>

"ፖለቲካ አይመለከተንም" ለምትሉ..... (ዮናስ አበራ)

“ፖለቲካ አይመለከተንም” ለምትሉ ….
ዮናስ አበራ
 
ለእነ “ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ” species
ከአንድ 9 ዓመታት በፊት የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ መስራችና ባለቤት ዶ/ር ፍስሃ በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ የፊት ገጽ ላይ ከትልቅ ፎቷቸው ጋር ወጥተው ነበር፡፡ በወቅቱ ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ኮሬንቲና ፖለቲካ በሩቁ ነው፡፡ ፖለቲካ በሚሸትበት አላሸትም” የሚል  በኋላ ላይ መተዛዘቢያ ያደረጋቸው የጅል clicheአቸው እንደ headline አብሮት ወጥቶም ነበር፡፡ ታዲያ በሳምንቱ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ላይ መስፍን ነጋሽ ደህና አድርጎ እንደተቻቸው አስታውሳለሁ፡፡ ዶ/ር ፍስሃ ከዚያ በኋላ እንደሚወራው ከሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት (ምክንያቱ ለብዙዎቻችን ግልጽ ያለሆነ) ያንን የመሰለ እንደልጃቸው ኮትኩተው ያሳደጉትን ዩኒቨርሲቲ ለሼኩ ሽጠዋል፡፡ ታዲያ አሁን ላይ “ፖለቲካና ኮሬንቲ በሩቁ ነው” ያሉትን አባባል ይደግሙት ይሆን? አይመስለኝም ።
ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ውጪ ሆኖ መኖር ይቻላል፡፡ የየትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ አቋም አለመደገፍም አለመቃወም ይቻል ይሆናል፡፡ ባጠቃላይ ግን ፍጹም ከፖለቲካ ውጪ ሆኖ መኖር ይቻላል ወይ?
እንደማንኛውም ዜጋ በሃገሪቷ ህግ ደንብና መመሪያ እየተዳደርክ ፖለቲካ እንዳይነካህ ሱሪህን ሰብስበህ ከፍ አርገህ ልራመድ ብትል እንኳን አትችልም፡፡
ነጋዴ ከሆንክ ፖለቲካና ፖለቲከኞች በሚያወጡልህ የንግድ ፖሊሲና ህግ ትተዳደራለህ፡፡ አስተማሪ ከሆንክ በአገሪቷ የትምህርት ፖሊሲ ነው የምትተዳደረው፡፡ ስለ ፍቺ፣ ስለ ውርስ፣ ስለ መሬት ይዞታ ጉዳይ እና ክርክር ቢገጥምህ ፍርድ ቤት ትሄዳለህ፡፡ እዚያ ደግሞ በአገሪቷ የፍትህ ህጎች ትዳኛለህ፡፡ እነዚህን ሁሉ ህጎችና ፖሊሲዎች ተረቅቀው የሚጸድቁትና ስራ ላይ እንዲውሉ የሚደረጉት በፖለቲካና በፖለቲከኞች እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በቅዱስ ቁርዓን አይደለም፡፡
ልጆችህ የሚማሩት የትምህርት ይዘትና ጥራትም (content & quality) የሚመራው በፖለቲከኞችና በፖለቲካ ነው፡፡ የአንተ ሰፈር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ኮብል ስቶን ሳይለብስ የላይኛው ሰፈር ቅድሚያ የተሰጠው በክፍለ ከተማህ አስተዳዳሪዎች ውሳኔ ነው፡፡ እነሱ ደግሞ የፖለቲካ ሹመኞች ናቸው፡፡ በቀደም አራት ኪሎ ባሻ ማነው ሰፈር የአጎትህ ቤት ፈርሶ ከከተማ ውጭ ወርውረዋቸው ወይም ዳስ ውስጥ ጥለዋቸው መንግስት መሬታቸውን በካሬ 100,000 ብር ሂሳብ ለባለሃብት “በጨረታ” የተሸጠው ፖለቲካ ባጸደቀው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ነው፡፡ ኮሬንቲ ይያዝህና ኮሬንቲ እያጣህ ጭለማ ቤት ውስጥ የምታድረው በኤልፓ ሃላፊዎች ሙትቻነት ነው!! እነዚህን ሙታን ሃላፊዎች አያደረገ የሚሾመው ደግሞ አራት ኪሎ የከተመው ከነሱው የማይሻል ሌላ ሙትቻ ስብስብ ነው!! 7 አመት ስለሞላው የአያትህ የመቃብር ቦታ አጽሙ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውሮ ቦታው ታርሶ ለሌሎች አዲስ ሟቾች የተዛወረው ካያትህ አስክሬን ብዙም የተሻሉ ባልሆኑ ሌሎች ሙታን ፖለቲከኞች ወጥቶ በጸደቀ መመሪያ ነው፡፡
ታዲያ ፖለቲካ አስክሬንና አጽምህን ሁሉ እየተመለከተ አንተ በቁም እያለህ ገና ሰጋህና ነብስህ ሳይለያየ በምን ሂሳብ ነው ፖለቲካ የማይመለከትህ?! አስከሬንህ እና አፅምህ እንኳን አልኩህ እኮ !!  ቀልደኛ !!
NB: አራት ኪሎ በገቡ ተረኛ ደናቁርት ሁሌ መመራት የማይታክታችሁ “ምሁራን” ዛሬም ሃገር እየፈረሰችም ተዘፍዝፋችሁ እርከንና ደሞዝ ጭማሪ ጠብቁ ብቻ !!
መጥኔ !
Filed in: Amharic