክርቤት ውሳኔ ሊያወጣ እና ለአለማቀፍ
ዜናዎች ለማሰራጨት እንዳሰበ ጭምጭምታዎች ወጡ! የአብዲኢሌ የምክር ቤት ውይይት ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ቀርቶ ከተሰጠው ወረቀት ውጪ ምንም ነገር ማንም የማይናገርበት ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ምክርቤት ነው አንቀጽ 39 ለውይይት የሚቀርበው፡፡
ቅዳሜ ጠዋት ይህን እንቅስቃሴ ለመገደብ መከለከያ ዋና ዋና የመንግስት መስሪያቤቶችን እንደ ቴሌ፣ ሚድያ፣ የመሳሰሉትን መክበብ ጀመረ፡፡ ወደ ምክር
ቤት መግባትን አገደ፡፡ አብዲ በቤተመንግስት መከበቡ ተሰማ፡፡ ከዚያ የሄጎ አደራጆች ቀድመው የተዘጋጁበትን እቅድ ይፋ አደረጉት፡፡ ከተማዋን ማውደም!!!
ስፕሬይ ቀለም ታደለ፣ መዝረፊያ፣ በር መስበሪያ፣ ካዝና ማንሻ ክሬን በመጠቀም ባንክ በጠራራ ጸሃይ መዘረፍ ተጧጧፈ!! መከለከያ ወረረን፣ ፕዝዳንታችን ታገተ
የሚሉ ወሬዎች ተሰራጭተው በብዙ የክልሉ ከተሞች ዘረፋው ተስፋፋ፡፡ የጂጅጋው ግን በጣም የተለየ ነበር፡፡
……. ተጠበን፣ ተጨንቀን፣ በተኩስ እሩምታ ተውጠን እያለ፣ ከስካሁኑ የተለየ የድረሱልን ጩኀት፣የሚካኤል ቤ/ክ ደወልን ተከትሎ በተከታታይ ተሰማ! ደውሉ የፀሎት መሳይ ሳይሆን በተደጋጋሚ፣ የማይቋረትና የአደጋ መጥሪያ አይነት የሚረብሽ ነበር።
አብረን ከተደበቅን ውስጥ የቤተክርስቲያኗ አካባቢ ያደጉ ልጆች በሩን ከፍተው በግቢው አጥር ሲመለከቱ ሚካኤል ቤ/ክ ከፍተኛ ጪስ ሲንቦለበል ተመለከቱ፡፡
“ሚኪን! እኮ ሚኪን?!” ብሎ አንደኛው ልጅ በንዴት አጓራ፣ እያየሁት ተለዋወጠ። የጂጂጋ 06 ወጣቶች ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ሚኪ ብለው ነው የሚጥሩት። “ሚኪየን” የመጨረሻ መሃላቸው ነው። ጥምቀት ድምቀቱን ለአስር አመት አይቻለሁ።
ያለምንም ወለም ዘለም እና ማንገራገር፣ ገጀራና ዱላ ይዘው በባዶ እግራቸው ወደ ቤተክርስቲያኗ ሮጡ! አወጣጣቸው ለመስዋዕትነት የመዘጋጀትና ሞትን የመቀበል የድፍረታቸውን ጣርያ ያሳያል! ለሀይማኖት የመሞመትን ክብር፣ ላሳደገቻቸው ቤክርስቲያን የመሰዋትን ትልቅ መንፈሳዊ ወኔ ያሳያል! ቀናሁባቸው! እንባዬ መጣ! ከጊቢያችን የወጠው አንዱ ልጅና ሌሎች ጎሮቤቶች ኡኡታ እያሰሙ ‹ውጡ! ውጡ!› እያሉ ቀሰቀሱ! ሌሎች ከዘራፊዎቹ ጋር በጨበጣ ገጠሟቸው! አጮልቄ ስመለከት አንድ ወጣት በአንድ እጁ ጄሪካን ውሃ በሌለኛው ቢላዋ ይዞ በሄጎዎች ተከቦ አየሁ። ውሃውን እያሳየ ባንድ እጁ ቢላዋውን እያሳየ ተዉኝ ልሂድ የሚላቸው ይመስላል። አላማው እሳቱን ማጥፋት ነው፣ ከከለከሉት ግን በቢላዋው ሊታገላቸው አንዳቸውን ገድሎ ሊሞት እንደቆረጠ ያስታውቅበታል። ከፈቱለት መውጫ፣ ወደ ቤተክርስቲያን ከነፈ።
የጥይት ድምጽ ይሰማል፣ በጥይት የተመቱና የቆሰሉ አየሁ። የተመቱትን እናቶች እየጎተቱ ወደ ጊቢ አስገቡና ወጥተው ደግሞ በየበሩ እያንኳኩ “ኸረ ስለሚካኤል” እያሉ ማደፋፈርና የተደበቁትን ማውጣት ተያያዙት። ማሸሽ፣ ሌሎችን ማገዝ፣ ማነሳሳት ተጀመረ!
ዘራፊዎቹ ቆራጥነታቸውን ሲያዩ አፈገፈጉ! ጋብ ሲል ተኩሱ ፣ ወጣቶቹ፣ ሴቶች፣ ልጆች ለቸርቿ ውሃ ማመላላስ ጀመሩ። ሌሎቹ ያፈገፈጉትን እየተከተሉ አባረሯቸው! በባዶ እግሩ የወጣው ልጅ ሚስማር ወግቶት እያነከሰ መጣ፣ የግቢውን በር ከፍቼ አስገባሁት። ነቀልንነት፣ እየደማ ተመልሶ እያነከሰ ሮጦ ወጣ!
በሚካኤል ቤተክርስቲያን ሰበብ የሀይል መመጣጠን መጥቶ እኔም ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን እንደማልሞት አምኜ ተነፈስኩ። የቸርቿ ደውል አዳነን! ከቀናት በሃላ
ሚስማር የወጋውን ልጅ አግኝቼ ‹እንዴት ድፍረቱ እንደመጣለት፣ ከነፍስውጪ ነፍስግቢ በቅጽበት እንዴት የጀግንነት ተግባር ውስጥ እንዴት ገብቶ እሱ ተርፎ እኛንም እንዳተረፈን ጠየቅኩት፡፡ ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በጂኦማቲክስ ከተመረቀ ሀያ ቀን አከባቢ ቢሆነው ነው። ግራጁኤሽን ፓርቲ የጫርንለት ባለፈው ሳምንት ነበር። ጭምትና ሳቂታ እንጂ እንዲህ ለጀግንነት ተግባር ማንም አያጨውም።
‹ሙክታሮ የቸርቿ ደወል አነዘረኝ! እራሴን አላውቀውም፣ እኔ እያለሁ ያሳደገኝ ቤተክርስቲያን ሲቃጠል ከማይ ሞት ይሻላል ብዬ ነው› አለኝና ከእንባውን ጋር ታገለ፡፡ ላለማልቀስ ጥርሱን ሲገጥም አየዋለሁ።
“ታውቃለህ ሙክታሮ ሚኪ መጠጊያችን ነው፣ እኛ ያለዚህ ቸርኝ ምንም ነን። ህይወቴን ቢወስዱት አይኔ እያየ የልጅነት አሳዳጊዬን መጠጊያዬን አይወስዱብኝ ብዬ ” ሳግ አቋረጠው። እንባው ኮለል እያለ በጉንጩ ላይ ወረደ። የኦርቶዶክስ ቤ/ክ ሀገርን እንዴት ስታድን እንደነበር ተገለጠልኝ!
Filed in: Amharic