>

የቀድሞ የሐዋሳ ከንቲባ ለፍርድ ካልቀረበ አዲሱ ከንቲባ ሁከት ቢቀሰቅስ ምን ይገርማል! (ስዩም ተሾመ)

የቀድሞ የሐዋሳ ከንቲባ ለፍርድ ካልቀረበ አዲሱ ከንቲባ ሁከት ቢቀሰቅስ ምን ይገርማል!

by Seyoum Teshome

 

ትናንት ሀዋሳ ከተማ ዙሪያ ካሉ የሲዳማ ዞን ወረዳዎች የመጡ ወጣቶች ከሲዳማ የክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከመከላከያ ጋር በፈጠሩት ግጭት ምክንያት ከተማዋ በወጣቶቹ የሽብር ተግባር ስትናጥ ውላ ነበር:: ከከተማዋ ብዙም ባልራቀችውና ከሲዳማ ዞን ወረዳዎች አንዷ በሆነችው ወንዶገነት ከሲዳማ ብሔር ውጭ የሆኑ የሌሎች ብሔሮች ተወላጆች የንግድ ሱቆችና መኖሪያዎች ላይ ንብረት የማቃጠልና የማውደም እንዲሁም የዝርፊያ ተግባራት በአካባቢው ተወላጅና ራሳቸውን ኤጄቶ ብለው በሚጠሩ ወጣቶች ተፈፅሟል። በተመሳሳይ በይርጋለም እና አለታ ወንዶ ከተማዎች በሌላ ብሔር ተወላጆች ንብረትና የንግድ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ዝርፊያና የንብረት ውድመት ተፈፅሟል:: እነዚህ እኩይ ድርጊቶች የአብሮነት እሴቶቻችንን መሰረት የሚንዱ ከመሆናቸውም በላይ በጥቂት ራስ ወዳድና ሙሰኛ የአከባቢው ባለስልጣናት፣ እንዲሁም በፀብና ጥላቻ የታወሩ ‘ብሔርተኛ አክቲቪስቶች’ (violence and hate desiminating, warmongering ethnic-activists) የተቀነባበሩና የብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ናቸው። በመሆኑም የሚመለከተው የመንግስት አካል በአስቸኳይ ህግ የማስከበርና ፍትህን የማስፈን ግዴታውን ሊወጣ ይገባል::

በእርግጥ ትናንት ወደ ማምሻው የመከላከያ ሰራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ሀይሎች ወደ ይርጋለም ከተማ የገቡ ቢሆንም ውድመት ከደረሰ በኋላ (long after the damage is done) መሆኑ በክልሉ የተሰማሩ የፀጥታ አካላት ቀድመው ያኮበኮበ አደጋን የመተንተን አቅም (threat analysis and preimptive action capacity) ላይ የተመሰረተ የፀጥታ ሀይሎች የማሰማራት ስራ ላይ አነስተኛ ስራ እንደተሰራ አመላካች ነው:: በሌላ ጎኑ ሀዋሳ ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠር የመከላከያ ሰራዊትን፣ የፌዴራል እንዲሁም የክልሉን የልዩ ሀይል ፓሊስ ሀይል ያካተተ የፀጥታ አስከባሪ ሀይሎች ማሰማራቱ ከተማው ላይ የነበረውን የተጋረጠ አደጋ አጋኖ የማየት ዝንባሌ (a tendency to overestimate the threat) እንደነበር ያሳያል:: በእርግጥ ይህ ዝንባል (threat forecast bias) ባለፈው አመት በዚህ ወቅት ሀዋሳ ላይ ከተከሰተው አሰቃቂ ሁኔታ (scenario) የመነጨ እንደሆነ መገመት ይቻላል:: በአንድ በኩል ብዛት ያለው ሀይል መሰማራቱ የከተማው ነዋሪ በሩን ዘግቶ እቤቱ ከመቀመጡ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር ይችል የነበረውን እልቂት መቆጣጠር ሲያስችል በሌላ ጎኑ ደግሞ የክልሉ የፀጥታ ኮማንድ (regional security command) የአደጋ ቅድመ-ግምገማ ማትሪክሱን እንደገና ማጤን (revisiting the threat assessment matrix) እና በደህንነት የቁጥጥርና ክትትል (intelligence monitoring and surveillance) ስራዎች ላይ የበለጠ የተቀናጀ ስራ መስራት እንዳለበት ያመላክታል::

ዛሬ ጠዋት ረፉዱ ላይ በሀዋሳ ከተማ ዋና ዋና በመንግስት የሚተዳደሩ ሆስፒታሎች (የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እና አዳሬ ሆስፒታሎች) ውስጥ በአካል ተገኝተው የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደነገሩኝ ከሆነ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው የብጥብጡ አካል የነበሩ ወጣቶች በህክምና እርዳታ ላይ እንደነበሩና ብዙ የልጆቻቸው ሁኔታ በሀዘን ድባብ ውስጥ የከተታቸው እናቶችና አዛውንት አባቶች በአከባቢው እንደነበሩም ገልፀዋል:: ይህ አላስፈላጊ የዜጎች ጉዳትና አካባቢውን አላስፈላጊ ወደሆነ የቀውስ ቀጠናነት የሚከት ድርጊት በድጋሚ እንዲከሰት የሆነው ባለፈው አመት ሀዋሳ ላይ ለተከሰተው አስከፊና የብሔር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈፃሚዎችና አቀነባባሪዎች እንዲሁም አስተባባሪ የነበሩ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ አለመደረጋቸው፣ ይባስ ብሎም ለበለጠ የክልሉና የዞኑ ሹመቶች የመታጨታቸውና በብሔራቸው ዋሻ ውስጥ ተሸሽገው የህግ የበላይነት ላይ የተሳለቁበት ድርጊት የፈጠረው የማናለብኝነት ድፍረት ስለሰጣቸው ነው:: ለዚህ ደግሞ “የብሔር ግጭት ማስነሳት የተጠርጣረው የቀድሞ የሃዋሳ ከንቲባ በክልል ደረጃ የቢሮ ሃላፊ ሆኖ ተሾመ!” በሚል ርዕስ በፌስቡክ ያወጣነውን ፅሁፍ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፦

አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ የቀድሞው የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ ነው፡፡ ከሰኔ 04/2010 ዓ.ም ጀምሮ በሃዋሳ ከተማ በሲዳማና_ወላይታ ተወላጆች መካከል የተፈጠረውን አሰቃቂ ግጭት በማስተባበር ወንጀል ተጠርጥሮ የእስር ማዘዣ ተቆርጦበት ነበር፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከምን እንደ ደረሰ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ብቻ ግን አንድ ሰሞን የሁለቱ ዞን አመራሮች “ከፍትህ በፊት እርቅን ለማስቀደም!” ተፍ ተፍ ሲሉ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የዚህ ዓላማ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባን በደቡብ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል የአስተዳደርና ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አድርጎ ለመሾም ኖሯል፡፡ በከንቲባነት ዘመኑ ሃዋሳ ከተማን በብሔር ግጭት ያመሳት ግለሰብ የቢሮውን ፋይናንስ እንዲያምስ፣ የክልሉን ህዝብ እንዲያተራምስ ተሾመ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2011 ዓ.ም “በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ሹመት ተሰጣቸው” በሚል ርዕስ የሚከተለውን ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል፦

ከንቲባው አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በሐዋሳ ከተማና አከባቢዋ በአንዳንድ የሲዳማና የወላይታ ብሔረሰብ አባላት መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ እጃቸው አለበት በሚል ከሌሎች የከተማው አመራሮች ጋር ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወቃል።

አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ክስ እንደቀረበባቸው ቢታወቅም ለክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በምክትል ሃላፊነት ደረጃ የአስተዳደርና ፋይናንስ ሃላፊ ሆነው እንዲሰሩ የደቡብ ክልል መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ሹመት እንደሰጣቸው ነው የተሰማው።

በፌደራል ጠቃላይ አቃቤ ህግ ክስ የተመሰረባቸው የሀዋሳ የቀድሞ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ይባላሉ።

ከአንድ ወር በፊት በፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በይፋ እንደተገለጸው አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በሀዋሳ ከተማና አከባቢዎ በአንዳንድ የሲዳማና የወላይታ ብሄረሰብ አባላት መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ እጃቸው አለበት ተበለው ከሌሎች 33 ሰዎች ጋር የክስ ፋይ ተከፍቶባቸዋል።

የአቃቤ ህግ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተፈጸመውና በርካታ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት የከንቲባው እጅ እንዳለበት በተለያዩ ማስረጃዎች ተረጋግጧል።

እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በነበራቸው ሚና ችግሩን ከመቆስቆስ በተጨማሪ እንዲባባስ አድርጎታል ይላል የአቃቤ ህግ ፣ማስረጃ። ለጠፋው ህይወትና ለደረሰው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከንቲባው ቴዎድሮስ ገቢባና ሌሎች አመራሮች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ያትታል።

በዚያም መስረት ነው ከንቲባውና ሌሎች አመራሮች ላይ ክስ የተመሰረተው።

ከስድስት ወራት በኋላ፡ የአቃቤ ህግ ክስ በሂደት ላይ እያለ ግን በከባድ ወንጀል የሚጠየቁት የሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በክልሉ መንግስት ሹመት እንደተሰጣቸው ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ ላይ የተመለከተው።

በቁጥር 2 – 1- 29 1123/5074 በቀን 26 አምስተኛ ወር 2011 ከደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ለክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት የተጻፈ ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው፡ በፌደራል አቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸው በሂደት ላይ ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በምክትል ሃላፊነት ደረጃ የቢሮው የአስተዳደርና ፋይናንስ ዘረፍ ሃላፊ ተደርገው መሾማቸውን ይገልጻል።

ለተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች ግልባጭ በተደረገው በዚሁ ደብዳቤ ላይ አቶ ቴዎድሮስ ከጥር 22 ጀምሮ በተመደቡበት ሃላፊነት ስራቸውን በመጀመር በትጋትና በታማኝነት እንዲወጡት ማሳሰቢያ ተካቶበታል።

በአጠቃላይ አቃቤ ህግ በከባድ ወንጀል ክስ የሚፈለግ ግለሰብ ሹመት መሰጠቱ አነጋጋሪ ሆኗል።

ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ደውለን ምክትል የቢሮ ሃላፊውን አነጋግረን ስለጉዳዩ ቢያውቁም ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውልናል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው ግለሰብ በደቡብ ክልል መስተዳድር ሹመት የተሰጠቸውን የሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ከንቲባን ጉዳይ ይዘን ወደ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስልክ ብንደውልም ምላሽ ለማግኘት አልቻልንም።

በዚህ ዙሪያ የደቡብ ክልል መስተዳድርም ሆነ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምላሽ የሚሰጡን ከሆነ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስንጮህ እንደነበረው መንግስት አሁንም ቢሆን በብሔር የማንነት ጥያቄዎች ጀርባ የተደበቁ የብሔር ነጋዴዎችና የህገወጥነትና ስርዓት አልበኝነት የሚያተርፉ የመንደር ደላሎች (ethnic enterpreuners who stand to profit from brokering public chaos and lawlessness) በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አግባብ ካልዘረጋና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልቻለ ሀገሪቷ ወደ አደገኛ አቅጣጫ እያመራች መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል:: ምክንያቱም ዛሬ ላይ እሽሩሩ እያለ የሚኮተኩተው የብሔር-ጽንፈኝነት (አክራሪ-ብሔርተኝነት) ነገ አድጎ መንግሥትን ራሱ ጨርሶ መብላቱ የማይቀር ነውና!!

Filed in: Amharic