>

“የፖለቲካ ትልቁ ጥቅሙ ሽፋን መስጠቱ!!!” (አዳም ረታ)

“የፖለቲካ ትልቁ ጥቅሙ ሽፋን መስጠቱ!!!”
አዳም ረታ
ከስንብት ቀለማት የተቀነጨበ  (በድአዳ ሊንጮ)
¨….ታውቃላችሁ ፖለቲከኞቻችን ትልልቅ ነገር እየተናገሩ ይማርኩናል። ጋዜጣ፣ ሬዲዮና ቲቪ አስደግፈው ያማልሉናል።
አንድ ዛፍ ይተክሉና ስለዚህ ስለተከሉት ዛፍ አስር ሰአት ያወራሉ። ይሄን የሚሰሙ የዋሃን እና ቂሎች፣ ዛፍ ብቻ ሳይሆን በቃ ደን ያደገ ይመስላቸዋል። ድርጊቱ ደቃቃ ቢሆንም ከጥዝጠዛው ብዛት የእውነት ትልቅ ይመስላቸዋል። በደኑ ማደግም በጣም ከማመናቸው የተነሳ እቆሙበት ወይ እተቀመጡበት ስለዚህ ስለተወራለት ደን ስለሆነው ዛፍ (እንዴት አንድ ዛፍ ደን ሊሆን እንደሚችል የሚመረምር ጥቂት ነው) በሰፊው ሊወያዩ ይችላሉ። የሚወያዩት እንዲህ ነው።
ለመሆኑ እንዲህ የተጠቀጠቀውን ደን እንዴት ልናልፈው ነው? (አንዱ ኮስታራ)
ለመሆኑ እዛ ውስጥ ያለው አውሬ ቢበላንስ? (ቦቅቧቃው)
ከመሄዳችን በፊት እንዲከላከለን የታጠቀ ሰው ካለ አብሮን እንዲሄድ ለምን እንለምንም? (ሌላ ብልጥ ነኝ ባይ ቦቅቧቃ)
ለመሆኑ ልጆቻችን ምን ሆነው ይሆን? እዚህ ቀረን እኮ። መላ ምቱ እስኪ! (ወላድ ወይዘሮ)
እንዴት እየመነጠርን መንገዱን ልንዘልቀው ነው (ቀጫጫ)
መንገድ መጀመራችን አይቀርም ብዬ ጠርጥሬ ገጀራ ልይዝ ነበር (ልበ ቢስ)
ያዝ ብዬህ ነበር ለምን ረሳህ? (ʻብዬ ነበርʼ ባይ)
ኧረ አላልክም! (ልበ ቢስ እንደገና)
ውሸታም አደረከኝ? (ነገር ነገር ሲለው ብዬ ነበር ባይ)።
ድርጅቶች ብናደርጋቸውም ይሰራል፤
የኮስታሮች ነጻ አውጪ ድርጅት (ኮነአድ)፣
ቦቅቧቆች ነጻ አውጪ ግንባር (ቦነግ)፣
የብልጥ ነኝ ባይ ቦቅቧቃ ግንባር (ብባቦግ)፣
የወይዘሮዎች ነጻ አውጪ ግንባር (ወነግ)፣
የቀጫጮች ካውንስል (ቀካ)፣
የልበ ቢሶች ኮሚቴ (ልበኮ)፣
የብዬ ነበር ግሩፕ (ብነግ)፣ ወዘተ……
እኔንና እኔን መሳዮች የሚሳነን የለም።
ቂሎች በሌለ ጉዳይ እንዲህ ያለ ቃል እየተመላለሱ ይቆዩና፣ ቁርሾ ተቀስቅሶ በበነጋታው የሁለት ወይም የሶስት ሰዎች ሬሳ እዛ ዛፍ ተተከለበት የተባለው ገጣባ ቦታ ላይ ይቀበራል።
ከቀብር መልስ ስለደረሰው ችግር የሚያጠና የሚመራመር አይኖርም። ʻእዚህ ጋ ዛፍ ነበር አልተባለም እንዴ?ʼ ብሎ የሚናገር፤ ʻሰው ሞቶ እንዲህ ስለ ዛፍ ታወራለህ ምነው ጨዋ አልነበርክም?ʼ ይባላል።
 ሰፋ አድርጌ ልመራመር ሲል፣ የሚቀናʻበት መዘናጊያ ይሰጠዋል። ከሰላሳ አመት በኋላ ʻምን አገኘህ?ʼ ቢባል የዚህ አገር ዶክተር የሚመልሰው የለውም። እንዲህ ዘመዶችዋ የተጋደሉባት አንዷ ቆንጆ፡ የሞተው ወንድሜ የገደለው ባሌ አዘኔ ቅጥ አጣ ከቤቴም አልወጣ ብትል ወዳ አይደለም። ቅጥ ማጣታቸው ከተጀመረ ቢከርምም ይረሱታል። ቅጥ ማጣት እንደ ቂጥኝ እንደሚወረስም ይረሳሉ። ቅጥ ማጣት መቼ እንደ ጀመሩ አያጠኑም። ቅጠ-ቢስ ሁሉ።
[…] አሁን የማወራው ስለ ሽፋን ነው!
ዘመን የሚያልፍ ልቡን የማይሰጥ ሽፋን አለ። ለአንድ ሐበሻ ከነጻነት የበለጠ ማታለያ አለ? ምን ይፈልጋሉ ከዚህ የበለጠ ውብ ነገር? ግን ይሄ ነጻነት የተባለውን ረቂቅ ነገር እስከዛሬ ምን እንደሆነ በትክክል ኖሮ ያየው አለ? (የ3000 ዘመን ታሪክ የጭቆና ታሪክ ነው እንል የለ) ካየ ነጻነት ነበርና ነጻነት ያስፈልገኛል አይልም። ከነበረበት ለምን ወደመረገጥ መርጦ ይመጣል? ካልነበረበት ደሞ ምን እንደሆነ አያውቅምና እንዴት ሊመኘው ይችላል? ግን በዚህ ቃል በነዚህ አራት ሆሄያት ብዙ ብዙ ሕይወት ያልፋል።
ብዙ ብዙ ሰው ይጠፋል።
ብዙ ብዙ ትሸወዳላችሁ።¨
Filed in: Amharic