>

ለብሄረተኝነት መድሀኑቱ አንድነት!!! (ኤፍሬም ለገሰ)

ለብሄረተኝነት መድሀኑቱ አንድነት!!!
ኤፍሬም ለገሰ
በአሁኑ ወቅት አገራችን የምትገኝበት የፓለቲካ ውጥንቅጥ የጀመረው ከዛሬ 40 እና 50 ዓመታት በፊት የፍርሃቻ ርዕዮተ ዓለም ላይ የተደገፈ የጥላቻ፣ የሴራ፣ የመሰሪ፣ የውሸትና በውጪ ኃይሎችም ድጋፍ በማግኘት የጀመረ  ፀረ-ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ነው። ይህንንም ለማሳካት ጠላት የሚባልና አስጊ ይሆናሉ የሚላቸውን “ጠላቶች” በመፍጠርና ሊያደርሱ ይችላሉ የሚላቸውን የፍርሃቻ ጥፋቶች በማምረትና በተገኘው  አጋጣሚ የህዝብንና የተቃዋሚ ሃይሎችን ለማሸማቀቅ ይሰራል።
ይህንንም የሚያደርገው  እንደሚታወቀው አምባገነኖችና ራስ ወዳድ ቡድኖች ከመሳሪያ፣ ከሚከተላቸው አባል ሌላና ዋነኛው የሚጠቀሙበት ስልት የፍርሃቻ ፕሮፓጋንዳ ነው።
ብዙ ሺህ አመታት የፈጀብንና የገነባነው የፍቅርና የአንድነት እሴቶቻችንን በመሰሪ ሕገ-መንግሥት ተደግፎ ሊበታትኑን የተጫኑብን የዛሬ 40ዋቹና 50ዋቹ ዓመታት በተጀመረው የሴራ የቅዥትና በእራስ ወዳድነት የተለከፈው  የብሄር ፖለቲካ ዛሬ በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህም እዚያም ችግርችን ግጭቶችን እየቀሰቀሰ ማህበረሰባችንን እያመሰና ለማፈራረስ  እየሞከረ ይገኛል።
እንደ ምታዩት እና እንደምትሰሙት የአገራችን ፖለቲካ እያደር ከድጡ ወደ ማጡ እየሄደ መሆኑ ይታያል በተለይ እትዮጵያ እና እትዮጵያዊነትን የኦነግና የህወሃት ቡድኖች ለማጥፋት በቁርኝት እየሰሩበት ይገኛል።
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ለሚታየው የኦነግ(ኦዴፓ)_ኢህአድግ ባለሁለት ምላስ ስልታዊ የኦሮሞ የባለተራነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከአሁኑ ጀምሮ የተቃውሞ ድምፃችንን ማሰማት ይኖርብናል። ኦነግና ህወሃት በፀረ_ኢትዮጵያ በሽታ የተለከፉ በመሆናቸው  አንድ ናቸው።
በአዲስ አበባም ሆነ በባህር ዳር ከተማ በተከሰተው አሳዛኝና በሴራ የተሞላ የከፍተኛ አመራሮች ሞት በተነሳ በህወሃትና በአዴፓ መካከል በተፈጠረው ሰጣ ገባ ወይም መግለጫዋች መካከል የአይጥ ምስክር ዲንቢጥ እንደሚባለው የኦነግ አመራሮችና ዋና አቀንቃኞቹ የሴራ ሙያ መምህራቸውን ህወሃትን እንደ እነሱ ድንጋጤና ፍራቻ በተሞላበት መልኩ ድጋፋቸውንና ገለፃቸውን እርስ በርሱ በተፃረረ መልኩ አሰምተዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ አገሪቷን እየገዛ (እየመራ) የሚገኘው የኦዴፓ ወይም ኦህዴድ በአዴፓና በህወሃት መካከል እየተከሰተ ስላለው ምልልስ አስተያያት አለመስጠቱ የሚያሳየው ኦዴፓ በኦነግ መጠለፉንና የሱ አገልጋይ መሆኑን ነው ቀድሞ ተክስተው የነበሩትን ግድያዋች፣ መፈናቀልን፣ ዘረፋን፣ ወጣቱን ለመጥፎ ተግባራት መገፋፋት፣ ግጭቶች ሳንዘረዝር።
በfebruary 24 2019 ጠ/ሚንስትር አብይ ባደረጉት ንግግር በ3 ወይም 4 ወር ውስጥ በማንኛውም ብሄር ስም መደራጀት እንደሚያበቃና በአገር አቀፍ ፖለቲካ ወይም ሁሉን አቀፍ አደረጃጀት እናውጃለን የተባለው የህልም እንጀራ ሆኖ የቀረ ይመስላል። ምንም የመንግስት ቃል አቀባይና የመንግስት የደህንነት አማካሪውና  ሌሎች ባለስልጣናት የአገራችን ዋነኛው ችግር የብሄር ፖለቲካው ነው ቢሉም ዝምታውን መርጧል።
ሌላው የአገርንና የሕዝብን አንድነት የማፍረስና የማቀዝቀዝ ስልት መሰሪ ሕገ-መንግስት በመጠቀም አገርን በብሄር ወይም በጎሳ መከፋፈል ነው። ለዚህም ትርክታዊ ልብ ወለድ ታሪክ በመፍጠር አዱን ከሌላው ጋር ለማጋጨት የተሰራ ነው። ያለው ሕገ-መንግስት በይዘትም ሆነ በአፈፃፀም በአብዛኛው በአገራችንና በህዝባችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰላምና ፀጥታ  ፀር ሆኖ የተሰራ ነው። ስለዚህም ነው ይህ ሕገመንግስት የግጭትና የጥፋት መሳሪያ የሚባለው።
አሁን የተገኘው ለውጥ በብዙ ወገኖቻችን ሞት፣ ስቃይና መከራ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለውበት የተገኘ ሆኖ ሳለ ድሉን ለፓለቲካ ፍጆታ ለጥቂት ግለሰቦች አሳልፎ መስጠትና እነሱን ፍፁማዊ አድርጎ ማቅረቡ ትክክል አይመስለኝም በመጀመሪያ ቀናት ያሳዩን  በጎ ስራዋች እንደተመሰገኑ ሳለ። እነ “ቲማ ለማ” ኢትዮጵያዊነትን
ከፍ አድርገው  ሲያወድሱ የአንድነት እሴቶቻችንን እያያወደሱ ንግግሮች ሲያደርጉልን 100% በሚባል መልኩ ግልብጥ ብሎ ሕዝባችን ድጋፉን ሰጥቶ ነበር ፤ በአሁኑ ሰዓት በአንዳንድ ፍርደ-ገምድልና አድላዊ በሚመስሉ ተግባሮቻቸው በለውጡ አቅጣጫ  ጥርጣሬን ፈጥረዋል። ይህ ያሳየው ሕዝባችን ዛሬም እንደ ትላንቱ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመከባበርና በሰላም መኖርን እንጂ የጎጥ ፖለቲካ አጀንዳው እንዳልሆነ ነው። ስለዚህ በአገራችን የጎጥ ፖለቲካና ፓርቲዋች በአዋጅ እንዲወገዱልንና በሁሉም ፅንፈኛ ብሄርተኞችና አቀንቃኞች ላይ እርምጃ ቢወሰድባቸው የተጀመረው የዲሞክራሲ ጉዞ ከግቡ እንዲደርስ ይረዳል። አለዚያ አሁን ባለው ሁኔታ የሕዝብ ትግስት ያልቅና የናንተንም ውድቀት ያስከትላል።
በተረፈ ዛሬ የምንጋጭበት የጎሳ ማንነት፣ ሀይማኖቶቻችን፣ ባህሎቻችን (ኢሬቻ፣ አሸንዳ፣ ጨምበላላ፣ ጉግሳ፣ ሽምግልና፣ ኪነጥበብ፣ አልባሳት፣ ወዘተ) ፣ ቋንቋዋቻችን፣ ማህበራዊ አስተዳደሮች፣ ወዘተ የቆዩልን የኖሩልን እድሜ ለጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሕይወታቸውን አሳልፈው ስላሰባሰቡን ነው እንጂ ዛሬ ወይአረብኛ ወይ እንግሊዝኛ ወይ ፈረንሳይኛ ወይ ጣላንኛ ተናጋሪዋች ሆነን ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ማንነት በያዘን ነበር። ስለዚህ እንደ ሕዝብ ማቶኮር ያለብን በመከባበር ላይ የተሞረኮዘ አንድነታችን ላይ ሆኖ ሳለ የአገራችንንም የወደፊት ዕጣ ፋንታ የምንወስነው እኛ እንደ  ሕዝብ እንጂ ጥቂት የአንድ ፖለቲካ ወይም ድርጅት አባላት አለመሆናቸውን በድምፃችን በኩራት ኢትዮጵያዊ ማንነታችንን ማስመስከር ይገባናል።
ማንም ግለሰብ ሆነ መንግሥት ከሕዝብ በላይ መሆን አይችልም እኛም መፍቀድ የለብንም። ስለዚህ የላቲን አሜሪካ ነፃአውጭው ሲሞን ቦሊቫር እንዳለው ፍርሃቻችንን በጀርባችን ተሸክመን አገራችንን ለማዳን  በአንድ ድምፅ መነሳት ይኖርብናል።
በአጠቃላይ አሁን የሚታየውና የወደፊት እጣ ፋንታ አስፈሪ ጉዞ ላይ ስለሆነ ያለን አማራጭ የተከሰቱት ችግሮች እንዳሉ ሆኖ በደሎቻችንን ይቅር ተባብለን በአዲስ መንፈስ በመከባበር  እንነሳ። ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች የምናያቸው እንዳንድ ስርዓት አልባ ወጣቶችን ለዚህ ያበቋቸው የዛሬዎቹ አዛውንቶች  በብሄር ፖለቲካ ተመርዘው ሌሎችን የመረዙት ናቸው ስለዚህ ወጣቶቻችንን ማስተማርና ማረም የሁላችንም የዜጎች ግዴታ ነው። አገራችንን ወደ ሰላም መንገድ ማምጣት አስፈላጊና ብቸኛው አማራጭ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር የብሄር ፖለቲካ መጨረሻው ቤተሰብን ሳይቀር የሚበትን የሚያጠፋ የወረርሽኝ የካንሰር በሽታ ነው። ፕሮፈሰር መስፍን እንደሚሉትም እንዘጭ እንቦጭ እንዳይደጋገም ዝምታችንን እንስበር።
ያለ ፍራቻ ለመኖርና ህልማችንን እውን እንድናደርገው በአንድነት ለሰላም እንነሳ።
ኢትዮጵያ ትቅደም!!!!
Filed in: Amharic