>

የኦሮሞ ብሔርተኞች ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የኃይል አማራጭን ጭምር ያካተተው ድጋፋቸው ምን አስልተው ነው? (አቻምየለህ ታምሩ)

የኦሮሞ ብሔርተኞች ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ የኃይል አማራጭን ጭምር ያካተተው ድጋፋቸው ምን አስልተው ነው?
አቻምየለህ ታምሩ
የኦሮሞ ብሔርተኞችን ያህል የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ በኃይል ጭምር ለማስመለስ  የደገፈና መድረክ የፈጠረ አካል ያለ አይመስለኝም። የኦሮሞ ብሐርተኞች «የሐረሪ ክልል ይፍረስ፣ ሐረር የኦሮሞ ነች» እያሉ  የሲዳማ  ክልል ግን  እንዲፈጠር  ለሲዳማ ክልልነት ጥያቄ  የሰጡትን ያላሰለሰ ድጋፍ  ዓላማ በሚመለከት የተለያዩ ሰዎች በተለያዬ መንገድ ሲበልቱት ተመልክቻለሁ።
ሆኖም ግን በደቡብ ክልል ካርታ ላይ የሲዳማ ዞን የት እንደሚገኝ ልብ ባለመባሉ የኦሮሞ ብሔርተኞች ከሲዳማ ክልልነት ያሰሉትን ጥቅም በሙሉ እንዳይጤን  ያደረገ ይመስላል። የሲዳማ ዞን የሚገኘው በደቡብ ክልል ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ሲሆን በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ከምዕራብ አርሲ፣ በምዕራብ ከዎላይታ፣ በደቡብ ምዕራብ ከቦረና፣ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ በጌዲዮና በጉጂ ዞን ይዋሰናል።
ከዚህ የሲዳማ ዞን መገኛ ተነስተን ጌዲዮ ዞንን ስንመለከት ዛሬ የደቡብ ክልል አካል የሆነው ጌዲዮ የደቡብ ክልል አካል ሆኖ መቀጠል የሚችለው ሲዳማ ዞን የደቡብ ክልል አካል ሆኖ መቀጠል ከቻለ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ሲዳማ የጎዲዮ ዞን ከደቡብ ክልል ጋር የሚያገናኘው  ሌላ የመሬት ኮሪዶር ስለሌለ ሲዳማ ክልል ሲሆን የጌዲዮ ዞን ከደቡብ ክልል ይገነጠላል ማለት ነው።
የጌዲዮ ዞን ሲዳማ ክልል ሲሆን ከደቡብ ክልል ተለይቶ  ብቻውን  ሲቀር  ያሉት አማራጮች ሶስት ብቻ ናቸው፤ አንደኛው ራሱን የቻለ ክልል መሆን፤ ሁለተኛው አማራጭ  የሲዳማ ክልል ልዩ ዞን መሆንና ሶሰተኛውና የመጨረሻው እድል ፈንታው ደግሞ  ከሲዳማ ዞን  በስቀር በአራቱም አቅጣጫ የሚያዋስነው ኦሮምያ ክልል የሚባለው ክልል ውስጥ መጠቃለል ብቻ ነው።
የኦሮሞ ብሔርተኞች ብሔርተኞች ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ እለት  «ኦሮሞ ነን በሉ» ብለው ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ግዲዮ ከጉጂ አፈናቅለዋል። ይህ በግልጽ የሚያሳየው የኦሮሞ ብሔርተኞችን ጌዲዮን የመዋጥ ጉመዠታ ነው።
ሰማዩንም ምድሩንም የኛ ነው  የሚሉት የኦሮሞ ብሔርተኞች አዋሳ ድረስ ተገኝተው  በጉልበትም ቢሆን ሲዳማን ክልል እናደርገዋለን  በማለት የኃይል አማራጭንም ቢሆን እንደሚደግፉ ሲናገሩ የሰማናቸው  ሲዳማ ክልል ሲሆን «ኦሮሞ ነን በሉ» ብለው ሊውጡት ያሰቡት ጌዲዮ ዞን ከደቡብ ክልል ስለሚነጥልላቸው  ተገንጥሎ የሚቀረውን ጌዲዮ ዞን ወደ ኦሮምያቸው የማካተትና  የመጠቅለል ሕልም  አይኖራቸውም ማለት አይቻልም።  የሆነው ሆኖ ሲዳማ ክልል ሲሆን የጌዲዮ እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን የምናየው ይሆናል።
Filed in: Amharic